በሆቴሎች ራሳቸውን አግልለው በተቀመጡ ሰዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር የላላ ነው

Views: 1283

ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ለ14 ቀናት ራሳቸውን በማግለል በሆቴሎች ውስጥ እንዲቀመጡ በተደረጉ እንግዶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር የላላ መሆኑ ተገለጸ። መንግሥት ባወጣው አስገዳጅ ሁኔታ ምክንያት በአዲስ አበባ የተለያዩ ሰባት ሆቴሎች ውስጥ ራሳቸውን አግልለው የሚገኙ ግለሰቦች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በመንግሥት በኩል የሚደረገው ክትትል እና ቁጥጥር የላላ ነው። ከሚደረገው የላላ ቁጥጥር ጋር ተያይዞም ቫይረሱንም ለመቆጣጠር አዳጋች እንደሚያርገው ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልጸዋል።

ለአንድ ወር ያህል በዱባይ ቆይታ አድርገው ማክሰኞ መጋቢት 15/2012 ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የገለጹት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ገና ከጅማሬው በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከፍተኛ እንግልት እንደገጠማቸው ገልፀዋል። አያይዘውም ባረፉበት ኤሊያና ሆቴል ውስጥ ምንም አይነት ጥበቃ እንዳልተደረገ እና ከቀናት በኋላ ኹለት የጤና ባለሙያዎች በመምጣት የሙቀት መጠናቸውን ለክተው እንደሄዱ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

‹‹ምናልባት ቫይረሱ ካለብኝ ቤተሰቦቼን እንዳልበክል በሚል ነው እንጂ፣ ቁጥጥር ባለመኖሩ ወጥቼ ለመሄድ የሚያግደኝ ነገር የለም›› ሲሉም አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዋ ጨምረው እንደገለጹት፣ ከዱባይ አዲስ አበበ በገቡ ጊዜ የተቀበላቸው ሰው እንዳልነበርና የተደረገው ጥንቃቄ የጎደለው መስተንግዶ በበሽታው የተያዘ ሰው አየር መንገድ ውስጥ ወዳሉት ሰዎች ለማስተላለፍ የሚችልበት አጋጣሚው ሰፊ እንደሆነም ጠቁመዋል።

‹‹ብዙ እንግልት ገጥሞናል። ምግብ እንኳን መመገብ አልቻልንም። የነበርንበት ቦታም ዝም ብሎ ሜዳ ላይ ነው።›› የሚሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ‹‹አቅም የለንም። ስለሆነም ሌሎች ዋጋቸው የሚቀንስ እንግዳ መቀበያ ሥፍራዎች አሉ። እናንተ የጤና ባለሙያዎችን መድቡልን። እኛም ራሳችንን አግልለን እንቀመጥ ብንልም የሚሰማን አልነበርም። መንግሥትም ይህን እያደረገ ያለው ገቢ ለመሰብሰብ ነው የሚመስለው እንጂ ቫይረሱን ለመቆጣጠር አይመስልም።›› ሲሉ አስረድተዋል።

በመጨረሻም የተፈቀዱ ሆቴሎች ግዮን፣ ኤልያና፣ ስካይላይት፣ አዜማን፣ ሳፋየር እና ቦን ፕላዛ መሆናቸው ሥም ዝርዘር የተሰጣቸው መሆኑን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ዝቅተኛ ዋጋው የግዮን ሆቴል 60 ዶላር ቢሆንም ቦታው እንደሞላ ስለተነገረን ከ200 ሰዎች መካከል ስምንታችን የመክፈል አቅም ስለነበረን ወደሌላ ሆቴል በማቅናት ራሳችን አግልለናል ብለዋል።

‹‹ሆቴሎቹም ቢሆን የሚያስክፍሉት ዋጋ ከፍተኛ የሚባል ነው። እኔ በግሌ ወደ 32 ሺሕ የሚጠጋ ብር ለ14ቀን ሆቴል ውስጥ ራሴን ለማግለል ከፍያለሁ። መንግሥት እውነት ይህን ካሰበ ብዙ መንገዶች ነበሩት። አሁንም ቢሆን ከቫይረሱ ነጻ የመሆናችን ነገር ገና የሚረጋገጥ ቢሆንም፣ በሆቴሎች ውስጥም ቢሆን ተጋላጭነታችን አልቀነሰም። እንደውም እኔ ከዱባይ እራሴን ጠብቄ ከቤት ሳልወጣ ነበር የቆየሁት። ከዛ ይልቅ ግን ተጋልጫለሁ ብዬ ነው የማስበው።›› ሲሉም ይናገራሉ።
አያይዘውም የአንዳንድ ሆቴሎች ሠራተኞቻቸው ጭምር ራስን ማግለል ወይም ወደ ማቆያ መግባት ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም ሲሉም ስጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ በአዲስ አበባ የሚገኙ ለይቶ ማቆያ አገልግሎት የማይሰጡ የሆቴሎች አስተዳዳሪዎች፣ በሆቴሎቻቸው የማቆያ አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ምክንያታቸው ሲጠየቁም፣ ‹‹መጀመሪያ ራሳችንን እና ሠራተኞቻችንን መከላከል ይቀድማል፤ የሚገኘው ገቢ ይቅርብን።›› ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ-19 የቅድመ ዝግጁነትና ምላሽ አስተባባሪ ዘውዱ አሰፋ በበኩላቸው፣ ክፍተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በማመን ስለሚደረገው ጥንቀቄ አስረድተዋል። በዚህም አንድ ከውጭ የመጣ ሰው እንግዳ መቀበያ ፓስፖርቱን እንዲሰጥ እንደሚደረግ፣ በአየር ማረፊያ ላይ በፖሊስ እንደሚታጀብ እንዲሁም በተለየላቸው መኪና መግባታቸው እንደሚረጋገጥ ገልጸዋል።

ይህ ብቻ አይደለም ያሉት ዘውዱ፣ ሆቴሎቹን በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ በማድረግ እንዲሁም በሆቴሎች ውስጥ ብዙ ሰዎች ሊመላለሱባቸው በሚችሉ ቦታዎች ወይም ኮሪደሮች እንዳይመላለሱ ክትትል እንደሚደረግ፣ እነሱን የሚከታተል የጤና ባለሙያ እንደተመደበም ያለውን ሁኔታ በሰጡት አስተያየት ጠቅሰዋል።
ድንገት የታመመ ሰው እንኳን ቢኖር የአንቡላንስ መኪናዎችን መድበናል ያሉት ዘውዱ፣ ‹‹ይህን እየሠራን እንኳን ክፍተቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ ይህንን ከሚሠራ ቡድን ጋር በጋራ እንሠራለን። ነገሮችን ለማጣራት እንሞክራለን።›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com