አረቄና ጠጅን ጨምሮ የስድስት አገር በቀል የምግቦችና መጠጦች ደረጃ ጸደቀ

0
1155

አረቄና ጠጅን ጨምሮ የስድስት አገር በቀል ምግቦችና መጠጦችን ደረጃ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረጉን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ደረጃ የተዘጋጀላቸው ምርቶች በርበሬ፣ ሽሮ፣ ቆሎ፣ በሶ፣ ጠጅ እና አረቄ ሲሆኑ፣ ደረጃው የተዘጋጀው በጥናት ላይ ተመስርቶ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ይስማ ጅሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

እነዚህን የምግብ እና መጠጥ ምርቶች ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በማሰባሰብ፣ ባህሪያቸውን በመለየት ሠፊ ትንተና፣ ጥናትና ምርምር ተደርጓል ተብሏል። ይስማ አክለውም፣ ከተለያዩ ቦታዎች በቀለምና በጣዕም ኹሉንም ያማከለ ብዙ ዓይነት የበርበሬ፣ ሽሮ፣ ቆሎ፣ በሶ፣ ምርቶችን በማሰባሰብ ወይንም በመቀላቀል ጥናት እና ምርምር ተደርጎባቸው ደረጃው እንደጸደቀ ተናግረዋል።

የጠጅ እና አረቄ ምርቶችም ለማኅበረሰቡ ጤንነት ሲባል ደረጃዎችን ከማውጣት ባሻገር፣ የኢትዮጵያ የባህል መጠጥ እንደመሆናቸው መጠን ወደ ውጭ ገበያ በስፋት ለመላክ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህ ደረጃ መውጣቱ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከማሳደጉ ባለፈ፣ ጥራቱን የጠበቀ ምርት በመላክ ምርቱ በውጭ ገበያ ተፈላጊነቱ እንደሚጨምር ያደርጋል ሲሉ ይስማ ገልጸዋል።

ደረጃው አብዛኞችን ዘርፎች እንደሚዳስስ እና የምርት አገልግሎት፣ የአሠራር ሥርዓት፣ የሕግ ማዕቀፍ፣ የአስተሻሸግና የአቀማመጥ ኹኔታን ጨምሮ ዝርዝር መስፈርትን አማልቶ የያዘ ነው ተብሏል።
የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የሚያማሉ ምርቶች ከአገር ውስጥ ባለፈ ወደ ተለያዩ የውጭ አገራት ለገበያ እንደሚቀርቡ እና ደረጃዎቹን የማያሟሉ ምርቶች እንዲሁ እንዲያሟሉ አስፈላጊው የምክር እና የሥልጠና አገልግሎት የሚሠጥበት ሒደት መመቻቸቱን ኃላፊው ጠቅሰዋል።

ለዚህም ደግሞ ኢንስቲትዩቱ ለሥልጠና የሚረዳ ትልቅ አካዳሚ እንደገነባ እና በተለያዩ የሥራ አመራር ዘርፎች ላይ ማለትም በሥራ አመራር፣ በአካባቢ ሥራ አመራር፣ የምግብ ደኅንነት ሥራ አመራር፣ በኃይል ማመጣጠን ሥራ አመራር እና በሌሎች ተጨማሪ ዘርፎችም ላይ በተቋሙ አማካይነት ሥልጠና እየተሠጠ እንደሚገኝ እና ይሄም ለደረጃ አተገባበሩ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ኃላፊው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የደረጃዎችን ጥናትና ምርምር በዋነኛነት በማስተባበር በኩል ሚናውን እየተወጣ ነው የተባለ ሲሆን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የተለያዩ የምርምር ተቋማት፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችና አከፋፋዮች፣ አስመጭና ላኪ ድርጅቶች፣ ቸርቻሪ ነጋዴዎች፣ እንዲሁም ሸማቾች በጥናቱ ላይ በዋነኛነት ተሳታፊ እንደነበሩ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በተጨማሪ በሰባት ዘርፎች ላይ ማለትም በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ዘርፍ፣ በኬሚካል ውጤቶች ዘርፍ፣ በኤሌክትሮ መካኒካልና በኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ፣ በኤሌክትሮኒክስ ኬሚካል ዘርፍ፣ በመሠረታዊ ዝግጅት ዘርፍ በየጊዜው ደረጃ እያዘጋጀ ነው ተብሏል። የሕብረተሰቡን ጤና እና የአካባቢን ደኅንነት ለመጠበቅ ደረጃ ማውጣቱ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ በተለይም በቡና፣ በቆዳና ሌጦ ምርት ላይ በየጊዜው የምታደርገው የደረጃ ማውጣት ሥራ እንደሚበረታታ እና ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ ከላይ ከተጠቀሱት ምርቶች በተጨማሪ በሌሎች ምርቶች ላይ በየጊዜው እየተከታተለ ደረጃ የማውጣቱን ተግባር እንደሚያሳድግ ኃላፊው ተናግረዋል።

ኤጀንሲው መስከረም 20/2014 ባካሄደው 32ተኛ መደበኛ ስብሰባው በምግብ እና የግብርና ውጤቶች ዘርፍ፣ የወተት እና የወተት ተዋጽዖ ማቀነባባሪዎች ላይ 14 አዲስ፣ 17 በክለሳ፣ እንዲሁም አራት አስገዳጅ ደረጃዎችን ማጸደቁ አይዘነጋም።
ምክር ቤቱ የምግብና ግብርና ዘርፍን ጨምሮ፣ በሰባት ዘርፎች 332 አዲስ፣ 190 የተከለሱ፣ እንዲሁም 184 በነበሩበት የቀጠሉ፣ በድምሩ 706 ደረጃዎች ላይ የመጨረሻ ረቂቆች ቀርበውለት ኹሉንም ደረጃዎች መርምሮ ማጽደቁ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here