‹‹ሁሉንም መቆጣጠር አንችልም››

0
722

ገመቹ ዱቢሶ ለመምራት ወስብስብ ከሆኑ ተቋማት ከሚመደቡት መካከል የሆነውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን ከዘጠኝ ዓመት አንስቶ እየመሩ ይገኛሉ። ተቋሙን እንዲመሩ በፓርላማ ከመመረጣቸው በፊት የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት ገመቹ፦ ወደ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የመጡት በአጨቃጫቂ ሪፖርታቸው የተነሳ ከሥልጣን የተነሱት ለማ አረጋዊን ተክተው ነበረ።

ገመቹ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የወሰዱ ሲሆን የማስተርስ ዲግሪያቸውን በፋይናንስ አስተዳደር ከግላስኮው ካልዶኒያን ዩንቨርሲቲ ማግኘት ችለዋል።

በተደጋጋሚ በፓርላማ በሚያቀርቡት አጨቃጫቂና አስደንጋጭ የኦዲት ሪፖርታቸው የሚታወቁት ገመቹ፤ ሥራቸው ፍሬያማ ይሆን ዘንደ የኦዲት ክፍተት ያለባቸው ተቋማት ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ሲሞግቱ ይታያል። በቢሊየን የሚቆጠሩ ብሮችን ለማዳን የሚያደርጉት ጥረት ግን ፍሬ ሲያፈራ አይታይም፤ በተቃራኒ በየዓመቱ ክፍተት እየጨመረ መጥቶ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ያቀረቡት ሪፖርቶች ያሣያሉ።

በቅርቡ በፕላን እና ልማት ኮሚሽንና በፓርላማ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ያደነቁት ገመቹ፤ አሁንም ተቋማቸው ያለበት ችግሮች አሳሳቢ መሆናቸውን ይገለጻሉ። ለአብነትም የሠራተኛ ፍልሰት መጨመርን ያነሳሉ።

የአዲስ ማለዳው ሳምሶን ብርሃኔ ስለ ኦዲት ክፈተቶችና ስለተወሰዱ እርምጃዎች እንዲሁም አገሪቷ በዚህ አኳያ ያለችበትን ደረጃ ዙሪያ ከገመቹ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ በተለያዩ ጊዜያት የኦዲት ክፍተቶችን ለፓርላማ አቅርበዋል፤ ነገር ግን በዚህ የሚስተካከል ነገር ግን አላየንም፤ ክፍተቶቹ እየጨመሩ እንጂ እየተስተካከሉ አልመጡም። ለዚህ ምክንያቱ ምን ይመስሎታል?
ገመቹ ዱቢሶ፡ ኦዲት ሪፖርት ምንም የተስተካከለ ነገር የለም ማለት አይቻልም። በየአመቱ አዲስ ኦዲት በሚደረግበት ጊዜ አዳዲስ ግኝቶች ይገኛሉ፤ ነባር ግኝቶችም ይቆያሉ። በመሀል ደግሞ የሚስተካከሉ የሚታረሙ ነገሮች ይኖራሉ። የሚስተካከል ነገር ዜሮ ነው ማለት አይቻልም፤ ይሁን እንጂ የኦዲት ግኝቶቹ ላይ አብዛኛዎቹ መሥሪያ ቤቶች እርምጃ ወስደው አልተገኙም። ይህ እንግዲህ የተለያዩ ምክንያቶች አሉት።

የመጀመሪያው ምክንያት ሊሆን የሚችለው እርምጃ አለመወሰዱ ነው። እኔ በማጥፋቴ ከሕግና አሠራር ውጪ በማድረጌ አለተጠየኩም፤ ስለዚህ እንዳስተካክል የሚገፋፋኝ ነገር አይኖርም ማለት ነው። ተጠያቂነት በሚገባ አለመረጋገጡ ምክንያት የመጣ ችግር ነው። ተጠያቂነት ስንል አስተዳደራዊ እርምጃ ወይም ሕጋዊ ሊሆን ይችላል። ፖለቲካዊም እርምጃ ሊሆን ይችላል።

ሕጋዊ ስንል ክፍተት ያለባቸውንና ያጠፉትን የተቋማት አመራሮች በሕግ ተጠያቂ አድርጎ የሕግ እርምጃ ተወስዶባቸው መመለስ ያለበት ገንዘብ እንዲመለስ አልያም ለሠሩት ሥራ እንዲጠየቁ ማድረግ ነው። አስተዳደራዊ ደግሞ ከፍርድ ቤት መልስ መሥሪያ ቤቱ ራሱ ወይም የመሥሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆነው ተቋም የሚወስደው እርምጃ ነው። የፖለቲካ አካላቶችም በተለያዩ ሰዎች ይህን ያህል ዓመት የሚሰጧቸው ወይም የሚሾሟቸው አካላት የሚወስዱባቸው እርምጃዎች ናቸው እንግዲህ ተጠያቂነት መረጋገጥ በዚህ መልኩ ነው የሚረጋገጠው ግን ይህ ሊሆን አልቻለም።

ኹለተኛው ምክንያት ደግሞ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያለው በተለየ በፋይናንስ፣ በንብረት ማስተዳደር፣ በግዢ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች አቅም ውስንነት ነው። ይህ ግን አንድ ምክንያት ይሆናል እንጂ ማሳበቢያ ሊሆን አይችልም። አንዱ ሥራ እየሠራ ሌላው እያጠፋ አቅም ስለሌለኝ ነው የሚል ምክንያት መደርደር አይቻልም። ነገር ግን በትክክል የሚታዩ ሕግና ስርዓትንና አሠራርን ያለመገንዘብ ችግሮች አሉ።

ከዚያ ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት የምታወጧቸው ሪፖርቶች በዘለለ ክፍተቶችን ወደ ሕግ አንዲሔድ ስታደርጉ አትታዩም። ለምሳሌ 2007 ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር እርሶ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወደ ሕግ የመውሰድ ኃላፊነት እንደተጣለባቹ ያትታል፤ ግን ይህን አታደርጉም? ለምን?
ይህንን በፊት አናደርግም ነበር። ለምንድነው ቢባል፤ በረጅም ጊዜ ውስጥ ያልነበረውና ከዛሬ ነገ ይለወጣል ምናልባት የግንዛቤ ክፍተትም ስለነበረ የትኩረትም ጉዳይ ላይ ነበር መሥራት የመረጥነው። ግን ቀደም ሲልም ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሥልጣኑ በነበራቸው ጊዜ አሁን ደግሞ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማስተላለፍ ጀምረናል። ምክንያቱም መንግሥትን ወክለው ክስ መመስረት የሚችሉት እነሱ ስለሆኑ ነው። ነገር ግን ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ብዙዎቹ ነገሮች ቢሄዱም እስካሁን ክስ አልተመሠረተም።

አንደኛው ምክንያት የኦዲት ሪፖርትን በሚገባ አለመገንዘብና ያለቀውን የሒሳብ ሥራ እንደገና እንዲሠራ የሚጠይቁበት ሁኔታ አለ። ይህ ምናልባት ቁጭ ብለን እንፈታለን ብለን ቀጠሮ ይዘን አሁንም ያልፈታነው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አሁን ባለው ነገር ላይ ተመስርቶ ክስ መመስረት ይችላሉ።

ኹለተኛውን ምክንያት ደግሞ ላስረዳ። እኔ እዚህ ቢሮ ውስጥ የነበርኩት ዘጠኝ ጊዜ ሪፖርት ቀርቧል። ከገባሁ ጀምሮ አንዳንድ ጊዜ ገንዘብ ሊጨምር ይችላል እንጂ ተመሳሳይ ነገሮች ናቸው። ምን እናድርግ ብሎ በአቅጣጫ ላይም ትንሽ ያለመወሰን ችግሮች አሉ። ለምን ጠርተን ሁሉንም ከምንከስና ፍርድ ቤት ከምናቀርብ የተወሰኑት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ብንወስድና ትላልቅ ነገሮች ላይ ትኩረት ብናደርግ የሚል ሐሳብም ዐቃቤ ሕግ ቢሮው ነበረው። ግን ይሄንንም ቢሆን እርምጃ ሲወሰድ አይታይም።

የቀድሞ የፍትሕ ሚኒስቴር በነበረ ጊዜ ነው ክፍተቶችን ማስተላለፍ የጀመርነው። ይህ ማለት ዐቃቤ ሕግ ሳይቋቋም በፊት ነው። በኛ በኩል ሊወሰድ የሚገባው ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ጥረቶችን ጀምረናል ያው እኛ በራሳችን አይደለም የምንከሰው። መክሰስ ያለበት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንደመሆኑ መጠን በስፋት እየሠራ ይመስላል። ግን መደምደሚያ ላይ አልደረሰም ምክንያቱም በተጨባጭ ክስ መስርቶ እስካላየሁ ወይም ደግሞ ከክስ መልስ በድርድር የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ እንዲመለስ እስካልተደረገ ድረስ ጅምር ነው ብዬ ማውራት አልችልም።

ስለ ጅምር ዝም ብዬ መውራት አልችልም። እኔ ማየት የምፈልገው ውጤት መጥቶ ማየትን ነው። ይመለስ ያልኩት የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ ተመልሶ ማየት ነው። በድርድርም ሆነ በፍርድ ቤትም ያስመልሱ ያው የእነርሱ ኃላፊነት ነው የሚሆነው። በዚያ ፍጥነትም ሆነ ደረጃ ስላልተኬደ የዝግጅት ነገሮች አሉ ግን ወደ ተግባር ስላልተገባ አሁንም ከዐቃቤ ሕግ አስከ አሁን ድረስ ቀጠሮ ላይ ነን። ያልተመቻቹ ነገሮች ስላለ ይህንን ነገር እንዴት በፍጥነት እናስኪደው የሚለው ላይ እየተነጋገርን ነው። ግን የኛ ሆነ የእነርሱ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ተገናኝተን ጊዜም አስቀምጠን እንሒድበት የሚል ሐሳብ አለኝ።

ምናልባት እንደዚህ እርምጃ ለመውሰድ የተቸገራችሁት የፖለቲካ ሹመኞች ስለሆኑ ሊሆን ይችላል?
የእኛ ኃላፊነት ኦዲት ማድረግ ነው። ከዚያም ሥራችንን ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ነው። መጀመሪያ ለኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤቱ ነው ክፍተቶችን እንዲያስተካክል የምናቀርበው። ከዚያም መሥሪያ ቤቱ የሚጠራበት አካል ካለ ለተቋሙ እንልካለን። የተጠቃለለ ሪፖርት እና ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ሪፖርቶችን ደግሞ ለፓርላማ እናቀርባለን። በተጨማሪም ለሥራ አስፈፃሚ አካላት የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅሕፈት ቤትንም ጨምሮ እንልካለን።

ይህንን በአግባቡ ያለማንም ተፅዕኖ እንሠራለን። ይህን ለምን አደረጋቹ የሚል አንድም ሰው የለም፤ ሊኖርም አይችልም። አንድም ሰው ደውሎ በሌላም መልኩ መጥቶ ይህንን አድርጉ የሚል ሰው አይኖርም የለም ቢኖርም እንኳን ተቀባይነት የለውም አንቀበልም። ይሄ መሥሪያ ቤት በሕገ መንግሥት የተቋቋመ መሥሪያ ቤት ነው። ሕጋዊነቱን ተከትሎ የወጣው የመቋቋሚያ አዋጁም ብዙ ነፃነት ነው የሚሠጠው። ሥራ ነፃነት አለው በተጨማሪም አልሞ አቅዶ መሥራት የተሟላ ነፃነት አለው። በተወሰነ ደረጃ ከበጀት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አሉ። ከዛው ውጪ ነፃና ገለልተኛ ነው።

በበጀት በኩል ያለው ክፍተት ምንድን ነው?
በጀት ላይ ያለው ችግር ሥራችንን የሚያስተጓጉል ቢሆንም በሕጉ መሠረት በጀት ቀጥታ ለፓርላማው ቀርቦ ነው መፅደቅ ያለበት። የእኛ ሕግ የሚለው እሱን ነው፤ ግን በተግባር የዋለው አሠራር በተቃራኒው ነው። ላለፉት ኹለት ዓመታት በቀጥታ ለፓርላማው ማቅረብ ጀምረናል።

እስካሁን ግን ገንዘብ ሚኒስቴር ጣሪያ እያወጣ ይሠጠናል። አንዳንዴ አሳማኝ ነገር አምጡ (‘ዲፌንድ’) ይላሉ፤ ይሁን እንጂ ገንዘብ ሚኒስቴር ራሱ ኦዲት የምናደርገው ተቋም ነው። ያ ትክክል አይደለም ብለን እየገፋን ነው ያለነው። አሁን ፓርላማው በሕጉ መሠረት በጀቱን ለእኛ አቅርቦ እናፀድቃለን በሚለው ሐሳብ ተግባብተናል።
ለኹለት ዓመታት ገንዘብ ሚኒስቴር ሔደን የማሳመኛ ሥራ አልሰራንም፤ ፓርላማ ላይ ሔደን ነው ሐሳብ ያቀረብነው። አምና ትንሽ ችግር አለ ዘንድሮ ደግሞ ለማስተካከል ከፓርላማው ጋር ተነጋግረናል። የበጀት ነፃነት በተሟላ መንገድ መከናወን አለበት ነው። ከዚያም ተቋሙን ማንም ተፅዕኖ አያደርግበትም ማለት ነው።

ግን እርምጃ በማስወሰድ ረገድ ደግሞ የእኛ ኃላፊነት አይደለም። ከእኛ የሚጠበቀው መከታተል እና እርምጃ ተወስዷል ወይስ አልተወሰደም ብለን እንደገና ማረጋገጥ ነው ያለብን። ካልተወሰደ ቅድም እንዳልኩሀ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጋር ሆነን ወደ ሕግ አግባብ እንዲሔድ ማድረግ ነው የእኛ ሥራ የሚሆነው።

ፓርላማው ሥራ አስፈፃሚው ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርግ ግፊት እያደረግን ነው። ባለሥልጣናቱ የአንድ ፓርቲ ወይም የሌላ ፓርቲ አባል ስለሆኑ ወይም ከዚያ ስለመጡ አይመስለኝም። በአጠቃላይ የተጠያቂነት ሥርዓቱን ከማስፈን ረገድ ጥብቅ አሠራሮች እስካሁን በነበረው ሁኔታ አልነበሩም። ፓርላማው መጥቶ ጠርቶ ይጠይቃቸዋል። እርምጃ እንወስዳለን፣ ተምረንበታል ኦዲት ግኝቱ ትክክል ነው ብለው ይሔዳሉ። አንዳንዱም ዋሽቶ ይሄዳል።

ፓርላማ ሲካሔድ፥ ይሄ ነገር ውሸት ነው ብለን ሕዝቡም እንዲገነዘበውም እናደርጋለን። ይሄ የሕዝብ አደራ ነው። የፓርላማ አባላቱም እንዲገነዘቡ እናደርጋለን። እኔ ብዬ የማስበው በፓርላማ ውስጥ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ጥግ ድረስ ተኪዷል ብዬ አላስብም። በአጠቃላይ በአገራችን ከነበረው የተጠያቂነት ስርዓት ካለመጠናከር ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር ነው። ይሄ ምናልባት በኦዲት ላይ ገዝፎ የሚታይ ይሁን እንጂ ሌላም አካባቢ የሚታይ ነገር ነው።

አንድ ባለሥልጣንም በሹመትም ይሠጠው በምንም የሕዝብ አደራና ቢሮ ነው የሚመራው። ከሕዝብ የተሰጠህን አደራ ባልተወጣህ ቁጥር መጠየቅ አለበት። ከኃላፊነት መነሳት የመጀመሪያው እርምጃ ሲሆን ቀጥሎ የሚመጣው የሕግና ሌሎች ተጠያቂነቶች መከተል አለባቸው። ይሄ የተጠናከረ ስላልነበረ ጅምርም ስላልነበረ ወደዚህ ርምጃ ባለመወሰዱ ምናልባት የመጣ ይመስለኛል እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆናቸው ችግር አይመስለኝም።

እናንተስ የመክሰስ መብት ወይም ደግሞ በሕግ የማቆም ሥልጣኑ ቢሰጣችሁስ? የሌሎቹ አገሮች ልምድ እንዴት ነው?
ኹለት ዓይነት ልምዶች ናቸው ያሉት። የ‘ዌስት ሚኒስቴር’ እና ‘ናፖሊታን ሲስተም’ የሚባሉ አሉ። ዌስት ሚኒስቴር ሲስተም ከእንግሊዞች የመጣ ሲሆን ኦዲተር ጀነራል ተብሎ ይጠራል። ሌላው ደግሞ ‘ኮርት ኦፍ ኦዲት’ የሚባለው ነው። እነዚህ የራሳቸው የሆነ ፍርድ ቤት አላቸው። ዋናው ኦዲት መሥሪያ ቤት ኦዲት ከማድረግ ባሻገር ዳኞች አሉት ጠርቶ ይጠይቅና እርምጃ ይወስዳል። የኦዲት ግኝት ተገኝቶበት እርምጃ ያልወሰደ ሰው ተከሶ ከተፈረደበት ሥልጣን ላይ እንዳይወጣ ገደብ ይጣልበታል ማለት ነው።

የኛ አገር አሠራር ከዚህ ለየት ይላል። እኛ የምንከተለው የዌስት ሚኒስቴር አሠራርን ነው።
የትኛው ነው እርሶ አሁን ባለው አሠራር ለኢትዮጵያ የሚጠቅመው የሚሉት?
ጉዳዩ የሕግ ብቻ አይደለም። መንግስትም በአግባቡ ሚናውን መወጣት አለበት። ስርዓት ቢዘረጋ ከሌሎች ስርዓቶች ጋር አብሮ አይሔድም እንጂ በቀጥታ ኦዲት ተደርጎ እየተከሰሰ ቢሄድ ሌላ አካል ስለማንጠብቅ ምናልባት የበለጠ ውጤት ሊያመጣ ይችላል።

ነገር ግን አሁን ያለውም ሊያስኬድ ይችላል። በተለይም ፓርላማ ሚናውን ሲወጣ ምንም ችግር ላያመጣ ይችላል። የመጀመሪያ አራት አመት ወደ ኦዲተር ቢሮ ስመጣ አንተ ምን እርምጃ ወሰደህ ነበር የምባለው ከዛ ፓርላማ አባላቶችን ስለ ተቋማችን አሠራር እና ተግባራት ማስረዳት ነበረብን። ከዚያም ጊዜ ወስደን የዓለም ዐቀፍ አሠራሮችን ፓርላማ እንዲረዳ አደረግን። ከዚያ እኔ ላይ የሚነሳ ጥያቄ መቆም ጀመረ።

ጭራሽ እኛ ነን እርምጃ መውሰድ ያለብን ማለት ጀመሩ። ይፋዊ የሕዝብ መድረኮች ማዘጋጀት ነበረብን። በፊት የነበረውን ግን አሳድገነውና ኦዲት ተደራጊ ተቋማት ምላሽ እንዲሰጡ በፓርላማ ፊት ማድረጉ ተጠናከረ። ከዚያም ባለፉት ሦስት ዓመታት ለውጥ መጣ። ለውጡም መፍራት ነበር። ኦዲት ተደራጊ ድርጅቶች እርምጃ መውሰዳቸውን መጠየቃቸው ሲጠናከር፤ ያጠፉት መፈናፈኛ አጡ።

መፍራት ግን መፍትሔ አይደለም። ስለዚህ ፓርላማው ከጥያቄ ባሻገር ክፍተቱን መስተካከሉን መከታተል እንዳለበት አመነ። ስለዚህም በወቅቱ በሥልጣን በነበሩት አፈ ጉባኤ አመራር ከፍተኛ ኦዲት ክፍተት ያለባቸው ተቋማት ክትትል እንዲደረግላቸው ተደረገ፤ ይህም ግን ለውጥ አላመጣም።

ከባለፈው በጀት ዓመት አንስቶ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ የትግበራ ዕቅድ ሰነድ አዘጋጅቶ ክትትል አድርጎ ለፓርላማ እንዲያቀርብ እየተደረገ ነው። በቅርቡ ኮሚቴው ሪፖርት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል። የሚፈለገው ውጤት ይመጣል አይመጣም ወይ የሚለው ከዛ ይታወቃል።

ግን ማን ነው የሚመራው ኮሚቴውን?
አፈ ጉባኤው ነው የሚመራው ግን የቴክኒካል ኮሚቴም አብሮ ተቋቁሟል። ይህ ዓይነቶች ጥረቶች ላይ በሚገባ ከተፈፀመ አሁን ያለው የሕግ በሚገባ ይሠራል።

ብዙ ጊዜ የምትወስዷቸው እርምጃዎች ክፍተት ካጋጠመ በኋላ ነው። ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት እርምጃ አትወስዱም። ለምሣሌ ፕሮጀክቶች ላይ ስንመለከት ወጪያቸው ተገቢ ጥናት ተደርገው ባለመጀመራቸው በከፍተኛ መልኩ ሲጨምር ተስተውሏል። ይህንን ቀድሞ መከላከል ለምን አልተቻለም?
ሁሉንም መቆጣጠር አንችልም። የኛ ግፊት በቂ ሥርዐት ተዘርግቷል ወይ የሚለውን ማየትና ማሳወቅ ነው። ክፍተት ከዛ ምክር እናቀርባለን። ሌላው ደንብና አሠራሮች በሚገባ ተተግብረዋል ወይ የሚለውን እንመለከታለን። የክዋኔ ኦዲት ሥራዎቻችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በ2003 እንኳን የቀደሞ ገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴርን የፕሮጀክት ገንዘብ አፈቃቀድ ስርዓትን ኦዲት አድርገን ለሕዝብ ይፋ አድርገን ነበር።

 

‹‹ይህን ለምን አደረጋቹ የሚል አንድም ሰው የለም፤ ሊኖርም አይችልም››

 

ምን አገኛችሁ ታዲያ?
ሰፊ ክፍተቶች ነበሩ። ፕሮጀክቶች ያለ ጥናትና ከመመሪያው ውጭ ተፈቅደዋል። ግን የተወሰዱ ምንም እርምጃዎች በተለይም እስከ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ አልነበሩም። ክፍተቶችን በተለያዩ የመንግሥት አካላት ብንሰጥም ምላሽ እምብዛም ነበር። ነገር ግን፤ በቅርቡ የፕላንና ልማት ኮሚሽን የእኛን ምክሮች በመቀበል እርምጃ መውሰድ ጀምሯል።

አሁንም ግን መንግሥትና ፕሮጀክቶች በኮታ እንጂ በጥናት ሲተገበር አይታይም። ለምሳሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከገበሬዎች ጋር ያላቸው መስተጋብና የሚያመጡት ገቢ ሳይታይ ነው እየተተገበሩ ያሉት?
አንድ ፕሮጀክት ትርፋማ ነው ወይስ አይደለም የሚሉትን የምናይበት መንገዶች አሉ። ለምሳሌ፡- አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን አዋጭነት አይተን ነበር። ዓላማቸው ምርታማነትን አሳድጎ ድህነትን መቀነስ ነው። ከዚያ ግን የተሠሩት ገደል ውስጥ ነበር። ከገደሉ ወጥቶ ለኅብረተሰቡ ጥቅም የሚውልበት መንገድ በአግባቡ ሳይታይ ነው የተጀመሩት መንገዶችም ላይ ተመሣሣይ ችግር ይታያል።

ቅድመ አዋጭነት ጥናት ወሣኝ ነው ይህንን ለመከታተል፤ ነገር ግን ሲተገበር አይታይም። ለምሳሌ እኛ ባደረግነው የኦዲት ምርምራ ከአርባ ዓመታት በፊት በተደረገ ጥናት መሠረት የተጀመረ ስኳር ፋብሪካ ማግኘት ችለናል። የሚያሳዝነው ምንም ዓይነት ተጨማሪ ጥናት ሳይደረግ ነበር ፕሮጀክቱ የተጀመረው።

አሁንም ቅድመ አዋጭነት ጥናት ሳይደረግ ወደ ተግባር የሚገባ ከሆነ ተመሳሳይ ችግር ይገጥመናል። የሚያመጡትም ውጤት በሥራ ዕድል ፈጠራና ለሚያመጡት ገቢ መታየት ይኖርበታል። በግንባታ አኳያ የሚፈጁት ጊዜ መታየት አለበት። ለምሳሌ የማዳበሪያ ፋሪካዎች እንመልከት። በሦስት ዓመት ያልቃል ተብሎ ቢታቀድም 10 ዓመት አልፎታል። ይህ አሁን በምን መልኩ አዋጭ አይደለም። ይህ ዓይነቱ ችግር ምን ኪሳራ አገሪቷ ላይ እያከተለ የሚለውንም ለማየት እየሞከርን ነው።

ብዙ ችግሮች የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ላይ የኦዲት ክፍተት ችግሮች በስፋት ይታያል። በተጨማሪም የኦዲት ሪፖርታቸው ለሕዝብ ግልፅ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ብዙ ክፍተት አሉባቸው። በዚህ አኳያ ለምን ግልፅ ያልሆናችሁት?
ኹለት ነገሮችን ግልፅ ላድርግ። ኮሚሽን ኦዲት የሚባል አሠራር አለ። በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥት ኦዲት በይዘቱ ሰፋ ያለ ነው። ምክንያቱም የሚያየው ‘Regulation of transaction’ ብቻ ስላልሆነ ነው፡:፡ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች እናያቸዋለን። በተወሰነ መልኩ በእኔ ሪፖርት ውስጥ ተካቶ ለመንግሥት ይቀርባል ነገር ግን የመጀመሪያ ትኩረቴ የመንግሥት ኦዲት ላይ ነበር። ምክንያቱም የዛሬ ዐሥር ዓመት ከፍተኛ ክፍተት ስለነበር ነው።

ታዲያ በዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ለምን እርምጃ አልተወሰደም?
አንዳንድ የሕግ ክፍተቶችን መስተካከል ነበረብን። ይሁን እንጂ መመሪያ ተከትለው እንዲሠሩ ለማድረግ ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ የተለያዩ ማኑዋል አዘጋጅተን ሰጥተናል። ይህን ተከትለው ሥሩ ወይስ አልሰሩም የሚለውን ለማረጋገጥ ምንም አላደረግንም። በዚህ መልኩ ግን አንቀጥልም።

አሁን አንድ ሥራ ክፍል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ኦዲት ለመቆጣጠር አዘጋጅተናል። ከመዋቅር ጋር በተያያዙ የሚቀሩት ሥራዎች ይቀሩናል፤ ያ ሲጠናቀቅ እናጠናክራለን። እስከዚያ ድረስ ግን ባላቸው ስትራቴጂክ አቅም በመነሳት ትልቅ ፕሮጀክቶችን ከዚህም ቀደም እንደምናደርገው እየተመለከትን ነው። ለምሣሌ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቅርቡ ክዋኔ ኦዲት አድርገን ነበር። በተመሳሳይ አሁን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት አፈፃፀማቸውን እየተመለከትን ነው።

ሌላው ደግሞ ከፍተኛ የሠራተኛ ፍልሰት በተቋማቹ እንደሚያጋጥም ይስተዋላል። አሁን የተስተካከለ ነገር አለ?
ምንም የተስተካከለ ነገር የለም። በተወሰነ መልኩ ተረጋግቶ ነበር ግን ለውጥ የለም።

እንደ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም እንዳደረጋቹ የናንተም ተቋም ካለው የተለያየ ተልዕኮ አንፃር የደሞዝ ጭማሪ ለምን አታደርጉም?
እዚህ አገር ላይ የተሻለ ደሞዝ ሊኖረው የሚገባ ተቋም ቢኖር የኦዲተር ጀነራል ቢሮ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ሁሉንም ተቋም ኦዲት ማድረጉ ነው። የሕዝብ ጥቅም ተነካ ተብሎ ከታመነ ደግሞ የግል ተቋማትንም ቢሮው ኦዲት ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህም ኦዲት ከሚደረጉት ተቋማት በበለጠ ተቋሞችን የበለጠ አቅም ሊኖረው ይገባል። የተለያዩ ምርምሮችን ለመከታተል እና ችግሮችን ለመለየት አቅም ያለው የሰው ኃይል ያስፈልጋል። ከተመራማሪዎች እኩል ወይም የበለጠ ዕውቀት ኦዲተሮች ሊኖራቸው ይገባል።

ሌሎች አገራት ላይ በጣም ተከፋይ የሆነ ተቋም ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ነው። ለዚህ ደግሞ ሚናው አንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ስላልሆነ ነው። ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ሁሉንም መዳሰሱ የተለየ ክፍያ እንዲያገኝ ያደረገው ምክንያቶች ናቸው። ብንጠይቅም ይህንን ያለመረዳት ችግር አለ። ወደፊት አገሪቱ ሊወስዱ የሚችሉ ተቋማትን መገንባት ሁሉንም ስርጭት ላይ ቁጥጥር የሚያደርጉ ከመንግሥት ጫና ነፃ የሆነ ተቋም ወሣኝ ናቸው። ስለዚህ ልዩ ትኩረት ይገባቸዋል። ሌላ አገር የመንግሥት ከ1-3 በመቶ በጀት ለኦዲተር መሥሪያ ቤቶች ይመደባል። የኛም ተቋም አሁን ባለበት መንገድ መቀጠል የለበትም። ሌላው አገር የኦዲተር መሥሪያ ቤት ወደፊቱን ችግሮች ሳይቀር ይጠቅማሉ። ለእኛ ይህንን ማድረግ አዳጋች ነው። ምክንያቱም ብቁ ሠራተኞችን ማቆየት አስቸጋሪ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here