የፍርድ ቤቶች በጀት በተወካዮች ምክር ቤት ሊፀድቅ ነው

0
556

የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የቀጣዩን ዓመት የበጀት ጥያቄያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጥታ አቅርበው ለማፀደቅ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ታወቀ። ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዳስታወቀው በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 79 ቁጥር 6 ላይ በግልፅ እንደተደነገገው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራሉን መንግሥት የዳኝነት አካል የሚያስተዳድርበትን በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ እንደሚያስወስንና በፀደቀም ጊዜ በጀቱን እንደሚያስተዳድር ባለሙሉ ሥልጣን መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀና ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ከተቋቋሙ ጀምሮ አሠራሩ በተቃራኒው ፍርድ ቤቶች ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች ባልተለየ መልኩ በጀታቸውን ከገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ያገኙ እንደነበር ይታወቃል። ይህ አካሔድ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር እንደሆነ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጨምሮ ገልጿል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕዝብ ግንኙነት ባልደረባ ሰለሞን እጅጉ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ እስካሁን ይሠራበት የነበረው አካሔድ ነፃ እና ገለልተኛ መሆን የሚገባቸውን ፍርድ ቤቶችን ነፃነት የነፈገ እና በበጀት ምክንያት ብዙ ማነቆዎች እንዲገጥማቸው የሚያደርግ እንደነበር ተናግረዋል። ሰለሞን “የሥራ አስፈፃሚ አካል በሆነው የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር እየቀረበ ይፀድቅ የነበረው በጀት ተቋማቱን በአንድ አካል ሥር እንዲሆኑ አድርጎ ቆይቷል፣ ተቋማዊ ነፃነታቸውን አጥተዋል” ብለዋል፤ በዚህም ሰለሞን ሥራ አስፈፃሚውን አካል ‘ስግብግብ ነው’ ሲሉ ኮንነዋል። ለዚህም ማብራሪያ ሲሰጡ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ሕግ ተርጓሚው አካል ከመንግሥት በጀት 3 በመቶ የሚሆነውን እንዲወስድ የሚደረግ አሠራር ቢኖርም በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ዜሮ ነጥብ 09 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ለፍርድ ቤቶች እንደሚደርስ አስታውቀዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጀት ዓመቱ ከመንግሥት 94 ሚሊዮን ብር ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደተበጀተ ተጠቁሞ፤ ይህም በቂ እንዳልሆነ ለመረዳት ተችሏል።
በበጀት እቅድና ትስስር ላይ የሚያተኩር ሥልጠና ለፍርድ ቤቱ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተሰጠ ሲሆን፤ በዚህም ወቅት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት ሰለሞን አረዳ በተቋማቱ ውስጥ የተጀመሩትን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ከበጀት ተፅእኖ መላቀቅ እንዳለባቸው ጠቁመው እስካሁን የነበረውንም አሠራር ‘ፈር የለቀቀ’ ሲሉ ተችተዋል።

ከዚህም በመነሳት ይህን ፈር የለቀቀ አሠራር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላትና አመራር ጋር በመሆን ፍርድ ቤቱ እየሠራ እንደሆነ ምክትል ፕሬዘዳንቱ ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here