ሐሙስ መጋቢት 15 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የኦሮሚያ ክልል፡- የከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ላይ ለተፈጸመው ግድያ የወንጀል ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ ላይ ክፍተቶችን መመልከቱን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ “የእርቅ ሂደቱ የወንጀል ተጠያቂነትን መተካት ወይም ማስተጓጎል የለበትም” ሲልም አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በመግለጫው፤ የከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ላይ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት ጥር 25 ቀን 2014 ይፋ በማድረግ፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በጅላ አባላቱ ላይ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ አባላት ላይ ተገቢ የሆነ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና ለተጎጂ ቤተሰቦች ተገቢ የሆነ ካሳ እንዲከፈላቸው ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ አስታውሷል፡፡
ይህንኑ የኮሚሽኑ ጥሪ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን በመመርመር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን ጥር 25 ቀን 2014 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማሳወቁንም ገልጿል።
ይህንኑ መሰረት በማድረግ ኮሚሽኑ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 3 ቀን 2014 ክትትል ያደረገ ሲሆን፤ በክትትሉም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ፣ ግድያውን ለመመርመር የተዋቀረውን የምርመራ ቡድን እንዲሁም የከረዩ ማኅበረሰብ የአገር ሽማግሌዎችን ማነጋገሩን ገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት በአንድ በኩል የተፈጸመውን ግድያ ለመመርመር ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ መርማሪ ቡድን ተቋቁሞ ሥራ የጀመረ መሆኑን ለመረዳት መቻሉን አስታውቋል፡፡
በሂደቱም እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ድረስ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኝ መሆኑን ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎቹ የሚገኙበትን የማቆያ ቦታ በመጎብኘት አረጋግጫለሁ ብሏል።
ኢሰመኮ የክልሉ መንግሥት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የተሻለ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ክፍተቶችንም መመልከቱን ገልጿል፡፡
በአንድ በኩል በአካባቢው ማኅበረሰብ በግድያው ላይ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን የተጠቆሙ፣ አልያም በድርጊቱ ዋነኛ ፈጻሚ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ገና በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ወይም ምርመራ እየተደረገባቸው አለመሆኑን ምክንያታዊ አሳማኝ ሁኔታዎችን ኮሚሽኑ መገንዘቡን አስታውቋል።
ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ ጭምር ያሉ በመሆናቸው በምርመራ ሂደቱ ላይ ጫና እያደረሱ መሆናቸውን ወይም ለሂደቱ አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ የሚገባቸው የፀጥታ እና የአስተዳዳር አካላትም ሥራው በሚፈለገው ፍጥነት እንዲጠናቀቅ በቂ ትብብር እያደረጉ እንዳልሆነ ተዓማኒ የመረጃ ምንጮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የምርመራ ሂደቱን በተመለከተ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ መሆኑን ኮሚሽኑ መረዳቱንም ገልጿል፡፡
የክልሉ መንግሥት ኮሚዩንኬሽን ቢሮ መጋቢት 13 ቀን 2014 በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ እየተካሄደ ካለው የወንጀል ምርመራ ሥራ ጎን ለጎን በኦሮሚያ ክልል የአባገዳዎች ምክር ቤት አስተባባሪነት በክልሉ መንግሥት እና በከረዩ ማኅበረሰብ የአገር ሽማግሌዎች መካከል ሽምግልና እየተካሄደ መሆኑን ኢሰመኮ ተረድቷል፡፡
መንግሥት በሕዝቡ ላይ የተፈጠረውን ቅሬታ በእርቅ እንዲፈታ ጥረት ማድረጉ ተገቢ ቢሆንም የእርቅ ሂደቱ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ሊያስቀር ስለማይችል የሕግ ተጠያቂነት ሂደቱ ሊደናቀፍ አይገባም ሲልም ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
አክሎም ተጠያቂነትንና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወሰዱ የሕግና የወንጀል ምርመራ እርምጃዎችን በአካባቢዎች ባሕልና ልማድ መሰረት በሚደረጉ የእርቅ ሂደቶች መደገፍ በአንዳንድ ሁኔታዎች የተለመደ ሂደት ቢሆንም፣ የዚህ አይነቱ አሰራር በተጎጂዎች፣ በተጎጂዎች ቤተሰቦችና በአካባቢው ማኅበረሰብ ሙሉ ፈቃድና ተሳትፎ ሊሆን ይገባል ብሏል።
ኢሰማኮ ይህን መሰል ሂደቶች በአካባቢው ማኅበረሰብ የሕግ ተጠያቂነትን ለመተካት አልያም ለማስቀረት የሚደረግ መሆኑን የሚያመላክት ቅሬታ ካለ ከጥቅሙ ይልቅ አሉታዊ ተጽዕኖው ሊያመዝን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሻል ሲልም አሳስቧል።
ስለሆነም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የተጎዱትን መካስ፣ ዕርቅና ሰላም፣ ፍትሕና ተጠያቂነት በአንድነት ሊተገበሩ የሚችሉና የሚገቡ በመሆናቸው፣ የመንግሥት ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ለዚህ አይነት የተሟላ ዕርቅ፣ ሰላምና ፍትሕ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል” በማለት አሳስበዋል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n





