የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለምን አይተባበሩም? ታሪክ – ነባራዊ እውነታ – መፍትሔ

0
903

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለቁጥር የሚቸግሩ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖራቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው። ከእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ ብዙዎቹ ይህ ነው የሚባል የርዕዮት ዓለም ልዩነት የላቸውም። “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” የሚለው ነባር ትችት ለኹለት ዐሥርት ዓመታት የዘለቀውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ባይላቀቀውም፣ ፓርቲዎቹ ግን በመተባበር ፈንታ እንዲያውም ወደ ብዙ እየተሰባበሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ታምራት አስታጥቄ ይህንን ችግር በመንተራስ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ድርጅቶች መተባበር አለመቻል ታሪካዊ መሠረት፣ ነባራዊ እውነታ በመመርመር ቀጣይ የመፍትሔ ሐሳቦች ለመጠቆም የጥናት ሰነዶችን በማገላበጥ እና ባለሙያዎችን በማነጋገር ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ አቅርቦታል።

የፖለቲካ ፓርቲ ጅማሮ በኢትዮጵያ
በዓለም ላይ በተለይም በምዕራባውያን ስርዓተ መንግሥት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኝ ሚና መጫወት የጀመሩት ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመሆኑ በጉዳዩ ዙሪያ የተፃፉት ድርሳናት ያወሳሉ። በኋላም ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡ በላቲን አሜሪካ፣ እስያና አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ አገራት የብዝኃ ፓርቲ ስርዓትን ተቀላቅለዋል።

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የቅኝ ግዛት ሰለባ ባትሆንም ፍፁማዊ በሆነ የፊውዳል ንጉሣዊ አገዛዝ ሥር በመሆኗ ምንም ዓይነት ፓርቲን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ባሕል አልነበራትም። በዘመናዊት ኢትዮጵያ የመጀመሪያው በሕግ የተመሠረተው ብቸኛ ፓርቲ በወታደራዊ ሶሻሊስታዊ የደርግ ዘመነ መንግሥት መስከረም 1 ቀን 1977 የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) እንደሆነ በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ተከትቦ እናገኘዋል።

ይሁንና የተደራጁ የፖለቲካ ቡድኖች ሕጋዊ ዕውቅና ባይኖራቸውም እንቅስቃሴ የጀመሩት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደነበር ይታወቃል። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ሰለሞን ገብረዮሐንስ በ‘European Scientific Journal’ በ2014 (እ.አ.አ) ‘Political Parties, Party Programmaticity And Party System in Post 1991 Ethiopia and Party System’ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ ንጉሣዊ ስርዓቱን መቃወም ሕገ ወጥ በመሆኑ፥ እነዚህ የፖለቲካ ቡድኖች ወይም ኃይሎች እንቅስቃሴ ያካሔዱ የነበሩት በኅቡዕ ወይም በነፍጥ በታገዘ ትግል ወይም ደግሞ ኹለቱንም አጣምረው እንደነበር በጥናታቸው አመላክተዋል።

በተመሣሣይም በደርግ ዘመነ መንግሥት ሁሉም ዓይነት የተቃውሞ ፖለቲካ ኃይሎች እንዲታገዱ፣ እንደ ወንጀል እንዲቆጠር እና የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ተደርጓል። ስለዚህ በኢትዮጵያ ስለ ብዝኃ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ መነጋገር የሚቻለው ከደርግ መንግሥት ውድቀት ማግስት በሕጋዊነት ከተፈቀደበት የ1983 የስርዓት ለውጥ በኋላ ባለው ዘመን ነው።

የፖለቲካ ፓርተዊዎች ብየና
ሚናቸው እና ዓይነታቸው
በፖለቲካ ፓርቲ ዙሪያ የተጻፉ ድርሳናት እና ጥናቶች የፖለቲካ ፓርቲ ብያኔን በተመለከተ አንድ ወጥ ፍቺ እንደሌለ ያመለክታሉ። ይሁንና በአጠቃላይ የፖለቲካ ፓርቲ ተግባሮች፣ በባሕርያትና ዓላማዎቹ ሊበየን እንደሚችል ግን ያመለክታሉ።

 

“ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት ከሔድን ይሔ [ከ90 በላይ ፓርቲዎች አሉ የሚባለው] የተሳሳተ መልዕክት ያስተላልፋል። በተጨማሪም ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም እንደማጥቂያና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተዓማኒነት ለማሳጣት ኢሕአዴግ ሊጠቀምበት ይችላል”

 

‘ኤሲኢ ኢንሳይክሎፔዲያ’ በ2013 (እ.አ.አ) የፖለቲካ ፓርቲ ማለት “የተደራጁ ሰዎች ስብስብ ሆኖ በሕግ የተሰጣቸውን መብቶች የሚተገብሩበት፣ ተመሣሣይ የሆነ የፖለቲካ ዓላማዎችና አመለካከቶች ያላቸው እንዲሁም በሕዝባዊ ፖሊሲዎች ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የራሳቸውን ዕጩ ተወዳዳሪ ለምርጫ በማቅረብ የመንግሥትን ቢሮ ለመያዝ የሚንቀሳቀሱ” ብሎ ብያኔውን ያስቀምጣል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በማኅበረሰባቸው ውስጥ የተለያዩ ተግባራት እንደማያከናውኑ ሰለሞን በጥናታቸው ዘርዝረዋል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል፡- አማራጭ ፖለሲ ያቀርባሉ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ አቅጣጫን ያመለክታሉ፣ እንዲሁም የስርዓተ መንግሥትን (‘ገቨርንመንት’) አጀንዳዎች በራሳቸው መንገድ ይቀርፃሉ። በተጨማሪም ውክልና፣ ልኂቃንን ማሰባሰብ እና መመልመል፣ ግብ ማስቀመጥ፣ ፍላጎትን ማሰባሰብና መግለጽ፣ የሕዝብ አስተያየቶችን ወደ መንግሥት ማስተላለፍ፣ ሕዝብን ማቀራረብና ማደራጀት፣ ተዓማኒ የፖለቲካ ስርዓት መፍጠርና መንግሥት ማቋቋም የሚጠቀሱት ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባራት ናቸው።

አንድሪው ሔይዉድ የተባሉ ጸሐፊ ‘Politics’ በሚል ርዕስ በ2002 (እ.አ.አ) ባሳተሙት መጽሐፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓይነታቸውን ለመወሰን የሚጠቅሙ መሥፈርቶች (‘ፓራሜትር’) እንደሚከተለው ይዘረዝራሉ።

እነርሱም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደራጁበት አግባብ/ደረጃ፣ በማኅበረ ፖለቲካ ግባቸው፣ በሚወክሉት የማኅበራዊ መደብ፣ በሚጫወቱት ዋና ዋና ሚናቸው እንዲሁም ባላቸው የፖለቲካ አቋም ወዘተ. መሥፈርቶችን ወስዶ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የካድሬ ወይም የብዝኃ (‘ማስ’)፣ የውሕደት ወይም የውክልና፣ ሕዝባዊ ፓርቲ ወይም የተለየ ፍላጎት፣ ግራ ወይም ቀኝ ዘመም ፓርቲ በመባል መክፈል እንደሚቻል በዝርዝር አስቀምጠዋል። የተቃዋሚ ፓርቲዎችም (በዘመኑ ቋንቋ ተፎካካሪ ፓርቲዎች) ያለውን ስርዓት ተቃዋሚ ወይም ተስማሚ (conforming) ሊሆኑ እንደሚችሉም ጽፈዋል። በኢትዮጵያም ነባራዊ ሁኔታ እንደሚታየው ፓርቲዎች ዘውግን መሠረት ያደረጉ ወይም ኅብረ ብሔራዊ ሊባሉ ይችላሉ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ዓይነቶች (‘ታይፖሎጂ’)
ተሾመ ወንድወሰን ‘Ethiopia Opposition Political Parties and Rebel Fronts: Past and Present’ በሚል ርዕስ በ‘Academy of Sciences, Engineer and Technology’ ከዐሥር ዓመታት በፊት ባሳተሙት ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች በኹለት ሰፊ ጎራዎች ሊመደቡ እንደሚችሉ በጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።

ከሕገ መንግሥት ውጪ የመንግሥት ለውጥ የሚፈልጉ እና በሕገ መንግሥቱ አጥር ተወስነው የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ በማለት ይከፍሏቸዋል።
በመጀመሪያዎቹ ጎራ የሚመደቡት ነፍጥ ያነሱ፣ የኅቡዕ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሲሆን፥ ብዙዎቹ ቅድመ 1983 የተቋቋሙ፣ ወታደራዊና ሲቪል ክንፍ ያላቸው፣ ብዙዎቹ በውጪ አገራት መሠረታቸውን የጣሉ እና በሕግ የታገዱ ናቸው። በወቅቱ ኦነግ ለዚህ ጎራ ዓይነተኛ ምሳሌ መሆን ነበር። በሌላ በኩል በኹለተኛው ጎራ የሚመደቡት ከ1983 በኋላ በሕግ የተመዘገቡ፣ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ በክልል ደረጃ ወይም በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተደራጁ ናቸው።

በርግጥ ከመጋቢት 2010 ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በመካሔድ ላይ ያለው የለውጥ ሒደት ኹለቱን ጎራዎች ወደ አንድ መድረክ ማምጣቱ ይታወቃል። በሕግ ደረጃ በኢትዮጵያ ምድር እንዳይንቀሳቀሱ የተከለከሉ የነበሩት ድርጅቶች አርበኞች ግንቦት 7፣ ኦነግ እና ኦብነግን ጨምሮ ሌሎችም ‘ነፍጣቸውን ጥለው’ አገር ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።

መሰባሰብ አለመቻል
በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ በፖለቲካ ፓርቲነት የመደራጀት ሙከራ በ1960ዎቹ ከጀመሩት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የግራ ዘመም ሶሻሊስት ርዕዮት ዓለም ተከታዮቹ መኢሶንና ኢሕአፓ ናቸው። የመከፋፈል ፖለቲካውም የተጀመረው በእነሱ እንደሆነ በብዙዎች ተጽፎ ይገኛል።

 

አዳነ “ለኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጓት ቢበዛ ሰባት የሚያህሉ ፓርቲዎች ናቸው” ይላሉ። “ይህ የሚሆነው ግን ብዙ መፈታት የሚገባቸውን ጥያቄዎች መልስ መስጠት ሲቻል” እንደሆነ አሳስበዋል።

 

መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ‘የኢትዮጵያ ታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ሕልሞች፡ የኢሕአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ’ በሚል ርዕስ በ2008 ባሳተሙት መጽሐፍ “ኹለቱም [መኢሶንና ኢሕአፓ] ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በቀጥታ የወጡና የተማሪው ንቅናቄ የጋራ ትግል ቀጥተኛ ወራሽ ስለነበሩ ከልምድ ማነስ ውጪ የተባበረ ትግል ለመምራት የተሻለ ታሪካዊ ዕድል ነበራቸው። ሆኖም አልተጠቀሙበትም” በማለት አስፍረዋል።

መረራ በመጽሐፋቸው የመኢሶኑ ኃይሌ ፊዳ አልጄሪያ ድረስ በመሔደ በዋናነት ኢሕአፓን ከፈጠረው ብርሃነ መስቀል ረዳ ቡድን ጋር ተነጋግሮ ነበር፤ ይሁንና ቡድኑን ለማሳመን ግን እንዳልተሳካለት ቁጭት በሚመስል አገላለጽ “የዚህ የመጀመሪያው ተባብሮ የመታገል ጥረት መክሸፍ ኃይሌ ፊዳንና ብርሃነ መስቀል ረዳን ጨምሮ የአንድ ትውልድ ምርጦች ውድ የሕይወት ዋጋ ከፍለውበታል” በማለት አስቀምጠውታል።

ከወታደራዊ ደርግ መንግሥት ውድቀት በፊትም እንዲሁ የመኢሶንና የኢሕአፓ አመራሮች ደርግ ከመውደቁ በፊት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት (ኢዲኃቅ) የሚል ኅብረት ከሌሎች በመሆን ፈጥረው እንደነበረም ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሯል። “እንደአነሳሳቸው የመከፋፈል ፖለቲካን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋት አዲስ ታሪክ ይፈጥራሉ ተብሎ ተስፋ ቢያደርግም የተሠሩበትን የታሪክ አጥር ሰብሮ መውጣት አልቻሉም። …የጋራ ድርጅታቸው ኢዲኃቅ ተገቢ ቀብር ሳያገኝ አንድ እርምጃ እንኳን ወደፊት ሳይወስዳቸው ሞቷል።”

የመኢሶንና የኢሕአፓን እንደምሳሌ ተነሳ እንጂ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብሮ የመሥራት እንዲሁም የመቀናጀት ያልተሳኩ ፍሬ አልባ በርካታ ሙከራዎች መጥቀስ ይቻላል። ዋና ዋናዎቹ ኅብረት፣ ኢዴፓ-መድሕን፣ ቅንጅት፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ወዘተ. ተጠቃሽ ሲሆኑ አሁንም የተለያዩ በብሔርም ሆነ ኅብረ ብሔራዊ በሆኑ ድርጅቶች መካክል ያልተቋጩ ሙከራዎች እንዳሉ ይታወቃል።

የፓርቲዎች ብዛትና አብሮ መሥራት አለመቻል
አዲስ ማለዳ በቅርቡ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ጋር ባካሔደችው ቃለ ምልልስ “እስካሁን በነበረው ሕግ መሠረት በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ የአካባቢ ፓርቲዎች የሚባሉት 60 አካባቢ ሲሆኑ፥ ኻያዎቹ ደግሞ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ተደራጅተዋል። ሌሎቹ ደግሞ ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበው ገና በሒደት ላይ የሚገኙ ናቸው። ለቦርዱ ጥያቄ ያላቀረቡም ፓርቲዎች አሉ። የምዝገባ ሒደት ላይ ያሉትን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ ዘጠና የሚጠጉ ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ” ማለታቸው ይታወሳል።

በርግጥ አዲስ ማለዳ ከኹለት ሳምንታት በፊት በሠራችው ዜና፥ ምርጫ ቦርድ ለአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ለምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ምክክር)፣ ለቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቅዴፓ) እና ለጋምቤላ ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ጋሕነን) – ለመጀመሪያ ኹለቱ የአገር ዐቀፍ እንዲሁም ለተቀሩት ኹለቱ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ሕጋዊነት ማረጋጋጫ ምስክር ወረቀት መስጠቱን ዘግባለች።

ሙሼ ሰሙ የቀድሞ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ከፍተኛ አመራር የነበሩ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ከቀጥተኛ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ ራሳቸውን አግልለዋል፤ ነገር ግን ወቅታዊውን የኢትዮጵያን ማኅበረ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች በሰፊው በመተንትን ይታወቃሉ። ሙሼ ከ90 በላይ የተቃዋሚዎች ፓርቲዎች አሉ የሚባውን በተመለከተ ተጋኗል ይላሉ። “ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት ከሔድን ይሔ [ከ90 በላይ ፓርቲዎች አሉ የሚባለው] የተሳሳተ መልዕክት ያስተላልፋል። በተጨማሪም ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም እንደማጥቂያና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተዓማኒነት ለማሳጣት ኢሕአዴግ ሊጠቀምበት ይችላል” በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ፖለቲከኞችም ሆኑ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ምሁራን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቁጥር መጋነኑን እንዲሁም ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠውን መሥፈርቶችን ያሟሉ ይሆን የሚለው ላይ ጥርጣሬ አላቸው። ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ‘ተቃውሞ’ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎችም የኢሕአዴግ የእጅ ሥራ ውጤቶች መሆናቸውንም ይናገራሉ።

ሙሼ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አደረጃጀት በተመለከተ በግላዊ ትውውቅ፣ በጓደኝነት በአካባቢ ስለሚደራጁ የቀበሌነት መንፈስ የተፀናወታቸው ናቸው ያሉ ሲሆን፥ አንዳንዶቹን ደግሞ ለመደራጀት ያበቃቸው ቁጭት፣ የአርበኝነት መንፈስ፣ የኢትዮጵያ የመገነጣጠል ስጋት ወዘተ. እንጂ ርዕዮተ ዓለም አይደለም ይላሉ።
የአርበኞች ግንቦት 7 የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ኤፍሬም ማዴቦ በበኩላቸው የፓርቲዎቹ ችግር የሚመነጨው ከአመሠራረታቸው ጀምሮ በጥቂት ልኂቃን የሚዋቀሩ በመሆናቸው የልኂቃኑ የስብዕና ችግርም አብሮ የሚነሳ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አዳነ ዓለማየሁ ሙሼና ኤፍሬም ባነሱት ሐሳብ ይሥማማሉ። አዳነ ‘ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የግለሰብ ፓርቲዎች ናቸው፤ ከግለሰብ ከፍ ካሉም የጥቂት ቡድኖች ናቸው’ በማለት በምሣሌ ያስረዳሉ፣ “የግለሰብ ልዩነቶች ብዙ ጊዜ የፓርቲዎች ልዩነቶች ሲሆኑ መመልከት የተለመደ ነው።” በዚህ የተነሳ አንዳንድ ጥናቶችም እንደሚያሳዩት የእንደዚህ ዓይነቶቹ ፓርቲ አመራሮችም ከሀብት፣ ከሥልጣንና ክብር የዘለለ ምክንያት ‘ራሽናል’ እንደሌላቸው አዳነ ጠቅሰዋል። ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነት ፓርቲዎች ውሕደት ‘ግላዊ’ ጥቅማቸው ስለሚያስቀርባቸው የማይታሰብ ነገር ነው።

አረጋሽ አዳነ የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (ዓረና) የሥራ አስፈፃሚ አባል ሲሆኑ፥ የቀድሞው ከፍተኛ የሕወሓት አመራር የነበሩና ረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተሳተፉ ሴት ናቸው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የማርክሲዝም ርዕዮት ዓለም ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፍን በመጥቀስ ብዙዎቹ ፓርቲዎች ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ማርክሲስት አስተሳሰብ ዝንባሌ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ። ይሁንና “በርግጥ የማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም በትክክል ተረድተነዋል ወይ?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

ለአረጋሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል አብሮ የመሥራት፣ ተቻችሎ መሔድ፣ የአቃፊነት አሠራሮችና አስተሳሰቦች አለመኖር ጎድቶናል ሲሉ በቁጭት ድምፀት ተናግረዋል። “የተካረረ ፖለቲካ ነው የምናካሒደው፤ የማጥፋትና የመጥፋት ዜሮ ‘ሰም ጌም’ የሚባለው ዓይነት” በማለት ገልጸዋል። ኤፍሬም መጠፋፋት የግራ ፖለቲካ ያወረሰን ትልቁ መጥፎ ልምድ ነው በማለት የአረጋሽን ሐሳብ ያጠናክሩታል። መረራ በበኩላቸው ‘Party Politics, Political Polarization and the Future of Ethiopian Democracy’ ብለው በሰየሙት የጥናት ሥራቸው እንዳመለከቱት፥ የፖለቲካ ፓርቲ ባሕል የኢትዮጵያን ፖለቲካን ከተዋወቀው ጊዜ ጀምሮ ማለትም ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ያለው የፓለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ የሴራና የጠልፎ መጣል የውድቀት ታሪክ ነው ይሉታል።

በተጨማሪም አረጋሽ የፖለቲካ ባሕላችን አለመዳበር፣ ለሕዝብ የፓርቲዎችን መርሐ ግብር አቅርቦ የመዳኘት ልምድ አለመኖር እና ዴሞክራሲን ለይስሙላ መጠቀማችን በፖለቲካችን ውስጥ መደማመጥ፣ አብሮ መሥራት ብሎም መዋሐድ እንዳይኖር እንቅፋት ናቸው ብለዋል።

“በመሆኑም፣” ይላሉ ሙሼ፥ መጠየቅ ያለበት “የተቃዋሚ ፓርቲ የምንላቸው በርዕዮተ ዓለም ደረጃ የጠራ አስተሳሰብ አላቸው ወይ? ዓላማቸው በደንብ በጽሑፍ ተቀርጿል ወይ? የሚወክሉት ኅብረተሰብ ይታወቃል? አባላቶችስ በአስተሳሰብ ዙሪያ ነው ወይ የሚመለመሉት?” ሲሉ ይሞግታሉ። ይህንን የሚያሟሉ ፓርቲዎች ስለመኖራቸው ሙሼ ይጠራጠራሉ ቢኖሩም በጣም ጥቂት ናቸው ሲሉ ራሳቸው ላነሱት ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

በተለይ ብዙዎቹ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ብሔርን መሠረት አድርገው የተደደራጁ በመሆናቸው ፓርቲዎች ለየግል ብሔራቸው የቆሙ ስለነበሩ አንድ የሚያደርጋቸውን አጀንዳ ቀርፀው እንዳይንቀሳቀሱ እንቅፋት ሆኗል ሲሉ ሙሼ ገልጸዋል። አዳነ በበኩላቸው በአጠቃላይ ከፖለቲካ ባሕል አኳያም ሲታይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳ ቀርፆ በጋራ ከመስራት ይልቅ ሁሉም በየጥጉ ወደ አላስፈላጊ ፉክክር (‘ሰፖርት ኮምፒቲሽን’) በማድረጋችን የፖለቲካ ባሕል እንዳናሳድግ አድርጎናል ብለዋል።

መፍትሔ
ሙሼ “ጥርት ያለ ርዕዮት ዓለም፣ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ መዳበር፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የአባላት ምልምላ እና በመርሕ መመራት ትኩረት የሚያሻቸው የቤት ሥራ መሆናቸውን በጠቆም እነዚህም ጠንክረው ከተተገበሩ ተቃዋሚውን ኃይል አንድ ደረጃ ከፍ ያደርጉታል ብዬ አምናለሁ” በማለት የመፍትሔ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።
ኤፍሬም በበኩላቸው “አሁን ያለውን ገዢ ፓርቲ ለመገዳደር ትልቅ ሆኖ መገኘት እንደሚያስፈልግ፥ ጎን ለጎንም ለሕዝብ አማራጭ ፓርቲ ሆኖ መቅረብ እንደሚያስፈልግ” አሥምረውበታል።

አዳነ “ለኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጓት ቢበዛ ሰባት የሚያህሉ ፓርቲዎች ናቸው” ይላሉ። “ይህ የሚሆነው ግን ብዙ መፈታት የሚገባቸውን ጥያቄዎች መልስ መስጠት ሲቻል” እንደሆነ አሳስበዋል። ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመተባበር ለምርጫ የማያስቸግሩ ቁጥር ያላቸው አማራጮች መሆን የሚችሉት በአጠቃላይ ውይይት ውስጥ ገብተው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አገራዊ ጉዳዮች በማስቀደም መፍትሔ ሲሰጡ መሆኑን አዳነ ያሠምሩበታል።

ሌላው በኹለተኛ ደረጃ መፍትሔ ብለው አዳነ ያስቀመጡት ወደ ዜግነት ፖለቲካ መምጣት እንደሚገባ ሲሆን፥ ‘ይህም ሲሆን ነው የርዕዮተ ዓለም ፖለቲካ ይኖረናል’ ይላሉ። የዜግነት ጉዳይን ለማምጣት በብሔር ፖለቲካ ላይ ውይይትና ድርድር ማድረግ እንደሚያስፈልግ እና በዚህ የሽግግር ወቅት ከብሔር ጋር ተያይዘው የሚነሱበትን ጥያቄዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ምላሽ እንደሚያገኙ ማድረግ እንደሚሻል ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል። የተቻኮለ መሰባሰብም አደጋ በማመልከት ሥራዎቹ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው አዳነ አሳስበዋል።

መውጫ
አረጋሽ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን እንዲወጡ፣ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመሔድ፣ የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ለመሆን እንዲሁም ጠንካራ ሆኖ ለመውጣት ተስፋም ስጋትም ይታያቸዋል። ኤፍሬም በበኩላቸው የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ ቀላል አይደለም፤ ሒደቱ ረጅም ጊዜ ይፈጃል ብለዋል። ሙሼ በተቃራኒው ተስፋ ብዙ እንደማይታያቸው በመግለጽ፥ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የተለመደው የለብ ለብ ሥራ መቀጠሉን በምክንያትነት አቅርበዋል።

የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አዳነ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዋር የሚዘውሩት የ1960ዎቹ ትውልድ ልኂቃን በመካከላቸው ዕርቅ ካላወረዱ አሊያም ከፖለቲካው ጠቅልለው ካልወጡ ችግሩ አይፈታም የሚል ጠንከር ያለ አስተያየት ሰንዝረዋል፤ “እኔ እንደማስበው ይሔ አንድ ትውልድ የብዙ ትውልዶችን ዕድሜና ዕድል ዘግቷል። [አሁን] ወጣቱ አገር መረከብ አለበት” በማለት።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here