በሦስት ወራት 150 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ከውጭ እንዲገባ ተወሰነ

0
580

መንግሥት የኑሮ ወድነትን ለማሻሻልና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ተከታታይነት ያለው እርምጃ እንደሚወስድ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ መጋቢት 7/2014 በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ መንግሥት በሰጠው አቅጣጫና የአገሪቱ ብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን በወሰነው መሠረት የኑሮ ውድነትን ለማሻሻልና ገበያውን ለማረጋጋት በሚቀጥሉት ሦስት ወራት 150 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ከውጭ እንዲገባ ተወስኗል።
በአሁኑ ጊዜም 12.5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ወደ አገር ውስጥ እየገባ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 4.8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ለኅብረተሰቡ እየተከፋፋለ ነው። 7.7 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ደግሞ በሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ወደ አገር ውስጥ ተጠቃሎ እንደሚገባ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ድፍድፍ ዘይት ከውጭ አስመጥተው በአገር ውስጥ ለሚያመርቱ ሦስት ፋብሪካዎችም ምርቶቻቸውን ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ የውጭ ምንዛሬ ተመቻችቶላቸዋል። የምግብ ዘይት እጥረትን ለዘለቄታው ለመፍታት እንዲቻልም ለሌሎች አቅራቢዎችም ዘይት ከውጭ አስመጥተው ለመንግሥት እንዲሸጡ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑንም ሚኒስትሩ አህመድ ገልጸዋል።
መንግሥት የኑሮ ወድነትን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ባለፉት ኹለትና ሦስት ዓመታት የምግብ ዘይት ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ በማድረጉ 23.7 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉንም ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here