ሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን ሳይጨምር በየካቲት ወር 2014 ለ46 ሺህ 603 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት የካቲት ወር አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር በ15 ሺህ 768 ብልጫ አሳይቷል ተብሏል፡፡
19 አዳዲስ የገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተገልጿል፡፡
በየካቲት ወር በአጠቃላይ 1 ሺህ 229 ለሚሆኑ ዜጎች በፕሮጀክትና በመደበኛ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር መደረጉንም ተጠቅሷል፡፡
ተቋሙ ሁሉም የድህረ-ክፍያ ደንበኞቹ የተጠቀሙበትን ወርሃዊ የኤሌክትሪክ የፍጆታ ሂሳብ ከተቋሙ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በተጨማሪ ባሉበት ቦታ ሆነው በቴሌ ብር፣ በCBE ብር፣ በኢንተርኔትና በሞባይል ባንኪንግ እንዲከፍሉ ማስቻሉ አስራርን ቀልጣፋ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩም ተገልጿል፡፡
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሉ 5 የክፍያ አማራጮች አማካኝነት በመጠቀም የሚከናወነው ክፍያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ ከአጠቃላይ የክፍያ መጠኑ 27 በመቶ መደረሱም ተመላክቷል፡፡
ይህ ቁጥር አሁንም አነሰተኛ በመሆኑ አሁንም ደንበኞች በተዘረጉ ዘመናዊ የክፍያ አማራጮች ተጠቅመው ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳባቸውን በቀላሉና ባሉበት ቦታ እንዲከፍሉ ተጠይቋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ችግር፣ በአንዳንድ ክልሎች የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ውድመት፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች አቅርቦት መዘግየት በወሩ የተስተዋሉ ዋና ዋና ማነቆዎች መሆኑን መጠቆሙን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



