አርብ መጋቢት 2 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአፋር እና በአማራ ክልሎች ላይ ሆነ ተብለው የተፈፀሙ ግድያዎችን ሳይጨምር በጦርነቱ ሳቢያ ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች ለሞት እንዲሁም 309 ንፁሀን ሰዎች ለቀላል እና ከባድ አካል ጉዳት መዳረጋቸውን ምርመራ ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
የተፈፀመው ግድያና የአካል ጉዳት በህወሃት ሃይሎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የተፈጸመም ነው ሲል ኮሚሽኑ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአፋር እና አማራ ክልሎች የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ያካሄደውን የምርመራ ሪፖርት ዛሬ አርብ መጋቢት 2 ቀን 2014 ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህም ከመስከረም እስከ ታህሳስ 2014 ባሉት 4 ወራት ባሰማራው የሰብዓዊ መብቶች ምርመራ ቡድን በአፋር እና በአማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በቆየው ጦርነት የተከሰቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን መመርምሮ በሪፖርቱ ማካተቱን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ 29 አባላቱን በማሰማራት በኹለቱ ክልሎች ባሉ 8 ዞኖች ተዘዋውሮ፣ ከ50 በላይ ቦታዎችን በማዳረስ፣ 427 ሚስጢራዊ ቃለመጠይቆችን፣ 136 ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት አመራሮች ጋር ስብሰባ በማድረግ እንዲሁም 12 የቡድን ውይይቶችን በማድረግ ሪፖርቱን ማጠናቀሩን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል።
በምርመራ ሪፖርቱም በሰሜን ኢትዮጵያ አማራ እና አፋር ክልሎች በተካሄደው ጦርነት ላይ በተሳተፉ ሃይሎች 403 ንጹሀን ዜጎች እንደተገደሉና ከ309 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተመላክቷል።
ኢሰመኮ ምርመራ ባደረገባቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች፣ በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች በተለይም እና በዋነኝነት በትግራይ ኃይሎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ተገድለዋል፤ በተጨማሪም በህገ ወጥ መንገድ ከተገደሉት በተጨማሪ 309 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋልም ተብሏል።
በተመሳሳይ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች በነበሩ የመንግሥት አስተዳደር ኃላፊዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ ያሏቸው ሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያን መፈፀሙም በሪፖርቱ ተገልጿል።
በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሺያዎችም፤ የትግራይ ኃይሎች እና የኦነግ ሸኔ አባላት ወይም ደጋፊ ናቸው በሚል የጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ ሕገወጥና ከዳኝነት ውጪ የሆኑ ግድያዎችን ፈጽመዋል፣ የአካል ጉዳትም አድርሰዋል ሲልም የኮሚሽኑ ሪፖርት አስታውቋል።
የህወሃት ሃይሎች በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀልን ሊያስጠይቁ የሚችሉ፤ የእገታ እና አስገድዶ መድፈር እንዲሁም የመሰወር ተግባራትን መፈፀማቸውም የኢሰመኮ ሪፖርት አመላክቷል። በአብዛኞቹ ምርምራዎች ከተደረሰው ሰፊ ሰብዓዊ ጉዳት ባሻገርም በሕወሃት ኃይሎች ሆን ተብሎ በታቀደ፣ በተጠና በተደራጀ መንገድ ስልታዊ የዘረፋ ተግባር መፈፀሙን ማረጋገጡንም ኢሰማኮ አስታውቋል።
በሰዎች ላይ ከተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶ በተጨማሪ የግለሰቦች ንብረት፣ አገልግሎት ሰጪ የመንግስት እና የግል ተቋማት በህወሃት ታጣቂዎች መዘረፋቸውና መውደማቸውም ተገልጿል።
በዚህም በአማራ ክልል 40 ሆስፒታሎች፣ 453 የጤና ተቋማት፣ 1 ሺህ 850 የጤና ኬላዎች በድምሩ 2 ሺህ 343 የጤና ተቋማት፤ በአፋር ክልል ደግሞ በድምሩ 66 የጤና ተቋማት ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል ተብሏል።
በተጨማሪም በአማራ ክልል 1 ሺህ 25 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ሲወድሙ፤ 3 ሺህ 82 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል መውደማቸውን በሪፖርቱ ተገልጿል።
በፋይናንስ ተቋማት በተለይም በ18 የንግድ ባንኮች 346 ቅርንጫፎች ላይ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ዘረፋ እና ውድመት በህወሃት ታጣቂ ኃይሎች መፈፀሙም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲመለሱ እንዳይቋቋሙ፣ ቶሎ እንዳያገግሙ እና ጥገኛ እንዲሆኑ መደረጉንም አስታውቋል።
የጤና መሰረተ ልማቶች በመውደማቸው በርካታ ነፍሰ ጡር እናቶች ህይወታቸው እንዳለፈም የገለፀው ኮሚሽኑ፤ ለአብነትም በአማራ ክልል መቄት ወረዳ ብቻ 8 ነፍሰ ጡር እናቶች በዚሁ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን በሪፖርቱ ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰማኮ) በሪፖርቱ የደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ፤ ሰብዓዊ ጥቃቶችን የፈፀሙትን ጨምሮ የሰብዓዊ መብትና የሰብዓዊነት ሕጎች ጥሰት የፈፀሙ እና ያስፈፀሙ ሰዎችና ቡድኖች ሁሉ ተጠያቂ ለማድረግ ገለልተኛ፣ ተዓማኒና የሰብዓዊ መብቶች ደረጃን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እንዲሁም የክስ ሂደት በአስቸኳይ እንዲጀመር አሳስቧል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ “ከአስራ አምስት ወራት በላይ የዘለቀው ጦርነት ከዚህ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም አድርገው ለፖለቲካዊ መፍትሔ ንግግር መጀመር ይገባቸዋል” ያሉ ሲሆን፤ በሪፖርቱ የተካተቱን ምክረ ሃሳቦች የመተግበሩ ሂደት በአፋጣኝ እንዲጀመር ለሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጥሪ አቅርበዋል።
_________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




