‹አንቱ በእናት› አዲስ መጽሐፍ

0
1637

የመጻሕፍት ገበያው አሁን ወደ ቀደመ መልኩ እያዘገመ ይመስላል። ለጆሮ ርቀው የነበሩ የመጻሕፍት ዜናዎች አሁን ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ‹እገሊት መጽሐፍ አወጣች! የእገሌን አነበብሽው?› ወዘተ. እየተባባሉ መጠያየቅም አሁን እየተዘወተረ ነው። አዳራሾች የመጽሐፍ ምርቃትን ከመርሃ ግብራቸው ዝርዝር መካከል አድርገው በርካታ ቅዳሜዎች የመጽሐፍት ጉዳይ እንዲወራባቸው መድረካቸውን ሰጥተዋል።

ከእነዚህ በቅርብ ሰሞን ለንባብ ከቀረቡ መጽሐፍት መካከል የማሞ አፈታ ‹አንቱ በእናት› የተሰኘው መጽሐፍ ይገኝበታል። በኻያ ምዕራፎች ተበጅቶ በ370 ገጾች ተቀንብቦ የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ፣ 10 ገጾቹ በምስል/በፎቶ የተሸፈኑ ናቸው።
ከመጽሐፉ የመግቢያ ገጾች ላይ በአንደኛው ደግሞ ተከታዩ የመጽሐፉ መታሰቢያ ቃል ይገኛል፤

‹‹በዚህ መጽሐፍ የተጠቀሱትን ገፈት ለቀመሱ፣ አገራቸው፣ የሚወዱት ሕዝባቸው፣ የፍቅር ጓደኞቻቸው፣ የትዳር አጋሮቻችውና ከአብራካቸው የወጡ ልጆቻቸውን እንደናፈቋቸው ወጥተው ለቀሩ ወገኖቼ በሙሉ፤ እንዲሁም ለረጅም ዓመታት በልጆቻቸው ናፍቆት እየተንገበገቡ እንዳለቀሱና መንገድ መንገድ እንዳዩ ውድ ልጆቻቸውን ሳያዩ ለቀሩ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ እናቶች ይሁንልኝ››

አዲስ ማለዳ ከመጽሐፉ ደራሲ ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታ እንደተረዳችው፣ መጽሐፉ እውነተኛ ታሪክን መሠረቱ ያደረገ፣ በልብወለድ የአተራረክ ስልት የተዘጋጀ ነው። ታሪኩም በርካታ ዓመታትን ተለያይተው በቆዩ ቤተሰቦች መካከል፣ በየነበሩበት የሆነውን ኹሉ የሚያነሳ ነው። ይልቁንም መታሰቢያነቱ እንደሚያመላክተው ከኹለት ሕዝቦች ጋር የተገናኘ ነው።

እንደ መጽሐፉ ደራሲ ገለጻ፣ በዚህ መጽሐፍ የተነሳና በኢትዮጵያና በኤርትራ ጦርነት መካከል የተከሰተ፣ በኹለቱም ዘንድ ያልታወቀ ታሪክ አለ። እናም የመጽሐፉ አዘጋጅ እውነተኛ ታሪክን፣ በተለይም በጦርነቱ ወቅት ያልታየና ያልተሰማ፣ ያልተነገረለትም ነው ያሉትን በዚህ መጽሐፍ አጋርተዋል። በድምሩ ግን ፍቅር፣ ስደት፣ መለያየትና መገናኘት፣ ራስን ለሌላ ቤዛ ማድረግ በመጽሐፉ ይነበባሉ። ገጸ ባህርያቱም በገሀዱ ዓለም ያሉ ሲሆኑ፣ የተወሰኑት ብቻ የሥም ለውጥ እንደተደረገባቸው ደራሲው ማሞ ተናግረዋል።

ማሞ ኹለተኛ ክፍል አለው ያሉትን ይህን መጽሐፍ አንባቢ ጋር ለማድረስ በርካታ ዓመታትን ወስደዋል። አዲስ ማለዳ ይህ ለምን ሆነ ስትል ጠይቃለች። እርሳቸውም በመልሳቸው የአቅም ጉዳይ ፈታኝ ሆኖባቸው እንደነበር አልሸሸጉም። በወረቀት ላይ የተጻፉትን የታሪኩን ክፍሎች በኮምፕዩተር መተየብ፣ የተተየበውን አጥርቶ ተመልክቶ ወደ ማተሚያ ቤት መላክና ከዛም የታተመውን ለገበያ ማቅረብ ከባድ ሒደት ነበር ይላሉ።

ያም ሆነ ይህ፣ ትግሉን በአሸናፊነት ጨርሰው መጽሐፉን ለአንባቢ አድርሰዋል። አሁንም ኹለተኛ እትም የመጻሕፍት ገበያ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ለዚህ ደረጃ እንዲደርስ ላገዟቸውና ለረዷቸው ለሰናይት በላይ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለልጆቻቸውም ላቅ ያለ ምስጋናን አቅርበዋል።
ይህ መጽሐፍ የፊታችን መጋቢት 24/2014 በይፋ ይመረቃል ተብሏል። በዚህ መሰናዶ ላይ መገኘት ለሚሹ ኹሉ ግብዣ ቀርቧል።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here