የማረሚያ ቤቱ ሰርግ

0
663

በኢትዮጵያ ለወትሮው ሰርግን በማረሚያ ቤት ሆኖ መከወን ለጆሮ እንግዳ ለዐይንም ባዳ ነው። ይሁን እንጂ ለ14 ዓመታት ያለመታከትና ማቋረጥ ፍርደኛ ፍቅረኛዋን በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እየተመላለሰች ስትጠይቅ ነበር የተባለችው የፍቅር ተምሳሌቷ በሳምንቱ መጨረሻ የፍቅር ጓደኝነቱን ወደ ትዳር ከፍ ለማድረግ በቅታለች። ከዚህ በላይ ዓመታትን በፍቅር የሚቆዩ አሉና ብርቅ ነወ ውይ? ለሚሉ ግን ብርቅም ድንቅም ያደረገው ሰርጉ በማረሚያ ቤት መከወኑ ነው።

እንስቷ በሕግ ጥላ ሥር ውሎ ለዓመታት ማረሚያ ቤት የሚገኘውን ፍቅረኛዋን ስትጠይቅ ኖራለች። እሱ ደግሞ ዛሬም የእስር ጊዜውን ባለመጨረሱ ማረሚያ ቤት ነው። ታዲያ ኹለቱ ፍቅረኞች (የአሁኑ ሙሽሮች) ትዳራቸውን ለመፈፀም ወስነዋል። በዚህም በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የካቲት 10/2011 ረፋድ ሰርጋቸውን ፈፅመው የበርካቶችን ትኩረት ስበዋል።

የማረሚያ ቤቱ ሰርግም በብዙ የማኅበራዊ ትስስር ገፆች ሲንሸራሸርና የ‹‹መልካም ትዳር ዘመን ይሁንላችሁ!›› ምኞትን ሲያስተናግድ ሰንብቷል። የሃይማኖት አባቶችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም የሰርጉ ድምቀት ሆነው ታይተዋል።

የሰርጉን ወጪ የቻሉት በአንዲት ሴት ላይ አሲድ በመድፋት ወንጀል ተፈርዶባቸው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚ ናቸውም ተብሏል።

ታራሚው ልጅቱ ላሳየችው የፍቅር ፅናት ከገንዘብ ስጦታ ባሻገር የቤትና የመኪና ሽልማት ለማበርከተትም ቃል ስለመግባታቸው ተሰምቷል።

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በ2005 በታራሚዎች ዘንድ ተመሳሳይ የሰርግ ሁነትን ስለማስተናገዱ መረጃዎች ያሳያሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here