አርብ መጋቢት 9 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) መንግስት ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል የማዛወር ሂደት እንዲራዘም መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት ባካሄደው የአገር ውስጥ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር የሚያስችል ማዕቀፎችን ማውጣቱ የሚታወስ ነው።
ይህም የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና ለማስፋት፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት ለማሻሻል፣ ተወዳዳሪነታቸውን ለማጎልበት፣ የካፒታል ተደራሽነታቸውን ለማሳደግ እና የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ተገልጿል።
በዚህ ፕሮግራም መሰረት የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ በመሸጥ ከፊል ወደ ግል ለማዛወር ሀሳብ አቅርቧል።
ባሳለፍነው ዓመት መስከረም ወር ላይም የኢትዮጵያ መንግስት በኦፕሬሽን፣ በመሰረተ ልማት አስተዳደር እና በቀጣይ ትውልድ የተሻሉ ተሞክሮዎችን በማምጣት ለኩባንያው እሴት ሊጨምሩ የሚችሉ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮችን ለመጋበዝ የፕሮፖዛል ጥያቄ አቅርቧል። በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ ተጫራቾች ጋር ውይይት ማድረጉ ይታወሳል።
ቢሆንም ግን የገንዘብ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገር ደረጃ እየታዩ ያሉትን ፈጣን የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋሙን በከፊል ወደ ግል የማዛወር ሂደቱን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ መወሰኑን አስታውቋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA



