በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽንና በሳፋሪኮም በኩል ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በውይይቱም ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ እንዲሁም ስለተገነቡ መሰረተ ልማቶች ዝርዝር መረጃ ለሳፋሪኮም ሰጥቷል ነው የተባለው።
ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ምቹ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን፣ የቴሌኮም፣ የውሃ እንዲሁም የመብራት መሰረተ ልማቶች መዘርጋታቸውን በማስታወስ ሳፋሪኮም ፓርኮቹን እንዲጎበኝ ጥሪ ቀርቦለታልም ተብሏል።
ሳፋሪኮም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብቶ መስራቱ፣ ፓርኮች አስካሁን በብዛት ሲሰሩበት ከነበረው የቴክስታይል ዘርፍ የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግና የቢዝነስ ዘርፎችን ለማካተት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ውጤታማ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል። ኮርፖሬሽኑም ከሳፋሪኮም ጋር በተለያዩ ዘርፎች አብሮ ለመስራት ያለውን ፍላጎት በግልጽ አስቀምጧል ነው የተባለው።
ሳፋሪኮም በበኩሉ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በተለይም በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ዳታ ሴንተር የመገንባትና፣ በሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሌሎች ፕሮጀክቶችን የመተግበር ፍላጎት እንዳለው ማሳወቁ ተገልጿል።
ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ብሎም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለው የስራ እንቅስቃሴ ጅማሮ መሆኑን ገልጾ፣ እጅግ ትልልቅ የተቋሙ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ወደፊት ተግባራዊ ይደረጋሉ፤ ለዚህም ሳፋሪኮም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ነው ሲል ገልጿል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ዳታ ሴንተሮችን የመገንባት፣ ኮሚዩኒኬሽን ታወሮችን የመትከል፣ እንዲሁም የቢሮ ኪራይና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ስራዎችን ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014


