የሕወሓት 44ኛ የምስረታ ዓመት ጉራማይሌ አከባበር

0
734

‹‹ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ትዕግሥት የሚባል ነገር አይሠራም››
-ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)

‹‹የሕውሓት አመራሮች ከትግሉ ዓላማና ግብ ውጭ በመራመድ አገሪቱን ለችግር ዳርገዋታል››
-አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) 44ኛ ዓመት የምስረታ በዓል፣ የካቲት 11/ 2011 በመቀሌ የሰማዕታት ሀውልት በርካታ የግንባሩ እና የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ነባር ታጋዮች እና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ተከብሯል። በዕለቱ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ሕገ መንግሥቱን የመጣስና፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች የሚሰነዘሩበት እንደሆነ ተናግረው፣ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን አንዱ የሚጠብቀው አንዱ የሚጥሰው መሆን እንደሌለበትም አሳስበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዕለቱ ለትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ “ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ትዕግሥት የሚባል ነገር ሁሌ አይሠራም፣ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ብለዋል።

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለዓሉ ባወጣው መግለጫም አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሰላምና መረጋጋት እየጠፋ መሆኑን፣ የሕዝቦች መሠረታዊ ፍላጎቶች የሆኑትን ልማትና ዴሞክራሲ ወደ ጎን በመባላቸው የተጀመረው ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሐዊ የልማት ዕድገት ችግር ውስጥ በመውደቅ ላይ ስለመሆኑ አትቷል።
መግለጫው፣ ሕወሓት ከ44 ዓመት በፊት ትግል ሲጀምር፣ በአገሪቱ የነበረው ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገርሰስ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩልነት የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዓላማ ያነገበ እንደነበርም አስታውቋል።

በ17 የትጥቅ ትግል ዓመታት ለመገመት የሚያስቸግር የሕይወት፣ አካልና ንብረት መስዋዕትነት መከፈሉን ያስታወሰው ማዕከላዊ ኮሚቴው፣ በዚህም ኢትዮጵያን ከመበታተን በማዳን፣ ባለፉት 27 ዓመታት ወደ አዲስ የልማትና የዴሞክራሲ ምዕራፍ መሸጋገር መቻሉን ገልጿል።

ድርጅቱና ደጋፊዎቹ የምሥረታ በዓሉን የሚያከብሩት፣ በኢትዮጵያ የተጀመረውና መላው ዓለም የመሰከረለት የለውጥና የዕድገት ጉዞ ወደ ኋላ እየተቀለበሰ፣ ብርሃን ማየት የተቻለበት የብልፅግና ጉዞ ወደ ሥጋትና ጭንቀት እየተቀየረ ባለበት ወቅት እንደሆነም መግለጫው አስታውቋል።

“የዚህ ሁሉ ችግር መሠረታዊ ምክንያት፣ በኢሕአዴግ አመራር ውስጥ እየተንከባለሉ የመጡ የጥገኝነት አስተሳሰብና ተግባር ወደ ከፋ ደረጃ በመድረሱ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ከዚህ ቀደም በኢሕአዴግ አመራር የተጀመረውን በጥልቀት የመታደስ ሒደት በጋራ በተቀመጠው አቅጣጫ ባለመሔዱና በመኰላሸቱ፣ እንዲሁም የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በመኖሩ ጭምር ነው፤” ይላል መግለጫው።

“ለአገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት መረጋገጥ ዕድሜ ልካቸውን የደከሙና የለፉ የሚረገሙበትና የሚብጠለጠሉበት፣ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዜጎች ላይ የተለያዩ በደሎችና ግፍ የፈጸሙ፣ እንዲሁም የአገራቸውን ሉዓላዊነት አሳልፈው የሰጡ ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር አብረው አገርና ሕዝብ የወጉ የሚመሠገኑበትና ክብር የሚሰጥበት የክህደት ዘመን ላይ ደርሰናል” በማለት ሕወሓት ተችቷል።

ስለዚህ ጉዳይ አዲስ ማለዳ ማብራሪያ የጠየቀቻቸው የትግራይ ብሔራዊ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሊያ ካሳ ክህደት ተፈጽሟል ሊባል የቻለው “ያለፉት 27 ዓመታት ልማት ተረስቶ ሁሉም ጨለማ እንደነበር መወሰዱና ለችግሮች ሁሉ ሕወሓትንና የትግራን ሕዝብ ተጠያቂ የማድረግ ነገር ስለመጣ ነው” ብለዋል። አልፎ ተርፎም “በትግራይ ተወላጆች ላይ እንዲዘመት እየተደረገ ነው” ሲሉም ወቅሰዋል።

ሕውሓት በነአረጋዊ በርሄ የገጠመው ተቃውሞ
የአገሪቱ ሁኔታ ሕወሓት ካወጣው መግለጫ በተቃራኒ እንደሆነ የሚገልፁ አሉ። የትግራይ ዴሞሪያሲያዊ ትብብር (ትዴት) እሁድ የካቲት 10 በቶፕ ቴን ሆቴል ባካሄደው ስብሰባ፣ ከሕወሓት ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ አንጸባርቋል። በዕለቱ፣ የሰማእታት መታሰቢያ በዓልን ምክንያት አድርጎ በቀረበው በዚህ ዝግጅት ላይ፣ “ትግሉ ግቡን መቷል ወይ?” በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) “የሕውሓት አመራሮች ከትግሉ ዓላማና ግብ ውጭ በመራመድ አገሪቱን በብሔርና በጎሳ ከፋፍለዋል፤ የፌደራሊዝሙን ጽንሰ ሐሳብ በሳተ መልኩ በመንቀሳቀስ አሁን ለምናየው የመከፋፈል ፖለቲካ ዳርገውናል። በመሆኑም አመራሮቹ ለአገሪቱ ሰላም ማጣትና ውድቀት ቀዳሚ ተጠያቂ ናቸው” ሲሉ ተደምጠዋል።

አረጋዊ “ትላንት የትግራይ ሰማዕታት የተዋደቁት፣ ሕይወታቸውን የገበሩት፣ በዱር በገደሉ የተንከራተቱት ጥቂቶችን ለማንገስ አልነበረም። ሰማዕታት ውድ ሕይወታቸውን የሠጡት ጥቂቶች በሙስና ባሕር ተዘፍቀው፣ የብዙኃኑን መብት እንዲጨፈልቁ፣ በሥልጣን አለአግባብ እንዲባልጉ አልነበረም። የትግራይ እና የሌሎች ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች እልህ አስጨራሽ መሰዋዕትነት የከፈሉት ጥቂት የሕወሓት አመራሮች የሐሳብ ልዩነት የፈጠሩ የገዛ ወገናቸውን እንዲያሳድዱና በሐሰት ወንጅለው እንዲያሰቃዩ አልነበረም” ብለዋል።

“የሕወሓት አመራሮች ዓመት ቆጥሮ በዓል ከማክበር በዘለለ ቆም ብለው ከየት ተነስተን የት ደረስን የሚለውን ሊያስቡት፣ ሊፈትሹት ይገባል። ለዴሞክራሲ፣ ለሕዝቦች ነጻነትና እኩልነት እንዳልታገልን፣ እንዳልተዋደቅን ሕዝባዊ ቁጣ ለምን ተቀሰቀሰብን ብለው ራሳቸውን ሊጠይቁ፣ ተገቢው እርምት ሊወስዱ የሚገባቸው ጊዜ ቢረፍድም አሁን ነበር። ግን በተግባር ይህ እየሆነ አይደለም። ይባስኑ ለመጪው ትውልድ ቂምና ጥላቻን ለማውረስ የሚዳዱ አመራሮች መኖራቸውን እያየን፣ እየታዘብን ነው” ሲሉም አክለዋል።

ሕወሓት በፖለቲካ ማዕከሉ ላይ የነበረው ተፅዕኖ በመቀነሱ የመገፋት ስሜት ሊጫነው እንደሚችል የሚናገሩት ፖለቲከኛው የሸዋስ አሰፋ “ይኼንንም የሚያባብሱ የፖለቲካ ትግሎች በኢሕአዴግ ውስጥ መቀጠላቸው በግልጽ የሚታይ ቢሆንም፥ ጉዳዩን ከሕዝብ ጋር ማገናኘት ስህተት ነው። ሕወሓት የጎዳው የኢትዮጵያን ሕዝብ ቢሆንም፣ ከፍተኛ በደል የፈጸመው ግን በትግራይ ሕዝብ ላይ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

የሸዋስ “የሕወሓት አመራሮች የሠሩት በደልና ግፍ አገር ከማፍረስ የማይተናነስ ነው፤ ለበደሉት በደልም ሊጠየቁና ሕግ ፊት ሊቆሙ ይገባል፤ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ መሽገው ሕዝቡ ላይ ውዥንብር እየፈጠሩ የሚገኙት የቀድሞ አመራሮችም ችላ ሊባሉ አይገባም” ሲሉ ተደምጠዋል። “በአገራችን የሚታየው የማንነት ጥያቄዎች መበራከት፣ በብሔር የሚደረጉ ግጭቶችና አለመግባባቶች፣ የሕወሓት አመራሮች ባለፉት 27 ዓመታት ያወሳሰቧቸው ችግሮች ናቸው” ሲሉ ያክላሉ።

በሕወሓት አመራሮች የተበላሸ አሠራርና በደል፣ የትግራይም ሕዝብ አብሮ ተጠያቂ መሆን የለበትም ያሉት አረጋዊ “እነዚህ ሙሰኛና ጨካኝ የሕወሓት አመራሮች፣ በትግራይ ተደብቀው ሕዝቡን እያንገላቱት ነው፤ መንግሥት ይህንን ችላ ማለት የለበትም፤ እኛም ሕዝቡ በነጻነት ሐሳቡን የሚገልጽበትና ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ ሌሎች አማራጮችን የሚያይበት ዕድል እንዲያገኝ መሥራት ይኖርብናል። ይህ ሲሆን ነው የትግራይ ሕዝብ ነጻ የሚወጣው” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት፣ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የሰላም እጦቶችን በመቅረፍ፣ የሕዝብ በተለይም የወጣቱን መሠረታዊ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በመመለስ፣ የተጀመረውን የተሃድሶ ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባም አረጋዊ አሳስበዋል።

የደብረጽዮንና የፓርቲያቸው መግለጫ በምሁራንም ተቃውሞ ገጥሞታል
ሰሞኑን የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ያደረጉት ንግግር በፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ትችት እየቀረበበት ነው። ደብረፅዮን ለትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ “ወቅቱ የደርግ ባለሥልጣናት የነበሩና ሌሎች ኃይሎች በሕዝብ ላይ ጫና ለመፍጠር እየሠሩ ያሉበት ነው” ማለታቸው ይታወሳል። የኢትዮጵያ ፌደራላዊና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን መንግሥታቸው በዝምታ እንደማይመለከተው መግለጻቸውን ተከትሎ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ቻላቸው ታረቀኝ ለጀርመን ድምጽ ራዲዮ በሰጡት አስተያየት “የፌዴራል ስርዓቱ አደጋ ላይ መውደቅ ከአንድ የፖለቲካ ኃይል ብቻ የሚሰማ አስተያየት ነው” ሲሉ ተችተዋል።

አክለውም፣ ውጭ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገር መግባታቸው፣ ለውጡ የፈጠረው አዎንታዊ እርምጃ ነው ሲሉ ተናግረዋል። የፌደራል ስርዓቱ መሸራረፍ፣ ሕገ መንግሥቱ መጣስ በተደጋጋሚ በአንድ የፖለቲካ ኃይል ብቻ እየተነሳ ነው ያሉት ምሁሩ፣ በሚባለው መጠን ስጋት እንደሌለም ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የታከለ ዑማ በበዓሉ ላይ ሳይገኙ መቅረት
ሕወሓት 44ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ ታከለ ዑማ የሚመራ ልዑካን ቡድን የሚያደርገው ጉብኝትም፣ የበዓሉ አካል ሆኖ የአቀባበል ሥነ ሥርዓትና የጉብኝት ፕሮግራም መዘጋጀቱ በሕወሓት መግለጫ ላይ ቢገለጽም እሳቸው ግን ሳይገኙ ቀርተዋል። ታከለ በሰማዕታት ሐውልት ጉንጉን አበባ ያኖራሉ ተብሎ ሲጠበቅም ነበር።

ተለያይተው የቆዩት የሕወሓት አመራሮች በጋራ መድረክ መገናኘት
በፖለቲካዊ ምክንያት ለዓመታት ተለያይተው የቆዩት የሕወሓት ነባር አመራሮች በመቀሌ ተገናኝተው 44ኛውን የካቲት 11 በዓል በጋራ አክብረዋል።
ከሰሞኑ የበዓል ሁነት በመልካም ጎን ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ቀደም ሲል ከግንባሩ የተባበሩትን ስዬ አብርሃ፣ ገብሩ አስራት፣ አረጋሽ አዳነ እና ሌሎች ጋር ዕርቀ ሠላም ማውረዳቸው እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። ከዚህ በመነሳት እነስዬ በቀጣይ አንዳንድ የሕወሓት አመራሮች ከያዙት መካረር ወጥተው ለአገር ሰላምና መረጋጋት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡ አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል የሚል ተስፋን የሰነቁም አሉ።

በ1993 ሕወሓት ካጋጠመው ክፍፍል በኋላ ነባር የሚባሉት የግንባሩ መስራችና አመራሮች ተነጥለው መውጣታቸው ይታወሳል። ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ መድረክ ተገናኝተው ትግል የጀመሩበትን 44ኛ ዓመት አክብረዋል።

የቀድሞ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዲሁም ከክፍፍሉ በኋላ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት የተባለ ፖርቲ ከአጋሮቻቸው ጋር መሥርተው እየተንቀሳቀሱ ያሉት ገብሩ አስራት “የካቲት 11 የአንድ ድርጅት በዓል ተደርጎ እየተከበረ መቆየቱ ተገቢ አልነበረም” ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል። የቀድሞ ታጋይ፣ ከትግል በኋላ የመከላከያ ሚኒስተር የነበሩት እንዲሁም ከክፍፍሉ በኋላ ለዓመታት ታስረው የተፈቱት ስዬ አብረሃ በበኩላቸው “ብዙ መቆሳሰል ቢያልፍም የጋራ ታሪክ አለን” በማለት በዓሉን ከቀድሞ ጓዶቻቸው ጋር ማክበራቸው ጥሩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ሊያ በበኩላቸው የቀድሞ አመራርና አባላት በበዓሉ ላይ የመገኘት መልእክት በታዳሚዎቹ መካካል “የሐሳብ ልዩነት ቢኖርም የትግራይ ሕዝብ የደኅንነትና ሕልውና ስጋት ሲደቀንበት በጋራ መቆም እንደሚገባ ማሳያ ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት የትግራይ ሕዝብ የሕልውና ስጋት አለበት ብሎ ያምናል ወይ ለሚለው ጥያቄም የቢሮ ኃላፊዋ አዎ የሚል ምልሽ ሰጥተዋል።

በፌደራል መንግሥት ፊት የተነሳው የሕወሓት በዓል
ሕወሓት 44ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ብቻውን በሩን ዘግቶ አክብሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቅዳሜና እሁድ በካቢኔ እና በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች ስብሰባ ራሳቸውን በሥራ ጠምደው ያሳለፉ ሲሆን፣ ቅዳሜ ዕለት በጅግጅጋ ለተከፈተው 8ኛው የከተሞች ጉባኤ በዋዜማው የእንኳን አደረሳችሁ የጽሑፍ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመንግሥት ሥልጣናቸው ባለፈ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርም በመሆናቸው በሕወሓት በዓል ላይ አለመገኘታቸውና ምንም ዓይነት መልእክት አለማስተላለፋቸው በራሱ ለሕወሓት አመራሮች የሚያስተላልፈው መራር መልዕክት አለው የሚሉ ወገኖች አሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here