አርብ መጋቢት 9 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ጉባኤውን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ለብሔራዊ መግባባት አደናቃፊ የሆኑ በርካታ ተንከባላይ አገራዊ ውስብስብ ችግሮችን ሁሉን አካታች በሆነ መንገድ ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ፣ የዜጎች ወንድማማችነትን የሚያጎለብትና የጋራ አገራዊ ራዕይ የሚሰንቅ፣ ፖለቲካዊ አለመግባባቶችንና ግጭትን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል እንዲሁም የአገሪቱን አንድነት የሚያስጠብቅ ውጤታማ ብሔራዊ ውይይት ለማድረግ ሕዝቡ የበኩሉን እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በየጊዜው እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ቢኖሩም ካለው ውስብስብ ችግር አንፃር ገና መቀረፍ ያለባቸው ቀሪ የቤት ሥራዎች ይኖሩናል ያሉት አፈ ጉባኤዋ ለዚህም መንግሥት፣ አምራች፣ አከፋፋይ ነጋዴዎችና ሸማቹ ኅብረተሰብ ተቀናጅቶ መስራትን ይጠይቃል ማለታቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ የክልሉ መንግስት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።
በተጨማሪም በጉባኤው በልዩ ልዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ በመምከር ማጽደቅ እንዲሁም ሹመት እና ረቂቅ ቃለ ጉባኤ ላይ በመምከር የምክር ቤቱ አባላት ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




