በፖለቲካ አውሬ የተበላችው ድሬዳዋ

0
860

በኢትዮጵያ ፖለቲካ በከፍተኛ ሁኔታ እየተተቸ ያለው የኮታ አስተዳደር በብዝኃነቷ የምትታወቀውን ድሬዳዋ ከተማንም እየፈተነ እንደሆነ ይነገራል። በድሬዳዋ የኦሮሞ እና ሶማሌ ብሔር ተወላጆች የከተማዋን መስተዳድር አርባ፣ አርባ በመቶ ድርሻ ሲወስዱ ሌሎቹ በሙሉ 20 በመቶውን ይከፋፈሉታል። ከዚህም በላይ የይገባኛል ጥያቄ ውጥረት ውስጥ የምትገኘው ድሬዳዋ ትኩረት ያሻታል በማለት የጻፉት ሙሉጌታ ገዛኸኝ ናቸው።

 

ድሬዳዋ ከአመሠራረቷ ጀምሮ ነዋሪዎቿን በአንዳች ፍቅር ያቆራኘች ‘ኮስሞፖሊታን’ ውብ ከተማ መሆኗን የውጭ ዜጎች ጭምር ይመሰክሩላታል። የምድር ባቡር ፀጋ የሆነችው ድሬ ለኢትዮጵውያን ከተሞች ሁለንተናዊ ዘይቤ ሆና ዘመናትን ተሻግራ የራሷን አሻራ አሳርፋለች። ወደ ድሬዳዋ ለሥራ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርካቶች መጉረፋቸው አሁን ያለውን የሥነ ሕዝብ ስብጥር ፈጥሯል። የድሬ ልጆች ልዩ መገለጫቸው ጎሳና ሃይማኖት ሳይሆን ወደ ከተማቸው የመጣ ሁሉ እንግድነት ሳይሰማው ቶሎ መላመዱ ነው።

ያላንዳች ልዩነት አብሮ መብላትና መጫዎት ብሒል በድሬዎች ዘንድ ብርቅ አይደለም። የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ ድሬዳዋ መኖሪያቸው ነበረች። እንዲያውም ‘የፍቅር ፈርጥ’ በሆነችው ድሬዳዋ መወለድ ያለማጋነን መታደል ነው። ድሬዎች የትም ቢሔዱ የትም ከአዕምሮአቸው ለአፍታም የማይፋቁ ሠፈሮች ከዚራ፣ መጋላ፣ ኮኔል፣ ገንደ ቆሬ፣ ደቻቱ፣ መልካ ጀብዱ ወዘተርፈ የትዝታዎቻቸው ፈለግ ናቸው። ስለ ድሬ ልጆች መልካምነት ድምፃዊው ማሕሙድ አሕመድ “የድሬ ልጅ ነች የከዚራ፣ ስለ ውበቷ ስንቱን ላውራ” እያለ እንዳቀነቀነው።

እንደ ድሬ ልጆች አገላለጽ “የምን ጭንቀት ፈታ በል አቦ…” ነውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተማዋ እያጋጠማት ካለው የፖለቲካ አስተዳደራዊ ሳንካ ስጋት እንዴት እፎይ ትበል የሚለው ከሁሉም ወገን ይጠበቃል።

የድሬ ቅርምት
በማኅበራዊ ግንኙነት ልዩ ተምሣሌትነት የምናውቃት ድሬዳዋ ሰው ከየት ይምጣ ከየት አብሮ የመኖር ሥነ ልቦና ጥብቅ ቁርኝት እየደበዘዘ የፖለቲካ አውሬ አስተሳሰብ ሰለባ ከሆነች ኹለት ዐሥርት ዓመታትን አስቆጠረች። በደርግ ዘመን የድሬዳዋ ራስ ገዝ ከአምስቱ የአገሪቱ ራስ ገዝ አካባቢዎች እንድትመደብ የተወሰነው በሱማሌ እና ኦሮሞ መካከል ውስጥ መገኘቷ ሲሆን የኹለቱም ጎሣ ተወላጆች የይገባኛል ጥያቄ ያነሱባታል። የጉርጉራ ጎሳዎች ከኦሮሞ ወደ ሱማሌ ኢሳ ጎሣዎች ዝርያ በመቀላቀል የሁለቱንም ጎሳዎች ባሕልና ቋንቋ ማንነት እንዲሁም ባሕሪያት ይጋራሉ። ከ1983 የሽግግር ዘመን ላይም ጥያቄው እንደ አዲስ እያገረሸ ቀጥሏል።

በ1987 በፀደቀው የፌዴራል ሕገ መንግሥት የድሬዳዋ በቻርተር ከተማነት ተጠሪነቷ ለፌዴራል ብትሆንም በእንጥልጥል የቀረው የይገባኛል ቅርምት ጥያቄ ትኩሳት እስከአሁንም መቋጫ ያልተገኘለት ነው። በ1994 የወጣው የከተማ አስተዳደሩ የሚተዳደርበት ቻርተር የፌደራል አካል መሆኗን እያተተ እንደ ክልል ወይም እንደ ፌደራል ከተማ የሰጣት ዕውቅና የለም። ቀደም ባሉት ዘመናት በምሥራቁ ክፍለ አገር በኢኮኖሚው የኢንዱስትሪ፣ በባቡር ትራንስፖርት ወዘተርፈ ንቁ የነበረችው ከተማ እየቆረቆዘች ለመምጣቷ አሁን በሚታየው የፖለቲካ ትኩሳት በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና መነፈጓ አባብሶታል።

ዘውጌነት የተጠናወተው የወያኔ አገዛዝ የድሬዳዋን ጉዳይ አልኮስኩሶ ተጨማሪ ምስቅልቅል የቤት ሥራ ትቶ ማለፉ ነዋሪዎቿን በእጅጉ እደሚያሳዝናቸው ይገልጻሉ። የዚሁ ኢሕአዴግ ጠባብ የዘር ፖለቲካ ፖሊሲ ዋነኛ እንቅፋትና የብሔር ግጭቶች መዘዝ በመሆኑ ስርዓቱ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ በውጭ አገራት በስደት የሚኖሩ የከተማዋ ተወላጆች ይናገራሉ።

ለድሬዳዋ ዘለቄታዊ መፍትሔ የፌደሬሽን ምክር ቤት ይህ ነው የሚባል የረባ ትኩረት ያለመስጠቱ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል። ይሁን እንጂ ቋንቋና ማንነት ላይ በተመሠረተው የክልል አወቃቀር ተመርኩዞ የይገባኛልና ትጠቃለልልኝ ጥያቄ ለሚያቀርቡት የሶሕዴፓ እና ኦሕዴድ (ኦዴፓ) ፓርቲዎች ውዝግብ አጀንዳ የነዋሪዎቿን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ አምርሮ ያሳስባቸዋል። ተግባራዊ የሆነው ሕግና አዋጅ በሁለቱ ጎሳዎች መካከል መግባባት ላይ እስከሚደረስ በሚል ሁኔታው በይደር እንዲቆይ ሲደረግ በ2004 የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ይባል የነበረው መጠሪያ የድሬዳዋ አስተዳደር ተተክቷል።

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 55 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በተደነገገው መሠረት የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/2004 የነዋሪዎቿን መብት በተመለከተ በመረጡት የመወከል፣ በበጀትና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የመወሰን፣ እኩልነትና ፍትሓዊነት ላይ የተመሠረተ አስተዳደር እንዲሰፍን…. ይላል። በአገሪቱ ኸለተኛዋ ትልቅ ከተማ የነበረችው ድሬዳዋ 341,831 ሕዝብ የሚኖርባት ሲሆን፥ ከቻርተር ከተማነቷ ይልቅ ብሔር ተኮር የሥልጣን ክፍፍል ቀመር መፎካከሪያ አድርጓታል።

በተለይም
ከ2008 ወዲህ የ40፡40፡20 አወቃቀር አንድምታው በመሆኑ የከተማዋን ተወላጆችና ነዋሪዎች ያለመረጋጋት ላይ ጥሏል። ስለሆነም 40 በመቶ ለኦሮሞ፣ 40 በመቶ ለሱማሌ እንዲሁም 20 በመቶ ለሌሎች በሚል የተዘረጋው አሠራር የራሱ ውስብስብ የፀጥታና አለመረጋጋት ተፅዕኖ እንደሚያስከትል የፖለቲካ ተንታኞች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። የፖለቲካ ምኅዳሩ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ከባድ ፈተና መደቀኑም አይቀርም። የከተማዋ ከንቲባ ለአምስት ዓመታት የሥራ ዘመን የሚሾም ሆኖ በፈረቃ በየኹለት ዓመት ተኩል ከኦሮሞ እና ከሱማሌ ተወላጅ እየተፈራረቀ ይወከላል። በኹለቱም ወገን የየራሳቸው አካል እንድትሆን ከፍተኛ ግፊት ማካሔዳቸው ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ያጦዘዋል።

ከተማዋ የቀድሞውን የጋራ አብሮ መኖር ራዕይ ይዛ የመቀጠሏ ሁኔታ በአዲስ ቀመር (ፎርሙላ) አግላይ ጠቅላይ ዕሳቤ ነዋሪው ከሥራ አጥነትና ፍትሐዊ ፖለቲካዊ መብት ተጠቃሚነት ማስፈን አንፃር ጥርጣሬ አለው። የድሬዳዋ መፃዒ ተስፋና ስጋቶች በተለየ ትንተና ሊታዩ የሚችሉ ስለሆነ የተወላጆቹን ፍላጎት በማጤን የምሁራኑንና በሳል ፖለቲከኞች ተሳትፎን ያካተተ ዘላቄታዊ መፍትሔ ማፈላለግ አገራዊ ግዴታ ይሆናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here