እናትና አባት ተገድለው ልጅ መውሰድ ማለት፣ ይሄ ዘር ማጥፋት ነው

0
989

ኡገቱ አዲንግ ይባላሉ። ትውልድና እድገታቸው በጋምቤላ ክልል ሲሆን፣ በማስተር ኦፍ አድምንስትሬሽን ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል። በአሁኑ ወቅት የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር የድንብር አዋሳኝ መሆኑን ተከትሎ በተለይ ከ2008 ወዲህ የሙርሌ ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው እየገቡ ጥቃት ያደርሳሉ። በዚህም ሕጻናት ዋና ተጎጂ ሲሆን፣ ነዋሪዎችም ሀብት ንብረታቸው ይዘረፋል፤ ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉም ይሆናሉ። አዋሳኝ ድንበሩ ሰፊ ከመሆኑ አንጻርም በፍጥነት መፍትሔ መስጠትና በተከታታይ የሚከሰተውን ይህን ችግር መፍታት የተቻለ አይመስልም። በቅርቡም በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ ክልሉ መሀል ከተማ ለመግባት ተገድደዋል። ነገሩም እየተባባሰ መጥቷል።
የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ኡገቱ አዲንግን በዚህ ጉዳይ ላይ አናግሯቸዋል። የነበረውንና ያለውን ሁኔታ፣ ወደፊት ምን ይደረግ በሚለው ዙሪያም ተከታዩን ቃለምልልስ አድርገዋል።

የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ክልሉ በመግባት በየዓመቱ ሕጻናት እንደሚወስዱ፣ ንብረትን እንደሚዘርፉ ከሰሞኑ እየተሰማ ነው። አሁን በድንበር አካባቢ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ከዚህ በፊትም የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የሚገቡ እነዚህ ታጣቂ ኃይሎች በተደጋጋሚ በጋምቤላ ክልል ጥቃት እያደረሱ መሆናቸውን በተለያየ ጊዜ ዐይተናል፤ ሠምተናል። በአሁኑ ስዓት ደግሞ በተመሳሳይ ድንበር አካባቢ መጥተው ክልሉን ለመረበሽ የተለያዩ ሙከራዎች ያደርጋሉ፤ በዚህም የተነሳ በማኅበረሰብ ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው ያለው።

ከሰሞኑ ጥቃት ለማድረስ ጥናት አድርገው፣ የእኛ ሚሊሻና ልዩ ኃይል ባደረገው ኦፕሬሽን ጥቃት ደርሶባቸው ሸሽተዋል፤ ያመለጡበት ሁኔታም አለ። ስለዚህ አሁንም በተለያየ ደረጃ ሙከራዎች አሉ ማለት ነው። የእኛ የጸጥታ ኃይል በተለያዩ አካባቢዎች የሚሞከሩ ጥቃቶችን በመመከት የታጣቂ ኃይሎች ፍላጎት እንዲመክን እያደረገ ነው።

እነዚህ ኃይሎች ፍላጎታቸው ኹለት ነው። አንደኛው ዒላማቸው የገበሬ ከብቶች ነው። ኹለተኛ ደግሞ ሕጻናት። ሕጻናትን ከእናት ወይም ከወላጅ ጋር ከተገኙ፣ ወላጆችን/ቤተሰብን ገድለው ከዚያ ሕጻኑን ይወስዳሉ። እረኛ ከተገኘ ደግሞ እሱ ተገድሎ ከብቶቹን ይወስዳሉ።
እና አሁንም ላይ የተለያዩ ኦፕሬሽኖች እያደረጉ ነው። በእኛም የጸጥታ ኃይል በሚደረግ ጥረት ጥፋቱ እየከሸፈ ነው።

እነዚህን ታጣቂዎች የሚያደራጃቸውና የሚልካቸው አካል ማን እንደሆነ ይታወቃል? በትክክል ምክንያትና ፍላጎታቸውስ ምንድን ነው?
እነዚህን ኃይሎች የሚያደራጃቸውና የሚልካቸው አካል ይሄ ነው ለማለት ያስቸግራል። ምክንያቱም እኛ ባደረግነው ማጣረት መሠረት እንደ ‹ባህል› ነው የወሰዱት። ይሄ የሙርሌ ባህል ነው ብለን እንወስዳለን። ምክንያቱም ከጥንት ጀምሮ የሚያደርጓቸው ተመሳሳይነት ያላቸው ድርጊቶች አሉ።

ግፊት የሚያደርግባቸው አንዱ ኢኮኖሚ ነው። ኹለተኛ ደግሞ በባህል ይሄን ያላደረገ አንድ ሙርሌ፣ ሚስት ማግባት ስለማይችል ወጣትነቱን ወይም ወንድነቱን የሚያረጋግጠው ይሄን ሲያደርግ ብቻ ነው። ይህ ስለሆነ እንዳልኩት አንደኛ እንደ ባህል ወሰዱት፣ ኹለተኛ ደግሞ እንደ ኢኮኖሚ አማራጭ ቆጥረው ነው እየተጠቀሙበት ያሉት።

የታጣቂዎች በተደጋጋሚ ድንበር ጥሶ መግባት ከሉዓላዊነት አንጻር እንዴት ይታያል? ችግሩ በየዓመቱ የሚያጋጥም ከመሆኑ አንጻርም እልባት ለመስጠት ምን እየተሠራ ነው?
ይህ ጉዳይ በየዓመቱ የሚመጣ ወይም የሚከሰት ነው። እንደዚህ የሚሆን ከሆነ እስከ መቼ ይቀጥላል? የሚል ጥያቄም ያመጣል። ምክንያቱም ሁሌ እንዲህ ከቀጠለ ለማኅበረሰቡ ቋሚ የደኅንነት ሥጋት ይሆናል። እናት አባት ተገድለው ልጅ መውሰድ ማለት፣ ይሄ ዘር ማጥፋት ነው። ገበሬም ደግሞ ቤተሰቡን ለማስተዳደር ብዙ ዓመት ደክሞ ያገኘው ሀብት በአንድ ቀን የሚወሰድ ከሆነ፣ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው፤ አገርን መድፈር ነው የሚሆነው።

ይህ ስለሆነ በዋናነት የመፍትሔ አካል ያስፈልጋል። የመፍትሔ አካል የሚሆኑ በመንግሥት የተሠሩ ሙከራዎች አሉ። እነዚያ ሙከራዎች እስከ አሁን ስኬት ባይኖራቸውም እንኳ ጥሩ ሙከራ ተብለው የሚወሰዱ ናቸው።
አንደኛ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ከደቡብ ሱዳን ጋር መነጋገር ነው። ይሄን እንግዲህ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የተመረጠው፣ በክቡር ዋና አፈ ጉባኤ የተመራ ቡድን ወደ ደቡብ ሱዳን ሔዶ ከደቡብ ሱዳን የበላይ አመራሮች ጋር የተወያየበት ሁኔታ ነበር። ዋና አጀንዳው ጥፋቱን የሚያደርሰው ኃይል በደቡብ ሱዳን ድንበር አቋርጦ እንዳይመጣ፣ ይሄ ደግሞ ድንበር መድፈር ስለሆነ ተነጋግረው እንደ አንድ ትልቅ አጀንዳ አንድ ነጥብ ላይ የደረሱበት ሁኔታ አለ።

ግቡ እነዚህን የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ታጣቂዎች ለደቡብ ሱዳንም ሥጋት ስለሆኑ ጥቃታቸውን ማስቆም ነው። ወደ ኋላ ልመልስህ እና ቅድም እነዚህን ኃይሎች ማነው ያደራጃቸው ብለህ የጠየቅከው ጥያቄ ትክክል ነው። ማን እንዳደራጃቸው ባናውቅም፣ ባለን መረጃ ከዚህ በፊት ደቡብ ሱዳን ውስጥ ሆነው፣ በደቡብ ሱዳን ሌላ ሥጋት በነበረበት ጊዜ በተለያየ ወትድርና ውስጥ ገብተው የታጠቁ ኃይሎች ናቸው።

ሰው ገድሎ መሣሪያ መውሰድ በእነሱ የተለመደ ነው። ሕጻን ልጅም ቢሆን መሣሪያ ታጥቆ ነው የሚንቀሳቀሰው። ኑሯቸውንም በየጫካው ገብተው አውሬ እየገደሉ በመብላት ነው የሚገፉት።

እናም ድንበር አቋርጠው ወደ እኛ እንዳይመጡና ያንን ማድረግ የአገር ሉዓላዊነትን መድፈር ስለሚሆን ማስቆም እንዳለባቸው መንግሥት ተናግሯል። ከበላይ አመራሮቻቸው በሰጡት መልስም፣ ‹እነዚህ ኃይሎች ከእኛ አቅም በላይ ስለሆኑ፣ እናንተ ጋር የሚያደርጉትን ድርጊት በሙሉ እኛም ጋር ያደርሳሉ› ብለዋል። በቅርብ ጊዜ በደንካ ማኅበረሰብ ላይ በአንድ ጊዜ 32 ሰው የተገደለበት ክስተት ነው ያለው። ይሄን ችግር እንግዲህ ውጫዊ ብቻ ሳይሆን እዚያም የደቡብ ሱዳን ውስጣዊ ችግር ነው።

ስለዚህ የሚሆነውና ያገኘነው መልስ ኹለት ነው። አንደኛ በውስጥ ወደ እናንተ የገቡ ካሉ እናንተም እንዲሸሹ አድርጉ፣ በእኛም በኩል ደግሞ የአሰሳ በማከናወን ፈጣን ሥራ እንሠራለን የሚል ነው። ይሄ ግን በኹለት ወይም በሦስት ቀን የሚፈታ አይደለም፤ ጊዜ ይወስዳል።
በሌላ በኩል፣ በደቡብ ሱዳን በኩል የማኅበረሰቡን ጥያቄ ከመፍታት አንጻር የሚታዩ ችግሮች አሉ። እነዚህም በዋናነት የመሠረተ ልማትና ማኅበረሰቡ ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲላመድ ከማድረግ አንጻር የሚታዩ ናቸው። በራሳቸው አካባቢ የመንገድ፣ የቴክኖሎጂና የመሳሰሉ ከመንግሥት ጋር ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ብዙ የተሠሩ ሥራዎች የሉም። ይሄ ደግሞ አንድ ትልቅ የደቡብ ሱዳን የቤት ሥራ መሆን አለበት።

ስለዚህ ዋናው መፍትሔ የሚሆነው ከደቡብ ሱዳን ጋር ተነጋግሮ ወደፊትም እንደ መንግሥት ተቆጣጥሮ፣ እነዚህ ሽፍታዎች ወደ መሀል እንዳይገቡ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ነው። አለበለዚያ የደቡብ ሱዳን መንግሥት አልተረጋጋም ማለት እኛም ጋር መረጋጋት የለም ማለት ነው። ኹለተኛው ደግሞ ያንን ግንኙነት ከታች ያሉ አካላት እንዲያስፈጽሙ ማድረግ ነው። ትልቁ ነገር የሚሆነው ከታች ያለው አመራር በተለይ ዞንና አጎራባች ዞኖች፣ ወረዳ ከወረዳ፣ ዞን ከዞን ትስስር እንዲኖርና ውይይቶች እንደደረጉ ቢደረግ ትልቅ አማራጭ ይሆናል።

ጊዜያዊ አማራጭ የሚሆነው፣ በመንግሥት እየተቀመጠ ያለ ሚሊሻና ልዩ ኃይል በማደራጀት አካባቢው በአግባቡ እንዲጠበቅ ማድረግ፤ ማኅበረሰቡም ነቅቶ ራሱን እንዲጠብቅ የሚሉ ጊዜያዊ መፍትሔዎች አሉ። ዘላቂ የሚሆነው ግን መንግሥት ከመንግሥት ጋር የሚያደርጉት ንግግር ነው የሚሆነው የሚል ሐሳብ ነው ያለኝ።

ደንበር አቋርጠው የሚገቡት እነዚህ ታጣቂ ኃይሎች ድርጊቱን እንደ ባህል ወስደውታል ብለዋል። መለስ ብለው ታሪካዊ ዳራውን ቢያነሱልን?
እንዳልኩት ከዚህ በፊትም ድንበር አቋርጠው ይገባሉ። እኛም በልጅነታችን እንደሚገቡ አባቶቻችን ሲነግሩን ነበር። እየገቡ አንድም ኹለትም ልጆች፣ ከብቶችም ይወስዱ ነበር። ግን ትልቅ ልምድ ያደረጉትና እንደዛም እንዳደረጉት የተስተዋለው፣ እንደምናስታውሰው በትክክል በ2008 ባደረሱት ጥቃት ወደ 180 ሰው የሞተበትና ከ200 በላይ ሕጻናት የተወሰዱበት ጊዜ ነው። ያንን ነው ትልቁ ብለን የምንወስደው። ከ2008 በኋላ ግን በየዓመቱ እንደዚህ በተከታታይ እየተከሠተ ይገኛል።

የ2008 ጥቃት ካደረሱ በኋላ የእኛ መከላከያ በኃይል ተነስቶ ሔዶ ወደ 109 ሕጻናት ማስመለስ ችሎ ነበር። ይሄም ብቻ አይደለም፣ የሙርሌ ካምፕ የምንለው አለ። ወደ ስምንት ልጆች ካምፕ ውስጥ ነው የተገኙት። ግጭቱም አልቆመም፤ እየቀጠለ ነው የሔደው። በየዓመቱ እንደዚህ ይሆናል።

እንዳሉት ችግሩ በየጊዜው ጊዜ ጠብቆ የሚከሠትና የታወቀ ከሆነ፤ ድንበር አካባቢ የሚኖረውን ማኅበረሰብ ደኅንነት ከመጠበቅና ከሉዓላዊነት አንጻር የፌዴራል መንግሥት ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?
የድንበር ጉዳይ ሲነሳ የአገር ጉዳይ ነው። ድንበር ተሻግሮ ወደ አገር መግባት የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው። በፌዴራል መንግሥት አሁን እየተሠሩ ያሉ ጥሩ ሥራዎች አሉ። አንደኛ በድንበሮች አካባቢ የፌዴራል ፖሊስ ማስቀመጥ፤ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚሄደው መንገድ ላይም የፌዴራል ፖሊስ አለ።

ይህ እንዳለ ሆኖ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያዋስነው ድንበር ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ ነው። ሰፊ ነው ይህ ደንበር፣ በወታደርም ማስጠበቅ የማትችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው። መንገዶች በፌዴራል መንግሥት እየተጠበቁ ነው፣ እሱ ምንም ችግር የለውም፤ ድንበሩን በሙሉ ማስጠበቅ ሊያስችግር ይችላል።

አስቸጋሪ ስለሆነ የፌዴራል መንግሥት ችግር ነው የምንለው ነገር አይኖርም። መሆን ካለበት በዋናነት እነዚህ ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ የፌዴራል ኃይል ከእኛ ጋር ቅርበት ይኑረው ነው። በ2008 የተደረገው ጥሩ ‹ኦፕሬሽን› ድንበር አቋርጠው የተወሰዱ ሕጻናትን እስከማስመለስ ደርሷል፤ ይህ ትልቅ ሥራ ነው። ቀላል ነገር አይደለም፤ ለወደፊትም እነዚያን ዓይነት ኦፕሬሽኖች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጥያቄ የምናቀርብ ይሆናል።

በአሁኑ ሰዓት ግን እንደ ጥያቄ ብለን አላየነውም። ምክንያቱም እነዚህ ሙርሌዎች በአብዛኛው በብዛት በቡድን ተደራጅተው አይደለም እየተንቀሳቀሱ ያሉት። ወይም በየቡድኑ ትንሽ ቁጥር ያላቸው ናቸው ሲመጡ። ግፋ ቢል 30 ናቸው፤ ግን አምስት፣ ስድስት፣ ተከፋፍለው ነው የሚመጡት።

ስለዚህ በቡድን አንድ ካምፕ ውስጥ ቢሆን ኖሮ፣ በመከላከያ ማጥቃት ይቻላል። በአሁኑ ሰዓት ግን በመከላከያ ማጥቃት የማይቻልበት ሁኔታ ላይ ነው ያሉት። ምክንያቱም እንዳልኩት ጥቃቅን ቡድኖች ናቸው የሚመጡት። ስለዚህ በአሁኑ ስዓት የመከላከያ ወይም ሌላ ኃይል መምጣት አለበት ብለን የምናስበብት ጊዜ አይደለም።

የመፍትሔ ሀሳብ የሚሆነው ምንድን ነው ከተባለ፣ እኛም አሁን የመፍትሔ አካል ሊሆን ይችላል በሚል እየሄድንበት ያለው ትልቁ ነገር፣ እዚህ አካባቢ ያለውን ሚሊሻ ማሠልጠን ነው። ዛሬ ከ900 በላይ ልዩ ኃይል አስመርቀናል። ከዚህ በላይ መሔድ አይቻልም። ቀድሞ እንደጠቀስኩት በኋላ ምናልባት ከአቅም በላይ የሚሆን ችግር ካለ ፌዴራል እንዲገባ መጠየቅ ይቻላል። ግን ያለው ጊዜያዊ መፍትሔ በክልሉ ውስጥ የጸጥታ ኃይል አደራጅተን በውስጥ ለውስጥ መከላከል የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ነው።

ምናልባት ከፌዴራል የምንጠይቀው ጥያቄ ቢኖር ምንድን ነው፣ እነዚህ የሚመጡ ታጣቂዎች ርቀት ያላቸው መሣሪያዎች ይይዛሉ። እኛ ጋር ግን የእኛ ልዩ ኃይል እየተዋጉ ያሉት በክላሽ ነው። የቡድን መሣሪያ ብዙ የለም። በክልሉ መንግሥት አቅም መግዛት የሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለም ያለነው። ምናልባት ይሄ ድጋፍ ካልሆነ በቀር በቂ ኃይል አለ።

እንደው ይቅርና እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ድንበር ጥሰው የሚገቡትን፣ ካሉበት ቦታ ራሱ ለማጥቃት ዝግጅት ቢደረግ እስከዚያ የምንሄድበት አቅም አለን። ግን የቡድን መሣሪያዎች አለመኖራቸው፣ ሌሎች ‹ሎጂስቲክሶች›፣ በተለይ ወታደራዊ ሎጂስቲክሶች አለመኖራቸው ታሳቢ ተደርጎ በፌዴራል ኃይል ከተሟላልን፣ ሌላ ኃይል ማምጣት ምን ያስፈልጋል? ትልቁን ኃይል መጠቀም የምንችልበት ሁኔታ አለን።

በዋናነት ግን የድንብር ጉዳይ እስከሆነ ድረስ፣ ይሄ ድንበር የአገራችን የኢትዮጵያ ድንበር ነው። ስለዚህ ፌዴራል መንግሥት ዳግም እንዳይመጡ የተጀመረውን ሥራ ማጠናከር አለበት፤ ተጀምሯል ግን ማጠናከር ያስፈልጋል። በሚገባው ልክ ከጠነከረ ምንም ችግር ይሆናል ብዬ የማስበው ነገር አይኖርም። አገራችን ሠላም ይሆናል፤ መጠበቅም የጋራ ኃላፊነታችን እስከሆነ ድረስ ከፌዴራል መንግሥት ጋር እንደ ክልል መንግሥት እኛም ኃላፊነት ስላለብን በጋራ እንሠራለን።

በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ራሳቸውን እንዲከላከሉ የምታደርጉት እንዴት ነው?
ያልታጠቀው ሰው ራሱን ይከላከላል ማለት ያስችግራል። በመረጃ ማገዝ ካልሆነ በቀር እነዚያን ሁሉ ለመከላከል አቅም አይኖራቸውም። ተከላከሉ የምንለው ግን፣ አንደኛ ከአካባቢው ሚሊሻን በማሠልጠን እነዚህ ያሠለጠንናቸው ሚሊሻዎች መሣሪያ ተሰጥቷቸው ጊዜያዊ ሆነው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ ነው። በአንድ ቀበሌ ውስጥ ከ10 በላይ የሚሆኑ ከዚህ በፊት በመከላከያ ተሳትፈው ልምድ ያላቸው ሰዎች አሉ።

ኹለተኛ ደግሞ አቅማቸው ለዚህ የደረሰና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሥልጠና ወስደው፣ ከሥልጠና በኋላ የሚያስፈልጋቸው ወታደራዊ ሎጂስቲክስ ተሟልቶላቸው ወደ ኦፕሬሽን እንዲገቡና ራሳቸውን እንዲከላከሉ ነው የምናደርገው። ተወርዋሪ የሚሆነው ደግሞ የክልሉ ልዩ ኃይል ነው። የክልሉ ልዩ ኃይል የታጠቀ ኃይል ስላለ፣ በዚህ አካባቢ ማንኛውም ችግር ሲኖር ወይም ሲያጋጥም የሥጋት ቀጠና እየለየ አፕሬሽን የሚሠራበት ሁኔታ አለ፤ ይኖራል።

ከዚህ ቀደም እንደሠማነው በታጣቂዎች ጥቃት ከዘጠኝ ሺሕ በላይ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። የተፈናቀሉ ዜጎች አሁን ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
ደንብር ላይ ያሉ ቀበሌ የሚኖሩ ሰዎች የተፈናቀሉበት ሁኔታ አለ። በሥጋትና ችግር ደርሶባቸው የተፈናቀሉ ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ቀጣይነት ያለው ሥራ ያስፈልጋል። በተለይ አካባቢው ሠላም እንዲሆን። ሠላም የሚረጋገጠው በአንድ ጊዜ አይደለም፤ ዛሬም ነገም፣ ከነገ ወዲያም ሠላም ሲሆን ነው ሰው ሠላም ሆኗል ብሎ ራሱን የሚያረጋጋው።

ድንበር አካባቢ ሥጋት ያለባቸው ሰዎች ወደ መሃል እንዲጠጉ ተደርጓል። ለእነዚህ አሁን ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ያስፈልጋል። ቀደም ብሎ የተፈናቀሉትን ደግሞ ተረጋግተው ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱና የራሳቸው ሚሊሻ መድበው ራሳቸውን እንዲከላከሉ አድርገናል። በፊት ከ22 ሺሕ በላይ ሰው ተፈናቅሏል የሚል ሪፖርት ነበር የምናቀርበው፣ በአሁኑ ሰዓት ግን ያን ያክል አይደለም። በሙርሌ ሥጋት ምክንያት ተፈናቅለው ወደ ቀያቸው ያልተመለሱ አሉ፤ አብዛኛው ግን ተመልሷል።

በታጣቂዎቹ ንብረታቸው የተዘረፈባቸውና ቤተሰቦቻቸውን ያጡ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መልሶ የማቋቋም ሥራስ እየተሠራ ነው?
ከዚህ በፊትም እንደ ክልል እንደውም በደንብ ያልሠራንበት ጉዳይ ቢኖር ይሄ ነው። በተለይ ቤተሰብ በሙሉ ተገድሎ አንድ ሕጻን ልጅ ብቻ የቀረበት ቤት አለ። ያው ተወስደው በኋላ የሚመለሱ ሕጻናትም አሉ። አስቀድሞ የጠቀስኳቸውት 109 ሕጻናት አሉ ለምሳሌ። እነዚህ አሁን በአካባቢው ኅብረተሰብ ከዚህ በፊት መንግሥት ጥቃቅን ዕርዳታ እያደረገ፣ የሲቪል ማኅበራት በተለይ የልማት ማኅበራት ዕርዳታ እያደረጉላቸው ነበር። ሙሉ ሕይወታቸውን ለመደገፍና ለመካስ ግን በመንግሥት በኩል የተሠራ ሥራ አልነበረም።
ሌላው ተማሪ ለሆኑት የትምህርት ቁሳቁሶች ናቸው ድጋፍ የሚደረጉት። ልጆቹ በአሁኑ ሰዓት ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከእናቶቻቸው ዘመድ በሕይወት ያለ/ያልሞተ ካለ ከእነርሱ ጋር ነው የሚኖሩት።
ከብቶቻቸውም ተወስደውባቸው የመተካትና መልሶ የማቋቋም ሥራም ከዚህ በፊት አላየንም። ይሄ ሥራ በመንግሥት አልተሠራም። የፌዴራል መንግሥትም ሥራ አልሠራም።

ስለዚህ ወደፊት ትልቅ ሥራ ሊሠራበት የሚገባ ነገር ነው። በቅርብ ጊዜ ደቡብ ሱዳን ላይ ያሉ ኃይሎች ሲዋጉ በእኛ በኩል የአራት ቀበሌ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ አራት ቀበሌዎች ወደ ዘጠኝ ሺሕ 591 አካባቢ ሰዎች ተፈናቅለዋል። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ስዓት በአጎራባች ቀበሌዎች ነው የሚገኙት፤ ወደ ቦታቸው ለመመለስም መንግሥት እየሠራ ነው።

ከተለያዩ ደጋፊ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር በቅርብ ጊዜ፣ መሠረታዊ ፍጆታ ተሟልቶላቸው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ሥራ እየተሠራ ነው። እንደ ረዥም ጊዜ ግን እንደ መንግሥት የቤት ሥራ አድረገን መውሰድ ያለብን ጉዳይ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here