ኤርትራዊያን ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ኢንተርኔት እንዲያስገበላቸው እየጠየቁ ነው

0
770

ሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ትውልደ ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር ኢላን መስክ የኢንተርኔት አቅርቦት በኤርትራ እንዲጀምር የኤርትራ ተወላጆች በስፋት እየጠየቁ ነው።

ቢሊየነሩ ኢላን መስክ በጦርነት ላለችው ዩክሬን ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠቱን ተከትሎ ነው ኤትርራዊያኑ በትዊተር እያደረጉት ባለው ማኅበራዊ ዘመቻ ለኤርትራም ተመሳሳዩን እንዲያደርግ እየጠየቁ ያሉት።
የስፔስኤክስ መሥራች ኢላን መስክ በቅርቡ ስታርሊንክ የተሰኘ የሳተላይት የኢንተርኔት ማቀባበያን ለዩክሬን አቅርቧል፡፡

የሩሲያን ወረራ ተከትሎ የኢንተርኔት መቋረጥ ቢኖርም ዩክሬናዊያን በስታርሊንክ አማካኝነት አገልግሎት እያገኙ ነው፡፡

‘ስታርሊንክ ለኤርትራ’ (#Starlink4Eritrea) በሚል የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ቁልፍ ቃል በማስቀደም ጥያቄ እያቀረቡ ያሉት በብዛት በውጭ የሚኖሩ ኤርትራዊያን እና ትውልደ ኤርትራዊያን ናቸው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ኤርትራዊ ዳያስፖራ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይገኛል፡፡

ኤርትራ በኢንተርኔት አቅርቦት አለመኖር የተነሳ ዜጎች ከመረጃ ርቀዋል። አገሪቷ በኢንተርኔት ሥርጭት በአፍሪካ እጅግ ዝቅተኛ አቅርቦት ካለባቸው አገራት ቀዳሚዋ ናት፡፡ የኢንተርናሽናል ቴሌኮሚኒኬሽን ዩኒየን ባወጣው ሪፖርት የኤርትራ የኢንተርኔት ተደራሽነት በመቶኛ፣ ከ1 እጅ በታች መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይህም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዝቅተኛ ከሚባሉት የሚመደብ ነው፡፡

በመንግሥት የተያዘው ኤሪቴል በአገሪቱ ብቸኛው የኢንተርኔት አቅራቢ ነው፡፡

በኤርትራ የሞባይል ዳታ (ኢንተርኔት) ስለሌለ ሕዝቦቿ ኢንተርኔት የሚያገኙት በዋይፋይ ብቻ ሲሆን፤ ፍጥነቱም እጅግ ቀርፋፋ የሚባል ነው፡፡ እንደ ፌስቡክና ትዊተር የመሰሉ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ለመዝለቅም መንግሥትን ሊያስቆጣ ስለሚችል ዜጎች እንደ ቪፒኤን የመሰሉ መሽሎኪያዎችን ለመጠቀም ይገደዳሉ ሲል ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል፡፡

ኤርትራ እንደ አውሮፓዊያኑ 1993 ወዲህ በአንድ ፓርቲና ግለሰብ የምትዘወር ምርጫ የማይካሄድባት፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ነጻ ሚዲያ የሌለባት አገር ስትሆን፤ ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ የሩሲያን ወረራ ለማውገዝ ካልፈቀዱ አምስት አገራት አንዷ ነበረች፡፡

የቢሊየነሩ ኢላን መስክ ስታርሊንክ ዝቅ ባለ የህዋ ምህዋር የምትሾር ሳተላይት ስትሆን ያለ ምንም የፋይበር ዝርጋታ ሰዎች ኢንተርኔት እንዲጠቀሙ ታስችላለች፡፡ ስታርሊንክ አገልግሎቱን ለማስጠት ምድር ላይ ካለ ጣቢያ ጋር ግንኙነት መፍጠር ይኖርባታል፡፡
_________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here