በእቃ ማጓጓዣ (ካርጎ) ውስጥ ዕቃ ጫኝና አውራጅ ሠራተኛ ተደብቆ ወደ ቤልጂየም እንዲወጣ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ 3 የአቪዬሽን የደህንነት ሠራተኞች ዋስትና ተፈቀደላቸው

0
1132

ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእቃ ማጓጓዣ (ካርጎ) ውስጥ አንድ ዕቃ ጫኝና አውራጅ ሠራተኛ ተደብቆ ወደ ቤልጂየም ሌዢ ከተማ እንዲወጣ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ 3 የአቪዬሽን የደህንነት ሠራተኞች ዋስትና ተፈቀደላቸው።

በአየር መንገዱ እቃ ጫኝና አውራጅ ሆኖ ሲሰራ የነበረ ሀብቴ አበበ የተባለ ግለሰብ፤ በየካቲት 7 ቀን 2014 የአየር መንገዱ ንብረት በሆነ አውሮፕላን ላይ ዕቃ ሲጭን ከቆየ በኋላ፤ የአበባ ምርት ጋር በካርጎ ውስጥ ተደብቆ ወደ ቤልጂየም ሌዢ ከተማ መውጣቱን ተከትሎ፣ በዕለቱ በቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም በአውሮፕላን ፍተሻ ሥራ ላይ የነበሩ 9 የአየር መንገዱ ሰራተኞች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ሲከናወን ቆይቷል።

ከእነዚህም 9 ተጠርጣሪዎች መካከል 6ቱ የአቪዬሽን ሠራተኞች ከወንጀሉ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው ማስረጃ ያልተገኘ በመሆኑ በዓቃቢ ህግ ውሳኔ ቀደም ሲል ከእስር ተፈተዋል።

ቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች ማለትም በአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ ወደ ውስጥ የሚገቡ ሠራተኞችን የመግቢያ መታወቂያ ተቀብሎ፣ መዝግቦ፣ መግባትና መውጣታቸውን የሚረጋግጥ እና ክትትል የሚያደርግ ሠራተኛ መሆኑ የተገለፀው አንድነት ደስታ፣ በአውሮፕላን የፍተሻ ባለሙያ ናት የተባለችው ትግስት ሙሉ እንዲሁም በአውሮፕላን ፍተሻና የሥራ እቅስቃሴ በመምራት ተመድቦ ነበር የተባለው ኤፍሬም ብርሀኑ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሔደባቸው ይገኛል።

እነዚህ ሠራተኞች በዕለቱ ቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም ፍተሻ እና ሪፖርት ባለማድረግ የሙያ ግዴታቸውን በየደረጃው በአግባቡ ባለመወጣት ወንጀል ተጠርጥረው ነው ምርመራ እየተካሔደባቸው የሚገኘው።

በትላንትናው ዕለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ተጠርጣሪዎቹን ያቀረበው የፌደራል ፖሊስ መርማሪዎች ግለሰቡ በአበባ ምርት ውስጥ ሆኖ ወደ ቤልጂየም እንዲጠፋ የተደረገ መሆኑን ዝርዝር ማስረጃዎች ማሰባሰባቸውን ገልጸው፤ ምርመራውን ከፖሊስ ጋር እያከናወነ ያለው ዓቃቢ ህግ ተጨማሪ ማስረጃዎችን እንዲያሰባስቡ እንዳዘዛቸው ለፍርድ ቤቱ አብራርተዋል።

ማስረጃውን ለማሰባሰብ ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ እንዲሰጣቸውም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የተጠርጣሪዎች ጠበቃ በበኩሉ ዛሬ መዝገቡ የተቀጠረው በመንግስት ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ ተጣርቶ እንዲቀርብ እና ወደ ቤልጅየም ሄዷል ስለተባለው የዕቃ ጫኝ እና አውራጅ ሠራተኛ ማስረጃ ውጤት ለመጠባበቅ መሆኑን ገልጿል።

ይህም ባልቀረበበት ሁኔታ ተጠርጣሪዎችን በእስር አቆይቶ ምርመራ የሚከናወንበት ሂደት አይኖርም ያለ ሲሆን፤ የዋስትና መብታቸው በሥነ ሥርዓት ህግ አንቀጽ 63 እና 67 መሰረት ሊነፈግ እንደማይገባ ጠቅሶ መከራከሪያ ነጥብ አንስቷል።

በተጨማሪም ጠበቃው ተጠርጣሪዎቹ አንድ ወር በእስር ላይ መቆየታቸውን ጠቅሶ፤ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው መታሰራቸው በሥራቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ይህን ታሳቢ አድርጎ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ጠይቋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ምርመራው አለመጠናቀቁን ተከትሎ፤ ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ማስረጃ ሊጠፋ ይችላል ሲል የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል።

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች እያንዳንዳቸው የ10 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ መፍቀዱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ ከአገር እንዳይወጡ እግድ እንዲጣል ትዛዝ ሰጥቷል።

የፌደራል ፖሊስ መርመሪ በበኩሉ በዋስትናው ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጾ ዋስትናው ይታገድልኝ ያለ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ስለመጠየቁ ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ አዟል።
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here