በዓመቱ ከቆዳ ኢንዱስትሪ ለማግኘት ከታቀደው የውጭ ምንዛሬ ግማሽ ያህሉ አልተገኘም

Views: 253

ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ወራት ከቆዳ ኢንዱስትሪው ለማግኘት ካቀደችው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ግማሽ ያህሉን እንኳን ማግኘት አለመቻሏን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ባለፉት ሰባት ወራት ከቆዳ ኢንዱስትሪው ከ121 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ታቅዶ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት 60 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብቻ በመገኘቱ የዕቅዱ 49 ነጥብ ሁለት በመቶ የሚሆነው ብቻ ተሳክቷል፡፡

በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ አራት ዓይነት ምርቶች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሲሆን፤ ባለፉት ሰባት ወራት በከፊል ካለቀለት ቆዳ 800 ሺ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፤ 57ሺ ዶላር ገቢ ተገኝቷል። አፈጻጸሙም ከአንድ በመቶ በታች ነው።

በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት 66 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ያለቀለት ቆዳ ኤክስፖርት ለማድረግ ታቅዶ 35 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዶላር ያህል ኤክስፖርት በማድረግ 53 ነጥብ ሁለት በመቶውን ለማሳካት ተችሏል።

እንዲሁም 37 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት የጫማ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 17 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 44 ነጥብ አምስት በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን፤ ከቆዳ ጓንት ሶስት ሚሊዮን 80ሺ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኤክስፖርት በማድረግ የዕቅዱን 72 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

በተጨማሪም ስድስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ የቆዳ እቃዎችና አልባሳት ምርት ኤክስፖርት ለማድረግ ታቅዶ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 87 ነጥብ ሁለት በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከዘርፉ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ 121 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 60 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡

አብዛኞቹ የቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያለቀለትን ቆዳ ለማምረት በሚፈለገው የብቃት ደረጃ ላይ ባለመገኘታቸው፤ በከፊል ያለቀለትን ቆዳ ገበያው ላይ በሚፈለገው መጠን ማስተዋወቅ ባለመቻሉ፤ በአሜሪካና በቻይና የንግድ ጦርነት ሳቢያ ዓለም ላይ የታየው ኢኮኖሚያዊ መቀዛቀዝ ለገቢው መቀዛቀዝ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩ ተገልጿል፡፡

የቆዳ ጥራት መጓደል፤ ፋብሪካዎች የምርት ስብጥሩን በማሳደግ የተለያዩ የገበያ አማራጮችንና መዳረሻዎችን ባለማፈላለጋቸው፤ ፋብሪካዎች የተረፈ ምርት መጣያ ቦታ ባለማግኘታቸው ምርታቸውን በተፈለገው መጠን እንዳያመርቱ እንቅፋት መፍጠሩ፤ ሰው ሰራሽ የኢንዱስትሪ ጨው አቅርቦት እጥረት መከሰቱና የመብራት መቆራረጥ የተጠበቀውን የኤክስፖርት ገቢ ከዘርፉ ለማግኘት ዋና ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸውን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com