አዲስ እየተዘጋጀ ያለው የሚዋጥ የወንዶች የወሊድ መከላከያ እንክብል እርግዝናን በመከላከል ረገድ 99 በመቶ ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ። በዚህም አዲሱ የወሊድ መከላከያ በሴቶች ላይ ብቻ የነበረውን ጫና ያቃልላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
የወሊድ መከላከያ እንክብሉ በአይጥ ላይ በተደረገ ሙከራ እርግዝናን ለመከላከል ውጤታማ መሆኑ እንደተረጋገጠም ነው የተነገረው።
በ‹አሜሪካ ኬሚካል ሶሳይቲ› ስብሰባ ላይ ግኝታቸውን ያቀረቡት ተመራማሪዎች፣ አዲሱ የወንዶች የወሊድ መከላከያ እንክብል ውጤታማ መሆኑን ገልጸው፣ ለዐስርት ዓመታት ያክል በአፍ የሚዋጥ የወንዶች የወሊድ መከላከያ እንክብል ለመፍጠር ጥረቶች የነበሩ ቢሆንም፣ እስካሁን ዕውቅና የተሰጠው መድኃኒት በገበያ ላይ አለመኖሩን አመላክተዋል።
የወንዶች የወሲብ ‹ሆርሞን› ‹ቴስቴስትሮን›ን ኢላማ ያደረጉ በርካታ ‹ክሊኒካል› ሙከራዎች እየተደረጉ ይሁን እንጂ፣ ከልክ ያለፈ የሰውነት ውፍረትን፣ ድብርትን እና ሌሎች የጎንዮሽ ጉዳቶችን የሚያስከትሉ ናቸው ተብሏል።
አሁን የተሸራው የወንዶች የወሊድ መከላከያ እንክብል ከሆርሞን ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑንና በቅርቡ በሰዎች ላይ ሙከራ ማድረግ እንደሚጀመር ተመላክቷል።
ሴቶች እርግዝናን ለመከላከል የተለያዩ መድኃቶችን ከመዋጥ ጀምሮ ማህፀን ውስጥ የሚገቡ መሣሪያዎችን እስከመጠቀም የሚገደዱ በመሆኑም፣ አዲሱ የወሊድ መከላከያ በሴቶች ላይ ብቻ የነበረውን ጫና ያቃልላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
በተቃራኒው ወንዶች ግን ኮንዶምን የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ከዚህ በዘለለ ‹ቫሴክቶሚ› የተባለ እና በቋሚነት እንዳይወልዱ የሚያደርገውን የቀዶ ጥገና አማራጭ ብቻ ነው ያለው።
በወንዶች ላይ ለወሊድ መከላከያ የሚደረገው ቫሴክቶሚ የተባለው ቀዶ ጥገና ሕክምና በዋጋው ውድ ሲሆን፣ ብዙም ስኬታማ እንዳልሆነ ይነገራል።
ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014


