ዴሞክራሲ በመሠረቱ የተለያዩ ርዕዮቶችን የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ድርጅቶችን በአንድ ማዕቀፍ ማኖር የሚያስችል ያጨዋወት ሕግ ነው። በዴሞክራሲ ስርዓት የፓርቲዎች ቁጥር የሚገደብበት አሠራር የለም። በተለይ ባልዳበሩ ፖለቲካዎች ውስጥ ምንም እንኳን የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ባይኖራቸው፣ የተለያየ ፓርቲዎችን መመሥረት፣ የተመሠረቱትን በመሰንጠቅ ወደ ብዙ መቀየር የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ዴሞክራሲዎች በጎለበቱ ቁጥር የፓርቲዎች ቁጥር ባይቀንስም፥ የተፅዕኖ ፓርቲዎቹ ቁጥር ግን እየቀነሰ “የኹለት ፓርቲ” ወይም “የሦስት ፓርቲ” ስርዓቶች ይዘረጋሉ። እንደምሳሌ የሚከተሉትን ሦስት አገራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር እና የተፅዕኖ ፈጣሪዎቹን ፓርቲዎች ቁጥር እንጥቀስ፦
የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት
በአሜሪካ፡ 40
በእንግሊዝ፡ 76+
በጀርመን፡ 47
በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ መቀመጫ ያላቸው ግን 2 ፓርቲዎች እና በስቴት ደረጃ ውክልና ያላቸው 6 ፓርቲዎች ብቻ ናቸው። በዩናይትድ ኪንግደም 18 ፓርቲዎች ፓርላማ ውስጥ መቀመጫ ያላቸው ሲሆን፥ ኹለቱ ፓርቲዎች ብቻ 82 በመቶ መቀመጫዎችን ‘ሀውስ ኦቭ ኮመንስ’ የሚባለው ምክር ቤት ውስጥ ወስደዋል። በጀርመን 8 ፓርቲዎች የቡንደስታግ (የፌዴራሉ ምክር ቤት) መቀመጫ ቢኖራቸውም፥ ከነሱ መካከል ኹለቱ ብቻ 50 በመቶ መቀመጫዎችን ወስደዋል።
ብዙዎቹ ዴሞክራሲዎች ኹለት ፓርቲዎች ብቻ የገነኑባቸው (“የኹለት ፓርቲ ስርዓት” – ‘ቱ ፓርቲ ሲስተም’) መሆኑ ዴሞክራሲዎች በሙሉ ባለ ኹለት ፓርቲ ናቸው ወይም መሆን አለባቸው የሚለውን ባያመለክትም፥ የብዙ ፓርቲዎች መኖር ግን ለዴሞክራሲ ሥጋት እንደማይሆንና በሕዝብ ምርጫ እየተንጓለሉ ኹለት ወይም ሦስት ዋነኛ ተቀናቃኞች ብቻ የመቅረት ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን ያመለክታል።
ይሁን እንጂ የኹለት ፓርቲ ስርዓቶችም ሌሎችን ባለማስጠጋት እና የራሳቸውን ‘ኢምፓየር’ በመመሥረት ይወቀሳሉ። በብዙዎቹ የኹለት ፓርቲ ስርዓቶች ውስጥ ሌሎች ፓርቲዎች ወደ ማዕከላዊው የፖለቲካ ጫወታ ለመግባት ብዙ መሰናክሎች ስለሚገጥሟቸው ሒደቱ ፈታኝ ይሆንባቸዋል።
በኢትዮጵያ ሕጋዊ መሥፈርቶችን የሚያሟሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥቂት ቢሆኑም፥ ጠቅላላ ቁጥራቸው ከ80 በላይ ነው። በዚያ ላይ ዴሞክራሲው የይስሙላ በመሆኑ የፌዴራሉም ይሁን የክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች በሙሉ በአንድ ፓርቲ ተጠቅልለዋል። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያበበ ከመጣ ፓርቲዎች በርዕዮተ ዓለም እየተዋሐዱ ወይም ደግሞ ጠንካራና ሕዝባዊ ድጋፍ ያላቸው ፓርቲዎች ብቻ እየተንጓለሉ በመውጣት ጥቂት ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ብቻ ጎልተው መውጣታቸው አይቀሬ ነው። ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር ለተወሰኑ ዐሥርታት መገንባት እስከሚቻል ድረስ ግን ምንም አቅም የሌላቸው በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችን ማየት አይቀሬ ይመስላል።
ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011