የኃይል ሥርቆት ሲፈፅሙ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

0
678

ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሽሮሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር በተደራጀ አንድ ማዕከል ውስጥ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርቆት ሲፈፅሙ የተገኙ 11 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን በአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኢነርጂ ማኔጅመንት ሥራ አስኪያጅ አስናቀው ፀሐይ ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት መጋቢት 2 ቀን 2014 የአገልግሎቱ ኢነርጂ ማኔጅመንት ቢሮ የኢንስፔክሽን ባለሙያዎች በአካባቢው ከሚገኙ የፖሊስ አካላት ጋር በመተባባር ባደረጉት ድንገተኛ የፍተሻ ከተፈቀደላቸው የኃይል መጠን ውጪ ሲጠቀሙ መገኘታቸው ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

የኃይል ሥርቆቱን የፈፀሙት እነዚህ ተጠርጣሪዎች፤ በአካባቢው በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር ተደራጅተው እንጀራ በመጋገር ስራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውንም ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

በተደረገው የማጣራት ሥራም 1 ሚሊዮን 65 ሺህ 889 ነጥብ 27 ኪ.ዋ.ሰ ኃይል መሰረቁንና በገንዘብ ሲተመን 2 ሚሊዮን 263 ሺህ 948 ብር ከ80 ሣንቲም የሚደረስ ሥርቆት መፈፀሙን አስናቀው አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕግ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ታሪኩ ማዕረጉ በበኩላቸው፤ ከተፈቀደለት የኃይል አጠቃቀም ውጭ ሲጠቀም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በአገሪቱ የኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 መሰረት በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡

አዋጁን ተላልፎ የኃይል ሥርቆት ተግባር ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም አካል በሕግ ከመጠየቁም በተጨማሪ ይጠቀምበት የነበረው አገልግሎት እንደሚቋረጥና ያላግባብ ለተጠቀመው የፍጆታ ሂሳብ በታሪፉ መሰረት ተሰልቶ ከዳግም ማስቀጠያ ክፍያ እና ከተጨማሪ ቅጣት ጋር እንዲከፈል ይደረጋል ብለዋል፡፡

በኢነርጂ አዋጁ ከአንቀፅ 28 እስከ 30 ድረስ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድርጊቶችን በዝርዝር የተቀመጡ መሆኑን ያነሱት ታሪኩ፤ በተለይ የኃይል ሥርቆት መፈፀም በአገሪቱ የፍትሃ-ብሔር እና የወንጀል ህግ መሰረት ተጠያቂነት የሚያስከትል ከመሆኑም ባሻገር ለትራንስፎረመር መቃጠል፣ ለሃይል መቆራረጥና ለከፍተኛ የኤሌክትሪክ አደጋ መንስኤ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ስለሆነም ህብረተሰቡ መሰል ድርጊቶችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ አካልና በአካባቢው ለሚገኝ የተቋሙ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በአካል በመቅረብ ጥቆማ ሊሰጥ ወይም በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል በመደወል ሊያሳወቅ ይገባል ብለዋል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4na

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here