ባልደራስ በ46 ዕሥረኞች ላይ የተሠጠው ውሳኔ ሕገ ወጥ ነው ሲል ገለጸ

0
881

ፓርቲው ሠላማዊ ሰልፍ አደርጋለሁ ብሏል

ባሳለፍነው መጋቢት 1/2014 በዋለው ችሎት፣ 34 የባልደራስ አባላትና የአዲስ አባባ ወጣቶች ወደ አባ ሳሙኤል ዕሥር ቤት መወሰዳቸው ሕገ ወጥ ተግባር በመሆኑ፣ ሠላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

የፓርቲው ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ “ሕገ አለ ብለን ለሕግ ተገዢ ሆነን ወደ ዕሥር ቤት ብንሔድም፣ በአንጻሩ ግን ዕሥረኞቹ በመጀመሪያ ፍርድ ቤት እያሉ፣ አንድ ፋይል ተከፍቶባቸው በሒደት ላይ ሳሉ ኹለተኛ ፋይል መክፈት ሕገ ወጥነት ነው” ብለዋል።

በምርመራ ላይ የነበሩትን ዕሥረኞች ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ሰኞ ዕለት እመለከተዋለሁ የሚል ቀጠሮ ሲሰጥ ዕሥረኞቹን ጭነው ወደ አባ ሳሙኤል ዕሥር ቤት ወስደዋቸዋል ያሉ ሲሆን፣ በምርመራ ላይ ያሉ ዕሥረኞች የሚታሠሩት በወረዳ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ፣ ካልሆነ ደግሞ በአዲስ አባባ ፖሊስ ኮሚሽን ነው ብለዋል።

አክለውም፣ ክስ የተመሠረተባቸው ዕሥረኞቹ ወደ አባ ሳሙኤል ዕሥር ቤት ሲሔዱ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሲሉ ያሳወቁት እስክንድር “ክስ የተመሠረተባቸውና ውሳኔ ያልተሰጣቸው እስረኞች ደግሞ የሚታሠሩት ቃሊቲና ቃሊቲ ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በመሆኑም፣ ይህን እና ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራትን መሠረት በማድረግ ሕዝቡን በማስተባባር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሰልፍ ለማድረግ እንገደዳለን ነው ያሉት። ይህንን የሚያደርጉት ወደ ማይፈልጉት አቅጣጫ እየተገፉ በመሆናቸው እንጂ፣ ኢትዮጵያ ባለችበት አሁናዊ ሁኔታ ይህን ለማድረግ ፈልገው እንዳልሆም እስክንድር አብራርተዋል።

የባለሥልጣናቱ ሥም ጠፋ ተብሎ በተመሠረተባቸው ክስ መሠረትም፤ “እኛ አገር ላይ ያሉ ባለሥልጣናት የተለየ ከለላ አላቸው፤ ሠው ሲሰድባቸው ፖሊስ ፈጥኖ ሒዶ ክስ ይመሰርትላቸዋል ማለት ነው። ኹላችንም በሕግ ፊት እኩል ስለሆንን ተዘለፍኩ፣ ተሰደብኩ የሚል ሠው ሒዶ ለፖሊስ አመልክቶ ፖሊስ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት ይመራዋል እንጂ አያስርም። አሁን እየሆነ ያለው ግን ከፕሮቶኮል አኳያ ሳይሆን ከሕግ አንጻር ትክክል አይደለም” በማለት ነው እስክንድር የተናገሩት።

አስቴር ስዩም ተባሉት የፓርቲው አመራር በበኩላቸው፣ ዕሥር ቤት መታሠር ዛሬ ባይጀመርም ገና ውሳኔ ያልተሰጠበት የምርመር ሒደት ላይ ያለ ታሳሪ ወደ አባ ሳሙኤል ዕሥር ቤት ሲሄድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ብለዋል። አስከትለውም ይህ ከሕግ አንጻር ትክክል አይደለም ያሉ ሲሆን፣ “በተጠርታሪዎች ላይ ጥቃት ለማድረስና ግፍ ለመፈጸመም የታሰበ ድርጊት ነው ብለን እንናምናለን” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“ሠንደቅ ዓላማን በተመለከተ፣ የአዲስ አባባ ከተማ ከንቲባ የዓድዋን በዓል በተመለከተ በሠጡት መግለጫ ምንም ዓይነት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ እንደሌለ መግለጻቸውን አንስተው፣ ከተማዋን የሚያስተዳድሩ ከንቲባዋ ይህን የመሠለ ሐሳብ ሠጥተው ዛሬ ደግሞ ይዘው የወጡበት ኹኔታ ወንጀል ነው ማለት ኹለት የሚጣረሱ ሐሳቦች ናቸው” ሲሉ አመራሯ ጨምረው ገልጸዋል።

እስክንድር በበኩላቸው፣ የባንዲራውን ጉዳይ “ሕጉ በግልጽ ሕገ ወጥ አድርጎታል። እኛ ግን ሕጉን አናከብርም። በተደጋጋሚ ተናግረናል። ሕጉ የሚጠይቀንን መስዋዕትነት እንከፍላላን” ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም “እንደዚህ ዓይነት ቅጥ ያጣ ሕግ አናከብርም” ያሉ ሲሆን፤ “ሠንደቅ ዓላማችን ታሪካችን፣ አሻራችን በመሆኑ ሠንደቅ ዓላማችንን አትያዙ የሚለንን በጭንቅላታችን ጥይት ቢሰዱብን እንደያዝናት እንሞታለን እንጅ አንቀበልም” ሲሉ ነው አቋማቸውን የገለጹት።
ፓርቲው ከክልላዊ ወደ አጋራዊ ፓርቲ እንደሚያድግ ካሁን በፊት ለአዲስ ማለዳ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ላይ ጥያቄውን ለምርጫ ቦርድ እንዳስገቡና በክልሎች ፊርማ የማሰባሰብ ሒደቱን ለማስጀመር ምርጫ ቦርድ ለክልል መስተዳድሮች ትብብር እንዲያደርጉ የሚጽፈውን ደብዳቤ አስገብተው ምላሹን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አስክንድር ጠቁመዋል።

ባሳለፍነው የካቲት 23/2014 በተከበረው የዓድዋ በዓል የተሳተፉና ሕዝቡን ለኹከትና ብጥበጥ አነሳስታችኋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው 34 የባልደራስ አባላትና የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ በአጠቃላይ 46 ታሳሪዎች ባሳለፍነው መጋቢት 1/2014 ወደ አባ ሳሙኤል ዕሥር ቤት ተወስደዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here