እኛ ማለት…

0
789

እንደማኅበረሰብ ብዙ ተቃራኒ ድርጊቶችን እንደምንናገር እና እንደምናደርግ የታዘቡት ዳግማዊ ሲሳይ፣ በዚህ ወግ የተሞላ መጣጥፋቸው የተናገርናቸው እና ያላደረግናቸው፣ የተናገርናቸው እና የተቃረንናቸን ታሪካዊ ኩነቶች እያጣቀሱ “እኛ ማለት…” እንዲህ ነን ይላሉ።

 

 

በአክሱም ሥልጣኔ የምንንቀባረር፣ በአድዋ ድል የምንኮራ፣ በቀደምት ቅኝ አልተገዛንም ባይነት የምንጀነን፣ ከጥቁሮች ሁሉ በላይ ነን የምንል፣ አብረን ለመብላት ብቻ የተፈጠርን የሚመስለን፣ አብረን ለመሥራት ያልታደልን፣ ለዘመናት እጅና እግራችንን አጣጥፈን የተቀመጥን፦
“አባይ ሥም ነው እንጂ ምን ጠቅሟል ለአገሩ፣
ትርፉ ለሌላ ነው ብዙ መገበሩን”
በኩራት ስንዘፍን የከረምን፤
“አባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል”ን የሸመደድን፣

እኛ ማለት…
ከአንድ እስከ ሠላሳ ታቦታትና ፃድቃንን እየዘከርን፣ ከሥራ የተፋታን፣ “አዳም በላብህ በወዝህ…” የሚለውን ቀዳሚ ትዕዛዝ የጣስን፣ በአቋራጭ ለመክበር ቆረጣ የሚቀናን፣ ለውጭ ተርቦች ለውስጥ ጉንዳኖች የሆንን ፍጥረቶች፣ ”ከፍጥረታት ሁሉ የመጀመሪያዋ ሉሲ ኢትዮጵያዊ ነች” የሚለውን የተቀበልን፣ ዝንጀሮነታችንን ያመንን፣ ያሳመንን፣ በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያዊነታችንን ከመጽሐፍ ቅዱስ አርባ ጊዜ ጠቀሳ በላይ እያሞገስን ሰውነታችንን ያደመቅን፣ ሳይንስን በሃይማኖት፣ ሃይማኖትን በሳይንስ ያጣፋን፣ ንጉሥ ገድለን ቀብረን በላዩ ላይ ቤት የሠራን፣
“በኃይሌ ጊዜ ወልጄ ወልጄ፣
በመንጌ ጊዜ ምን ላብላው ለልጄ”
የሚለውን የተቀኘን።
ስድሳ ሰውን በአንድ ጉድጓድ አነባብረን፣ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም”ን ያዜምን።
እኛ ማለት…
በትናንት ውስጥ ትናንትን፣ በዛሬ ውስጥ ትናንትን፣ በነገም ውስጥ ትናንትን ብቻ የምናይ የምንመስል። ትናንትም ዛሬም ነገም ሊያመልጠን ትንሽ ብቻ የቀረን። ለመያዝ የምንሳደድ፣ በመዛል ውስጥ የምንሮጥ፣ ገዳይ ነው ያልነውን ገድለን፣ ተርፏል ያልነውን ጨርሰን፣ ደብዛውን ያጠፋን። እንግሊዘኛ ቋንቋን መግባቢያ ሳይሆን የዕውቀት መለኪያ አድርገን፣ በ‘is’ እና ‘was’ መካከል ያለው ድንበር የሚያደናግረን፤ ልክ ‘See you last night’ ወይም ‘ልመጣ ሔጃለሁ’ ዓይነት ድንግር ውስጥ ያለን፣ ግዕዝን፣ ንባብና ውርድን እስከታች ያልዘለቅን በ“What’s up” ግን የሰከርን።
እኛ ማለት…
ሱሪን ከፍና ዝቅ አድርጎ በመታጠቅ መካከል ያለው ልዩነት ብዙም ግድ የሌለን፣ ጠይቀን ለመረዳት፣ ተምረን ለማወቅ፣ ዐውቀንም ለመጠንቀቅ ጊዜ የሌለን፣ ፌስቡክና ካንዲ ክራሽ ዓይናችንን ያጥበረበረን፣ የልጃችንን ዳይፐር ለመቀየር ጨዋታችንን ለአፍታ ማቆም የከበደን፣ በጉብዝናችን ወራት ጡረታችን የሚያሳስበን፣ ዛሬን የምንሠራው ነጋችንን የተሻለ ስለማድረግ መሆኑ በቅጡ ያልገባን፣ አዲስ ነገር ለመጀመር ድፍረቱ ብዙም የሌለን፣ አገራችንም ሆነን ከአገራችንም ወጥተን በዘረኝነት ገመድ የተተበተብን፣ ከምንኖርበት አገር ሥልጣኔ በትንሹም ያልጨለፍን፣ ከርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነት ይልቅ አጥንትና ጉልጥምት መቁጠር የሚቀናን፣ መሸት አድርገን አንድ ምዕራፍ መጽሐፍ ከማንበብ ይልቅ፣ ንግት አድርገን እስከ ጠዋቱ ስድስት ሰዓት መቀምቀም የሚያስደስተን፣
ታላቁ ባለራዕዩ መሪያችን ያልነውን አድዋ ቀብረን ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሐውልት የምናስጠብቅ (ሐሜት ነው)፣ በሕይወት እያለን ለመወቃቀስና ለመማማር ያልታደልን።
እኛ ማለት…
በብቸኝነት መቶ ፐርሰንት ፓርላማ አሸንፈን አውራ ፓርቲ የሆንን ግን ደግሞ በአውራ ችግሮች የተተበተብን፣ ለበጎ ምግባር ሞተን ሳይሆን በክፋት ገድለን የምንፎክር፤ቀድመን ከመተባበር ይልቅ ወህኒ ስንቅ ማቀበል የሚቀናን፣ እኛው ራሳችን ድራሹን አጥፍተን አብረን ለፍለጋ የምንወጣ፤ከአስር ስኳር ፋብሪካ አንድ ገንብተን ላማስመረቅ መንገድ የምንዘጋ፣በወርቅ ስም ባሌስትራ የምንመዝን፣እስር ቤት ውስጥ ዋይፋይና ላፕቶፕ የለንም ብለን ፍርድ ቤትን የምንጠይቅ፣የምድሩ መጨናነቅ ሲያስቸግረን አለምንም ሀፍረት አውሮፕላን የገዛን፤ ደራሲው እንዳለው “ገዳይ ሲባል አቤት ሟችም ሲባል አቤት” የምንል ወይም ያልን፤
እኛ ማለት…
ተራሮችን አንቀጠቀጥን ያልን ትውልዶች በተራ ብዕረኛ ተሸብረን ምድረ ጋዜጠኛን ተከርቸም ያከረምን፣ በሕልም ዓለም ሺሕዎችን የቀለብን፣ በምኞት ፍሪዳ የጣልን፣ ጮማ ያስቆረጥን፣ ውስኪ የተራጨን፣ ሲነዱን የምንነዳ፣ ለምን ብለን የማንጠይቅ፣ በመንጋነት የምንጓዝ መድረሻችንን ያላወቅን።
የለም፣ የለም ይህ የእኛ ታሪክ ሌላኛው ገጽ ነው፣ የተረሳ ወይም ተቀዶ የተጣለማ ሌላ ገጽ አለን።
እኛ ማለት…
በአፍሪካ የመጀመሪያዎቹን የረዥም ርቀት ሴት አትሌቶች ለዓለም ያስተዋወቅን፣ ደራርቱና ፋጡማ ሺሕ ሜትሮችን በእግራቸው እየጠቀለሉ፣ በአንገታቸው ወርቅ ሲያጠልቁ፣ ሰንደቅ ሲያውለበልቡ አብረን የደስታ ሳግ የያዘን። እልፎች የቀኑበትን ከየትኛው ፕላኔት ነው የመጣው የተባለውን የዓለምን ክብረ ወሰኖችን በመሰባበር ጉድ ያስባለውን ኃይሌን በትውልዳችን የተጋራን፣ ጀግኖቻችንን አክብረን ያልጠገብን፣ በዓለም መድረክ ላይ ያገዘፍናቸውን በጓሮ በር “አስጠንቁለው እኮ ነው፣ ውይ ገብጋባ ነው” እያልን የቦጨቅን፣ በቴዲ አፍሮ ዜማ ፍቅር፣ አንድነት፣ ተስፋ፣ ትንቢት የተነገረን፣ በማመንና ባለማመን መሐከል የተወጠርን።
እኛ ማለት…
የተጠላውን “ኢትዮጵያዊነት” ወይም “አንድ ሕዝብ አንድ ኢትዮጵያን” ከታማኝ ጋር ያስተጋባን፣ ይህንንም ለማየት የታደልን፣ በፍቅርና ይቅር ባይነት ግዞተኞች ነጻ ሲወጡ ለመመልከት የቻልን፣ ብልት ላይ ውሃ ማንጠልጠል፣ ጥፍር መንቀል፣ ዕርቃን ሰውነትን ባዶ ሲሚንቶ ላይ ያሳደርን፣ ሰውን የሚያክል ሕያው ፍጡር ቀጥቅጠንና ዘቅዝቀን ከእነ ሕይወቱ የሰቀልን፣ የገደልን፣ የአረመኔነት መጀመሪያንም መጨረሻንም እንደምናውቅ ለዓለም ያሳየን፣ ታሪካችን ሁሉ የጦርነት፣ የግደለውና ፍለጠው፣ “የእናሸንፋለንና፣ እናቸንፋለን” የሆነ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማምጣት ነፍጥ አንስተን ጫካ የምንገባ፣ ከንግግር ይልቅ ጥይት ማጮህ የሚቀድመን።
የለም… የለም… ኢትዮጵያ እኮ በፋሲል ግንብ የጥንት ኪነ ሕንፃ የምትኮራ፣ በአክሱም ሐውልት ሽቅብ የምትንጠራራ፣ በነጃሺ መስጊድ ስለ ሃይማኖት እኩልነት የምትሰብክ፣ በአባይ ወንዝ ትልቅነት የምትኮፈስ፣ በልማታዊነቷ የምትኮራ፣ ሚሊዮንና ቢሊዮን ብሮች እንደቀልድ በተረት መልክ የሚነገርባት የሆነች የተረት አገር የምትመስል ‘ኢትዮጵያ’!!! በቃ ሰውየው እንዳለው ታሪካችን ሁሉ የበሬ ይሆን እንዴ?
“በሬ መብላት፣ በሬ መልበስ፣ በበሬ ማረስ፣ ስለበሬ መዝፈን፣ አንድ በሬ ከነበረን ሁለትና ሦስት ማድረግና ማብዛት…
እኛ ማለት…
በይቅርታና መደመር የተደመርንና ያልተደመርን፣ ምሕረትንና ማለፍን ለዓለም ያሳየን፣ ልዩነትንና መቻቻልን ከየት መጀመር እንደሚቻል የሰበክን የተሰበክን፣ በጎደሉት እስር ቤቶች ተረኞችን ማስገባት የጀመርን በአንድ ጉዳይ ኹለት አቋም ይዘን ብቅ ያልን፣ “ብሩ ጠፋ፣ ብሩ ተበላ፣ የቀን ጅቦች ወረሩን” ባልን ማግስት፣ የስኳር ፋብሪካ ያስመረቅን፣ የኢንዱስትሪ መንደር ሥራ ያስጀመርን፣ኻያ አምስት ሚሊየን ተጓዦችን በዓመት ማስተናገድ የሚችል የመንገደኞች ተርሚናልን በኩራት የመረቅን፣ ከኢሱ ጋር በፍቅር እፍ ያልን።
እኛ ማለት…
አንድ እንሁን አንድነት ይጠቅማል እያልን፥ የጎጥ ጥጋችንን ይዘን የምንባላና የምንባጠስ፣ የታሸገ ውሃ ይዘን በሸገር ጎዳናዎች የተንጎማለልን፣ ወገብ ጨበጥ አድርገን በየምሽት ክበቡ የደነስን፣ አንድ ቦታ ስጋ ቤት ሲከፈት ከጎኑ ዳጣና አዋዜ ቤት ከመክፈት ይልቅ የስጋ ቤት ፉክክር ውስጥ የገባን፣ በርበሬን ከሸክላ፣ ቅቤን ከሙዝ፣ የጤፍ ዱቄትን ከጀሶ የምንደባልቅ፣ ጠዋት ጠዋት ቤተክርስቲያን፣ ቀን ቀን ጥንቁልናና ሀሜት፣ ማታ ማታ የግሮሰሪ ወንበር አሟቂ ዘመነኞች ወይም የዘመን ጉዶች።
እኛ ማለት…
በቅን ዕሳቤና በመጥፎ ዕሳቤ እንዲሁም በሕያሴ ዕሳቤ መካከል ያለው ልዩነት ያልገባን፣ የፌስቡክ አርበኞች፣ አውሮፓና አሜሪካ ቁጭ ብለን ሸገር ድንጋይ የምናስወረውር፣ የምናዋጋና የምናባላ፣ ሁሉም የፖለቲካ ተንታኝ፣ አክቲቪስታና ተንታኝ። እውነት ግን እኛ ማነን? ምንድንስ ነን? ምንስ ነን?

ዳግማዊ ሲሳይ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው sisaydagemawi@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here