ኹለቱ የላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለጸ

ኹለቱ የላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለጸ

ከዐስራ አንዱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት መካከል ቤተ-ማርያም እና ቤተ-መድኃኒዓለም የመሰነጣጠቅ አደጋ እንደደረሰባቸው የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን ላሊበላ ከተማን ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ወራት፣ በቀጥተኛ መንገድ ባይሆንም በአብያተ ክርስትያናቱ ውስጥ የሚገኙ የድንጋይ ፍልፍል ቅርሶች የላይኛው ክፍላቸውን ለመትረይስ እና ለሌሎች ከባድ የጦር መሣሪያ መደገፊያ አውሎ ለመተኮሻነት እንደተጠቀማቸው ተገልጿል። በዚህም የተነሳ የመሰነጣጠቅ አደጋ እንደገጠማቸው የቢሮው ኃላፊ መልካሙ ዓለሙ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከኹለት ዓመት በፊት ጀምሮ ከዐስራ አንዱ መካከል ቤተ-ማርያም እና ቤተ-መድኃኒዓለም አደጋ ተጋርጦባቸው እንደነበር አውስተዋል። እናም እነዚህ ቀድመው የተጠቀሱት ቅርሶች ለጦር መሣሪያ መተኮሻ እንደድጋፍ መዋላቸው የጉዳት መጠኑን ከማስፋቱ ባሻገር፣ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ እንዲገኙ ማድረጉን መልካሙ ተናግረዋል።

ኃላፊው አያይዘውም፣ በኹለተኛው ምድብ የተቀመጡት ቤተ-አማኑኤል፣ ቤተ-ገብርኤል፣ ቤተ-መርቆርዮስ፣ ቤተ-አባ ሊባኖስ፣ ቤተ- ሚካኤል እና ቤተ-ጊዮርጊስም ላይ አደጋው እንዳለ ገልጸዋል። የከተማ አስተዳደሩ ‹በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም› በፌዴራል መንግሥት በኩል ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ፣ እንዲሁም የፈረንሳይ መንግሥትም በሙሉ አቅሙ ወደ ጥገና መግባት ባለመቻሉ በቅርሶች ላይ የተጋረጠው አደጋ ጨምሯል ብለዋል።

በፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና በላሊበላ ከተማ አስተዳደር በኩል በየዓመቱ ራሱን የቻለ በጀት በየስድስት ወሩ በመመደብ፣ ከኹለት መቶ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎችን በመመልመል በአብያተ ክርስትያናቱ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶችን በየጊዜው የማፅዳት ዘመቻ ይከናወን ነበር። ይህም በ2013 በመጀመሪያው ሩብ ዓመት አለመከናወኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።

የፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፣ በሕወሓት ቡድን ቤተ-ማርያም እና ቤተ-መድኃኒዓለም አብያተ ክርስትያናት ላይ የመሰነጣጠቅ አደጋ እንደደረሰባቸው የሚጠቁም መረጃ አልደረሰንም፤ ባለሥልጣኑም ራሱን በቻለ ጥናት አላረጋገጠም ብለዋል።

ዳይሬክተሯ አክለውም፣ ባለሥልጣኑ ከጦርነቱ በፊት ለቅርሱ የሚገባውን በጀት መድቦ ከመሥራት እንዳልተቆጠበ እና አሁን ባለው ሁኔታ ባለሥልጣኑ ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ታቅዶ የነበረውን የጥገና ሥራ ለማስጀመር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅርሶች ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ከሚደርስባቸው አደጋ በተጓዳኝ፣ ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ወደ ሥልጣን በሚመጡ መንግሥታት ትኩረት ማነስ፣ ለበርካታ ዓመታት ተገቢውን መጠለያ ማግኘት ባለመቻልና በመሳሰለው ምክንያት ለችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል።

ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ከመንግሥት ጋር ውል ተዋውለው ወደ ሥራ የሚገቡ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ተገቢውን ጥገና ባለማድረጋቸው እና ድርጅቶችን የሚቆጣጠራቸው አካላት ትኩረት አናሳ መሆን፣ ከዛም ባለፈ ዘላቂ ወይም አስተማማኝ ጥገና በመነፈጋቸው የጉዳቱ መጠኑ አሳሳቢ ወደሚባል ደረጃ እንዲደርስ ማድረጉን በተለያየ አጋጣሚ ይገለጻል።

አሁን ባለው ሁኔታ የፈረንሳይ መንግሥት ጥገና ማድረግ ለመጀመር የሚያደናቅፉት ችግሮች አለመኖሩን ተከትሎ፣ ወደ ሥራ መግባት እንደሚችል የፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን አሳውቋል። ከ2011 ጀምሮ በፈረንሳይ መንግሥት ለቅርሶች ጥገና ለማድረግ አንዳንድ የጥናትና የዝግጅት ሥራዎች ተጀምረው የነበረ ቢሆንም፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪዲ 19 ወረርሽኝ እና በኋላም በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት እስካሁን ባለው ጊዜ ምንም ዓይነት ዕድሳት አለመጀመሩ ተመላክቷል።

በዩኔስኮም ሆነ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ዘላቂ መፍትሔ አለመቀመጡን እና ተገቢውን ትኩረት አለማግኘቱን ተከትሎ፣ የላሊበላ አብያተ ክርስትያናት በውስጡ የሚገኙ ቅርሶች ከተጋረጠባቸው አደጋ መላቀቅ አለመቻላቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here