የጉራፈረዳ ነዋሪዎች በግድያ እና ዝርፍያ እየተሰቃዩ መሆኑን ገለፁ

0
524

ሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ግድያ እና ዝርፍያ ህዝቡን ምሬት ውስጥ መክተቱ ተገለፀ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንነታቸው ያልታወቁና በቡድን በሚንቀሳቀሱ ታጠቂዎች ተደጋጋሚ ትንኮሳ፣ የከብትና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ እየተፈጸመ እንደሚገኝ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ ካሉ ስድስት ቀበሌዎች ውስጥ አንዱ በሆነው ኩጃ ቀበሌ ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋጋሚ የከብት ዝርፊያ እንዲሁም በነዋሪዎች ላይ ግድያ እየተፈጸመ መሆኑን የቀበሌው ነዋሪ የሆነው ግለሰብ ተናግሯል፡፡

ስለጉዳዩ የሬዲዮ ጣቢያው የጠየቃቸው የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መመርያ ኃላፊ ተስፋይ ጊስካር፤ ለጸጥታው መደፍረስ በዋናነት በቀበሌዋ ከፍተኛ የሆነ ህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውርና ሽያጭ መበራከት ዋናው ምክንያት ነው ያሉ ሲሆን፤ እንዲህ ያለውን ድርጊት ህብረተሰቡ በአንድነት አለመታገሉ ደግሞ ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንነታቸው ያልታወቁና ታጥቀው በቡድን በሚንቀሳቀሱ አካላት ተደጋጋሚ የከብትና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ እየተካሄደ ሲሆን ንጹሀን ላይ ደግሞ ግድያ እየተፈፀመ ነው ሲሊ ተስፋይ አረጋግጠዋል፡፡

ቀበሌዋ ለጋምቤላ ክልል አኙዋክ ዞን ዲማ ወረዳና ምዕራብ ኦሞ ዞን አዋሳኝ በመሆኗ ከዚህ ቀደም ከሱርማ ወረዳ አካባቢ ተነስተው በሚመጡ ሽፍቶች የከብት ዝርፊያ ይፈጸም እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አሁንም ያለው ከዚሁ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የተናገሩት ኃላፊው፤ ዝርፍያው እና ግድያው የሚፈጸመው ጨለማን ተገን አድርገው በሚንቀሳቀሱና በጫካ የሚደበቁ ሰርጎ ገብ ታጣቂዎች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በትላንትናው ዕለትም በጉራ ፈርዳ አንድ ግለሰብ በሽፍቶች እንደተገደለ እና ከብቶቹም እንደተዘረፉበት ነው ተስፋዬ የተናገሩት፡፡

አሁን በኩጃ ቀበሌ ለሚታየው የጸጥታ መደፍረስ ህብረተሰቡና የወረዳው ጸጥታና ፖሊስ መዋቅር ወንጀልን በጋራ ለመከላከል የሚያደርገው ቅንጅት አናሳነት ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ በጉያው የተመሸጉ ህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ነጋዴዎች ፣ ደላላዎችና አስተላላፊዎችን ለህግ አካላት አሳልፎ እስካልሰጠና ተደራጅቶ ወንጀልን እስካልተከላከለ ድረስ መሰል የጸጥታ ችግሮች በፖሊስና በጸጥታ መዋቅሩ ሥራ ብቻ የሚፈቱ አይሆኑም ብለዋል፡፡

በቀጠናው ከፍተኛ የጦር መሳሪያና የጥይት ፍሬ ዝውውርና ሽያጭ የሚፈጸምበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ኃላፊው ገልጸው፤ የወረዳው የጸጥታ መዋቅሮች ችግሩን ለመፍታት ከህዝቡ ጋር እየመከርንበት እንገኛለን ሲሉም ለሬዲዮ ጣቢያው ተናግረዋል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here