ሐሙስ መጋቢት 15 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ለኢድ አልፈጥር እና ኢድ አልአድሀ የዳያስፖራ የአገር ቤት ጥሪ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብት፣ ፖለቲካና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ የተከናወኑ ተግባራት ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ዳያስፖራዎች በበቃ እንዲሁም “ሆም ካሚንግ” በሚል የገና እና ጥምቀት በአልን ወደ አገር ቤት መጥተው በተለያዩ ተግባራት ከአገራቸው ጎን መሆናቸውን እንዳሳዩ አውስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመርሀ ግብሩ ወደ አገራቸው ለሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን አስፈላጊው ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።
አምባሳደር ዲና መርሀ ግብሩ ዳያስፓራው በአገራዊ ጉዳይ እንዲሳተፍ እድል ይፈጥራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ቃል አቀባዩ አክለውም በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 የተባሉ ረቂቅ የህግ ሰነዶች እንዳይጸድቅ ለመከላከል፤ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ መንግስት ከአሜሪካ መንግስት ጋር የሰነዱ ጠቃሚ አለመሆን ማስገንዘብ ላይ የማያቋርጥ ተግባር እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




