የወርቅ የወጪ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል

Views: 387

ኢትዮጵያ ከወርቅ የምታገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆሉ የቀጠለ ሲሆን፣ ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ ወርቅ 17 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ገቢ ተገኝቷል። ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በኹለት ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ነው።
ከተላከው ወርቅ ውስጥ 1282 ኪሎግራም የሚሆነው ድርጅቶች የላኩት ሲሆን፣ 1931 ኪሎግራም የሚሆነው ወርቅ የተላከው በባህላዊ አምራቾች ነው። በጥቅሉ 3213 ኪሎግራም ወርቅ በያዝነው በጀት ዓመት መጀመሪያ ግማሽ ዓመት ውስጥ የተላከ ሲሆን፣ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ154 ኪሎግራም ያነሰ ነው።

የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት መቀነሱ እንደ ዋነኛ ምክንያት የተጠቀሰ ሲሆን፣ ዋነኛ አምራች የነበረው ሚድሮክ ወደ ሥራ መግባት አለመቻሉ የተገኘው ገቢ እንዳይሻሻል ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል። ከ2009 በፊት ከወርቅ በአማካይ ቢያንስ ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይገኝ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ በያዝነው በጀት ዓመት ከዚህ ቀደም ይገኝ የነበረው ሩብ እንኳን ማሳካት እንደማይቻል መረጃዎች አመላክተዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ወርቅ ከአጠቃላይ የውጪ ንግድ ገቢ ያለው ድርሻ ከ10 በመቶ ወደ አንድ በመቶ ወርዷል። ይህም የአገሪቷ የወጪ ንግድ ገቢ መሻሻል እንዳያሳይ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማዕድን ግኝት ሥራዎች ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክትር በትሩ ኃይሌ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የወርቅ ማውጣት ሥራውን ያቆመው ሜድሮክ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ቢታቀድም፣ በተለያዩ ምክንያቶች እስከ አሁን ሥራ አለመጀመሩ አገሪቷ የመታገኘው የወርቅ ገቢ እንዲቀንስ አንደኛው ምክንያት ነው።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የሚመረተው የወርቅ ምርት በባህላዊ መንገድ ተመርቶ በሕገወጥ መንገድ ከአገር መውጣቱ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በ2011 በጀት ዓመት 35 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ወርቅ ከአገር ሊወጣ ሲል መያዙን አስታውሰዋል። በያዝነው 2012 በጀት ዓመትም በተደረገ የድንበሮች ቁጥጥር 14 ኪሎ ግራም ወርቅ በቶጎ ጫሌ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሲወጣ መያዙንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው ወርቅ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘውን የሚልከው በኢፈርት ከሚተዳደሩት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ኢዛና የተባለው የማዕድን አምራች ድርጅት ሲሆን፣ በያዝነው በጀት ዓመት ብቻ ከ200 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ወደ ወጪ ልኳል።

ከዛሬ ኹለት ዓመት በፊት የተዘጋው ሚድሮክ ጎልድ በዓመት ከአራት ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ይልክ የነበረ ሲሆን በቅርቡ የትግበራ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ዳግም ወደ ሥራ ሊገባ እንደሆነ ድርጅቱ ማሳወቁ ይታወሳል።

በቅርቡ በመንግሥት ይፋ በሆነው የአገር በቀል የኢኮኖሚ አጀንዳ ላይ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ወርቅን ጨምሮ የማዕድን ዘርፍ ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ3 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ታቅዷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com