በዓለም ላይ ያሉ አገራት ቁሳዊና ሰብዓዊ ዕድግት የሚከተሉት ሥርዓተ ትምህርት ነጸብራቅ መሆኑ ይነገራል። የአፍሪካ አገራትም ከጥልቅ ድህነታቸው ጀርባ የተበላሸ ሥርዓተ ትምህርት መኖሩ የሚታመን ነው።
ኢትዮጵያም የምትከተለው ሥርዓተ ትምህርት ለድህነቷና በየዘመኑ ለሚነሳው አገራዊ ግጭት እንደ መንስኤ ተደርጎ ይወሰዳል።
ከሞራል ያፈነገጡ በርካታ ‹የተማሩ ዜጎች› ያሉባት አገር ከመሆኗም በላይ፣ የአገሪቱ ዋና ችግር እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ፖለቲካም የተበላሸው የትምህርት ሥርዓት ውጤት እንደሆነ ይነሳል።
የአዲስ ማለዳው ሳሙኤል ታዴ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልገዋል የሚሉ የዘርፉ ምሁራንን በማነጋገር እና የ2013 የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን በማጣቀስ፣ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።
ከ110 ሚሊዮን በላይ ዜጋ ያላት ኢትዮጵያ፣ ጥልቅ የሆነ ድህነቷ ዋና መነሻ የትምህርት ጥራት መጓደል መሆኑ ይነሳል።
ድህነት ተወግዶ ዕድገት የሚረጋገጠው በትምህርት እና በዕውቀት ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ትምህርት ለአገሪቱ መፍትሔ ሲያመጣ ዕምብዛም አይታይም። ይባስ ብሎም ዘመናዊ ትምህርት ይሠጥ ባልነበረበት ወቅት ከዚህ የተሻለ ሠላምና ምጣኔ ሀብት እንደነበራት ነው የሚነገረው።
‹‹ያልተማሩ አባቶቻችን ያቆዩዋትን አገር የተማሩ መኃይማን ደርሰው አፈረሷት›› ሲባል በማኅበረሰቡ የሚደመጠውም፣ ትምህርት ለኢትዮጵያ የዕድገቷ መሠረት ሳይሆን፣ የጉስቁልናዋ መንስኤ እየሆነ ለመምጣቱ ማሳያ ነው።
የትምህርት ሥርዓቱ መስመር ሊይዝ ባለመቻሉና ተቆርቋሪ ባለቤት በማጣቱ አገሪቱ የተማረና የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል እያጣች፣ ያላት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችም በየጊዜው እየተባባሱ መጥተዋል።
ስለሆነም፣ ጊዜና አቅም ሰጥቶ የትምህርት ሥርዓቱን ማሻሻል እስካልተቻለ ድረስም አገሪቱ ወደ ከፍታ ሳይሆን ቁልቁል እንደምትወርድ ይነገራል።
የተደረገው የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ ምን ፋይዳ አመጣ?
ቀድሞ የነበረውን የትምህርት ዘርፍ ችግር ያስቀራል የተባለ የትምህርት ማሻሻያ ባለፉት ኹለትና ሦስት ዓመታት ተደርጎ፣ አዲስ የትምህርት እና የሥልጠና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ፣ አዳዲስ አሠራሮችን በማስተዋወቅ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል።
ይህ ማሻሻያ የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ፣ በኢትዮጵያ ለ20 ዓመት ሲሠራበት የቆየውን የትምህርት ሥርዓት ፖሊሲ በመቀየር የመማር ማስተማሩን የጥራት ደረጃ ያሻሽላል፣ እንዲሁም ሙያዊ ግዴታውን በብቃት የሚወጣ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የትምህርት ማኅበረሰብ ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ ነበር።
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብረ ገብነት፣ አገር በቀል ዕውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች መሆናቸው በወቅቱ ተገልጿል።
በተጨማሪም የትምህርት ፍኖተ ካርታ ማሻሻያ በቀድመው የትምህርት ሥርዓት 10ኛ ክፍል ማብቂያ ላይ ይሰጥ የነበረው አገራዊ የመልቀቂያ ፈተና እንዲቀር መደረጉ እንደ ጥሩ ነገር ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ የታሰበውን ያህል የትምህርት ጥራት ሲያመጣ አልታየም።
ለዚህም ከዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ወደ ዩንቨርስቲ እንዲገቡ መደረጉ የ10ኛ ክፍል ፈተና ባለመኖሩ በርካታ ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ድረስ እንደዘለቁ ተነግሯል። ይህም 10ኛ ክፍል ላይ ይሰጥ የነበረውን ፈተና ከማስቀረት ባለፈ ቀጥሎ ስለሚፈጠረው ኹኔታ መፍትሔ ያላስቀመጠ የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ አካል ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ይተቻል።
በጥቅሉም የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ ቢደረግም፣ ከበፊቱ የተሻለ በትምህርት ዘርፉ ላይ ውጤት ሲመጣ አልታየም። በርካታ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ብቁ ዜጋ ከማፍራት አኳያ ጥያቄ የሚነሳባቸው ሲሆን፣ በፖለቲካ ጥገኝነታቸውም በየጊዜው የብጥብጥ ማዕከል መሆናቸው አልቀረም። ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባለው የትምህርት ዕርከን ላይ ያለው ችግርም ሠፊና ውስብስብ መሆኑ የሚታይና በተደጋጋሚ የሚገለጽ ነው።
ለአብነትም በቅርቡ በጅማ ዩኒቨርስቲ በተካሄደ መድረክ በኢትዮጵያ ካሉ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች 65 በመቶ የሚሆኑት ማንበብ አይችሉም። እንዲሁም የሚያስተምሩትን ትምህርት ከተፈተኑ መምህራን ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት ብቁ አለመሆናቸው በመድረኩ ተገልጿል። በተጨማሪም፣ ላለፉት ሰባት ዓመታት አገር አቀፍ ፈተና እንደሚሰረቅ፣ ያሉት ትምህርት ቤቶችም 99 በመቶ አስፈላጊውን መስፈርት የሚያሟሉ አለመሆናቸው ተረጋግጧል።
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ሰለሞን በላይ (ዶ/ር)፣ ቀደም ብሎ የተደረገው ማሻሻያ ብዙም ያልተመከረበት፣ በምሁራን በደንብ ያልታየ እንደነበር አንስተዋል። በትምህርት ሥርዓቱ ላይ አሁን የሚታየው አጠቃላይ ችግርም የኢትዮጵያ ችግር ነጸብራቅ ነው ይላሉ።
ኢትዮጵያ የምትከተለው ሥርዓተ-ትምህርት ለተማሪዎች ሕይወት ምንም ጥቅም የሌለው በአሰስ ገሰስ የተሞላ የቆሸሸ ዘርፍ ነው ብለውታል። ለዚህም ነው ብዙ ተማሪዎች ለራሳቸው ችግር ከራሳቸው መፍትሔ የማያፈልቁት የሚሉት መምህሩ። የሥርዓተ ትምህርቱ አጠቃላይ ይዘቱና ፍልስፍናው ልክ አይደለም፤ መሠረታዊ የሆነ ችግር አለበት ባይ ናቸው።
አክለውም፣ የትምህርት መሠረታዊ ይዘቱ ባህል መሆን አለበት። ምዕራባውያኑ በዋናነት ባህላቸውን ነው ለተማሪዎቻቸው የሚያስተምሩት። ባህላቸውን ወደ ትምህርት ያመጡትና መተላለፍ ያለበትን ያስተላልፋሉ፤ መለወጥ ያለበትን እንዲለወጥ ያደርጋሉ። እኛ አገር ግን ኑሯችንና ትምህርታችን በጣም የተለያዬ ነው። የዕለት ከዕለት ኑሯችን፣ ጭንቀታችንና ችግራችን ትምህርታችን ውስጥ የለም። ስለዚህም ተምረን ለውጥ የማናመጣው ስለራሳችን እና ስለሚያስፈልገን በሚገባ ስለማናውቅ ነው የሚል ሐሳባቸውን ሠንዝረዋል።
ኢትዮጵያው ውስጥ አንድ ተማሪ ሲማር ከወላጆቹ አስተሳሰብና አሠራር እየራቀ ነው የሚሔደው ያሉት መምህሩ፣ እርሻና አናጢነት እየጠፋው እጁም እየለሰለሰ ይሔዳል። ይህም ከእኛ ባህልና ኑሮ ጋር የማይገናኝ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ስለመሆናችን ማሳያ ነው የሚል ሐሳብ አላቸው።
መምህር የሚሆኑት በኢኮኖሚና በትምህርት አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑት ናቸው። ሙያውን የሚጠቀሙት ለመሸጋገሪያነት ነው፤ የተሻለ ነገር ሲያገኙ የፈተኑትን ፈተና እንኳን ሳይሰበስቡ ነው የሚጠፉት። አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ የተበላሸ መሆኑን ሲነገር የሚሰማ የለም፤ ቢሰማም እንዳልሰማ ነው የሚያልፈው። ሆኖም ግን ትምህርት ለአንድ አገር ዋና ነገር ነውና አንድ አፍታ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መሠረታዊ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ጦርነትና ኮሮና ያሳደረው ጫና በምን መልኩ ተፈታ?
ከኹለት ዓመት በላይ በቀጠለው የኮሮና ቫይረስ ወርርሽኝ እንዲሁም ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ክፉኛ ከተጎዱ ዘርፎች መካከል የትምህርት መስኩ ዋነኛው እንደሆነ ይታመናል።
ወትሮም ብዙ መዛነፎች ያሉበት የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት፣ ቀድሞ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ ተማሪዎች አንድ ዓመት ሊሆን ትንሽ ለሚቀረው ጊዜ ቤት በመዋላቸው፣ መማርና ማወቅ የሚገባቸውን ነጥብ ሳያውቁ እንደቀሩ ተማሪዎችም ሆነ መምህራን ይናገራሉ።
ከዚያ ባለፈም በተለየ በምሥራቅ አማራ፣ እንዲሁም በአፋር ክልል ብዙ ቦታዎች፣ በኦሮሚያ (በወለጋ) እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በርካታ ተማሪዎች ከጦርነትና ግጭቶች ጋር በተያያዘ ከትምህርት ገበታቸው ርቀው ከርመዋል። በድርቅ የተነሳ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎች ስለመኖራቸውም የሚታወቅ ነው።
በትግራይ ክልልም እንዲሁ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በመላ አገሪቱ ትምህርት ቤቶች ከተዘጉበት ከመጋቢት 2012 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ትምህርት እንደተቋረጠ ነው።
ብዙ ቅሬታ ያስነሳው የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት
ኮሮና ቫይረስ እና ድርቅ፣ በተለይም ጦርነትና ግጭት የተማሪዎችን ሕይዎት እየፈተነ ባለበት ኹኔታ ውስጥም ቢሆን፣ ከብዙ መጓተት በኋላ በኹለት ዙር ለ2013 ዓመት የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና መሰጠቱ ይታወሳል።
ሆኖም፣ ከፈተና አወጣጡ ጀምሮ በቫይረሱ እና በጦርነት ምክንያት በተለያዩ አካባቢ ያሉ ተማሪዎች ሳይማሩት የተካተተ ጥያቄ አለ ከሚለው ቅሬታ ጀምሮ፣ ፈተና አሰጣጥ ሒደቱ ላይም ከፍተኛ ቅሬታ ሲነሳ ቆይቷል።
በአንዳንድ ቦታዎች በተቋም ደረጃ ፈተና ተሰርቆ በመውጣት ተማሪዎች አስቀድመው ሠርተውት እንዲገቡ እንደሚደረግም ነው በግልጽ የሚነገረው።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋም (ፕ/ር) ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ፣ ‹‹የፈተና መሰረቅ ከግለሰብ ይልቅ ተቋማዊ እየሆነ በመምጣቱ፣ በአጠቃላይ የደረሰብን የሞራል ክስረት ከፍተኛ ነው። የእኔ ክልል ተማሪዎች ማለፍ አለባቸው በሚል በተቋም ደረጃ የፈተና ወረቀቶችን በመስረቅና መልስ በመስጠት ጭምር ተባባሪ የሆኑ አመራሮች መኖራቸው የትምህርት ሲስተሙ ጥራት፣ ተዓማኒነት ከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› ነበር ያሉት።
ግማሹ በልፋቱ ውጤት ሲያመጣ፣ ሌላው ደግሞ ሳይማር የዲግሪ ወረቀት እየተቀበለ የሚያልፍበት ሒደት በትምህርት ጥራቱ ላይ ትልቅ ችግር ሆኖ መቀጠሉና አገሪቱ በትምህርት የምትፈታው ችግር እንዳይኖር ብሎም ብቁ ዜጋ እንዳይኖራት ማድረጉ ነው የሚነሳው።
በዘንድሮ የፈተና ሒደት ላይም የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት የተሠረዘው ከፈተናው ቀን ቀድሞ በመውጣቱ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር በይፋ ተናግሯል።
በዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና አሰጣጡ ላይ የጎሉ ክፍተቶች መታዬት የጀመሩት በተለይ ከ2009 ጀምሮ ቢሆንም፣ የዘንድሮ ደግሞ ከፈተና ጥያቄ አወጣጡና አሰጣጡ ጀምሮ አስተራረሙ፣ እንዲሁም ውጤት አሰጣጡ የባሰ ችግር ያለበት መሆኑ እየተነገረ ነው።
በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የተማሪዎችን ውጤት ለማየት ያህልም፣ በዋግኽምራ ለዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ከወሰዱ 2 ሺሕ 923 ተማሪዎች ውስጥ 705 የሚሆኑት ብቻ ማለፊያ ውጤት አምጥተዋል። በብሔረሰብ አስተዳደሩ ካሉት 16 መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 15ቱ ሲያስፈትኑ ከእነዚህም ውስጥ 2 ሺሕ 218ቱ ማለፍ አልቻሉም። ተማሪዎቹ መጀመሪያም ቢሆን በጦርነቱ ምክንያት በመፈናቀላቸው፣ በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ‹ፕላዝማ› ባለመኖሩ እና በሌሎች ምክንያቶች የተሟላ ትምህርት እንዳላገኙ ተገልጿል።
በሰሜን ወሎ ዞን ባሉ ስድስት ትምህርት ቤቶች የተፈተኑ ኹሉም ተማሪዎች እንዲሁ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት አለማምጣታቸው ተነግሯል። ዞኑ በአጠቃላይ ካስፈተናቸው 9 ሺሕ 710 ተማሪዎች ውስጥ 3 ሺሕ 657 ብቻ ያለፉ መሆናቸውም ነው የተገለጸው። ፈተና አሰጣጡ፣ ዞኑ ለአምስት ወራት የጦርነት ቀጠና ሆኖ መቆየቱን እና ተማሪዎች በተፈተኑ ወቅትም አስተማማኝ ሠላም አለመኖሩን ያላገናዘበ እንደነበር በዞኑ በኩል ተገልጿል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንም 11 ሺሕ 953 ተማሪዎች ተፈትነው ማለፊያ ውጤት ያመጡት 3 ሺሕ 42 የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ይህም ማለፊያው የጸጥታ ችግር ከሌለባቸው ሌሎች አካባቢዎች ጋር ተመሳሳይ መደረጉ በተማሪዎችና ወላጆች ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩ ተስተውሏል።
ጦርነት ያልነበረበትና ተማሪዎች የተሻለ የፈተና ዝግጅት አድርገው ፈተና ወስደዋል ተብሎ በሚታሰብባቸው ቦታዎችም ችግሩ የጎላ ሆኖ ታይቷል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንም ከ13 ሺሕ 862 ተፈታኝ ተማሪዎች ውስጥ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት መማጣት የቻሉት 3 ሺሕ 6 ብቻ መሆናቸውን ታውቋል። የዞኑ ትምህርት መመሪያም የእርማት ጥራት ችግር ማሳያ መኖሩን አመላክቶ፣ 140 ያመጣ አንድ ተማሪ ውጤቱ እንደገና ሲታይ 601 ማምጣቱን ነው የገለጸው።
ምዕራብ ጎጃም ዞንም እንዲሁ 25 ሺሕ 926 ተማሪዎች ተፈትነው የዩኒቨርስቲ መግቢያ ነጥብ ማምጣት የቻሉት 4 ሺሕ 195 የሚሆኑት ብቻ ናቸው። 21 ሺሕ 731 ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርስቲ ማለፍ ያልቻሉበት የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያም፣ የክልሉ ማህበረሰብ ሙሉ ትኩረቱን ጦርነት ላይ አድርጎ በከረመበት ወቅት፣ በብዙ ወስብስብ ችግሮች ውስጥ ሆነው ለተፈተኑ ተማሪዎች ተጨማሪ ማበረታቻ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ነጥብ መስጠት ሲገባ፣ በሠላም ጊዜ ተደርጎ የማያውቅ ውሳኔ መወሰኑ እንደ ትምህርት አመራር ባለሙያ በእጀጉ ያሳዝናል ሲል ገልጿል።
22 ሺሕ 297 ተማሪዎችን አስፈትኖ 3 ሺሕ 384 ተማዎች ብቻ ማለፋቸውን የገለጸው የምስራቅ ጎጃም ትምህርት መምሪያም፣ 162 ያመጣ አንድ ተማሪ ቅሬታ በማቅረቡ ውጤቱ 647 ተብሎ መስተካከሉን ጠቅሶ፣ የተማሪዎች የፈተና አስተራረምና ውጤት አሞላል ችግር እንዳለበት ገልጿል።
ችግሩ በስፋት የታየው በአማራ ክልል ይሁን እንጂ፣ በአፋር ክልልም ችግሩ የሠፋ መሆኑ ተመላክቷል። በጉራጌ ዞን ኤገር በሚባል ወረዳ ኹሉም ተማሪዎች እንዳላለፉ ተገልጿል። ሲዳማ ክልል ሎካ አባያ ወረዳ ከ444 ተፈታኞች ውስጥ ያለፉት አምስት ተማሪዎች ብቻ ናቸው። በደቡብ ጎንደር ታች ጋይንትም እንዲሁ 1720 ተማሪዎች ተፈትነው 22 ብቻ ሲያልፉ፣ ከዳባት ወረዳም 1166 ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ውጤት ያመጡት 37 ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። በከፋ ዞን ተማሪዎችን ካስፈተኑ 57 ትምህርት ቤቶች 36 ከሚሆኑት አንድም ተማሪ የዩኒቨርስቲ ማለፊያ ማምጣት አለመቻሉ ታውቋል። 4 ሺሕ 579 ተማሪዎች ተፈትነውም፣ 738 ብቻ በማለፋቸውም የዞኑ ትምህርት መምሪያ ፈተናው እንደገና እንዲታይ ሲል ጠይቋል።
አሁንም ቢሆን የሥነ-ዜጋ ትምህርት ከሌሎች የትምህርት ዓይነቶች አንጻር ሲታይ የታየበት የውጤት ግሽበት አሳማኝ ባለመሆኑ የተሠረዘው እንዲስተካከል፣ የፀጥታ ችግር ውስጥ ለነበሩ ክልሎች የተለየ ውሳኔ እንዲደረግ፣ የፈተና እርማቱ እንደገና እንዲታይና የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤቱም እንዲሻሻል በተለያዩ አካላት ጥያቄዎች እየቀረቡ ይገኛል።
አገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ ከ20ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ቅሬታ አስተናግጃለሁ ቢልም፣ ችግሩ በስፋት ካለባቸው አካባቢዎች ወይስ ከየት አካባቢ የሚለውን ግልጽ አላደረገም። አሁንም ድረስ ቅሬታቸውን እያሰሙ ያሉ ተማሪዎች፣ ወላጆችና መምህራን ቢኖሩም፣ ተቋሙ እርማቱ በጥንቃቄ መሠራቱን ገልጾ፣ የእርማት ችግሩ የተፈጠረው ከ559 በማይበልጡ ተማሪዎች ላይ ነው ሲል አስቀምጧል።
ትምህርት ሚኒስቴር ትግራይ ክልል የነበሩ አራት ዩኒቨርስቲዎች አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸውን ጠቅሶ፣ በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች አጠቃላይ የመቀበል አቅም አናሳ መሆን ማለፊያውን ከፍ እንዲል እንዳደረገው ቢገልጽም፣ የተቋሞች የመቀበል አቅም የታወቀ ሆኖ ሳለ በጠቅላላ ከተፈተኑት ውስጥ 25 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እንዲገቡ መደረጉም ለትምህርት ሥርዓቱ አደጋው የከፋ መሆኑን የሚገልጹ የትምህርት አመራር ተቋማት አሉ።
በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪ መቀበል አለመቻላቸው ቢነሳም፣ ከክልሉ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች አለመኖራቸውን ማየትም ያስፈልግ ነበር በማለት የቀረበውን ምክንያት ውድቅ ያደርገዋል።
ይህም ከፍተኛ ውጤት ያላቸው (ሰቃይ የሚባሉ) ተማሪዎች መጀመሪያ ከተነገራቸው ውጤት ይልቅ፣ እንደገና ሲታይ የበለጠ ሆኖ መገኘቱ እርማት የሚሠራውን ተቋምና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት እንዝህላልነት ያሳዬ ነው በማለት በርካቶች ይተቻሉ።
በዚህም የአማራ ምሁራን መማክርት፣ የሲቪልና የኃይማኖት ድርጅቶች፣ የአማራ ብሔራዊ ክልል ትምህርት ቢሮና በክልሉ ያሉ የዞን ትምህርት መመሪያዎች፣ ከፈተና አስተራረሙ ጀምሮ ውጤት አሰጣጡ እና ማለፊያ ነጥቡ እንደገና እንዲታይ ቅሬታቸውንና ተቃውማቸውን እያቀረቡ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በበኩሉ፣ በ2013 የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ላይ በቀረቡ አቤቱታዎች መሠረት የተደረጉ ምርመራዎችን ይፋ ባደረገበት መግለጫው፣ ‹‹በፈተና ወቅት የተፈጠሩ የእርማት ስህተቶች በድጋሚ እንዲታይልን ቅሬታችንን ለፈተናዎች ኤጀንሲ ብናቀርብም ቅሬታችንን ተቀብሎ ሊያስተናግደን አልቻለም በማለት የቀረበውን ጥቆማ በተመለከተ ተቋሙ ባደረገው ምርመራ፣ የፈተናዎች ኤጀንሲ የፈተና እርማትን አስመልክቶ ተማሪዎች ያቀረቡትን ቅሬታ በመቀበል ምላሽ መስጠቱን የገለጸ ቢሆንም፣ የተቋሙ መርማሪዎች ለምርመራ ሥራ በኤጀንሲው በተገኙበት ወቅት በርካታ ተማሪዎች ቅሬታቸውን ለማቅረብ በኤጀንሲው ቢገኙም፣ ወደ ውስጥ ገብቶ ቅሬታን ለማቅረብም ሆነ ቅሬታቸውን ተቀብሎ ሊያስተናግዳቸው እንዳልቻለ፣ ይልቁንም ቅሬታቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲያቀርቡ ተነግሯቸዋል›› ሲል ገልጿል።
ማንኛውም ዜጋ በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ ለሚመለከተው አገልግሎት ሰጪ ተቋም የማቅረብ መብት እንዳለውና ቅሬታ የቀረበለት አካልም ቅሬታውን ተቀብሎ ያለምንም ገደብ ምላሽ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት በዐዋጅ የተደነገገ ቢሆንም፣ ቅሬታቸውን ይዘው ወደ ትምህርት ሚኒስቴር በመሔድ ለማቅረብ ጥረት ቢያደርጉም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ጉዳዩ የሚመለከተው የፈተናዎች ኤጀንሲ ነው በሚል ቅሬታቸውን ሳይቀበል የቀረ መሆኑን አመላክቷል።
በዚህ ምክንያትም ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቅሬታቸውን ለማቅረብ መጥተው ለእንግልት እየተዳረጉ እንደሚገኙና አስተዳደራዊ በደል እየተፈጸመባቸው መሆኑን የተቋሙ መርማሪዎች በቦታው በመገኘት ማረጋገጣቸውን ነው ያሳወቀው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤም (ኢሰመጉ) በሠላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በአፋጣኝ ይቁሙ ሲል በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት በርካታ ተፈታኞች እና ወላጆች ቅሬታ እያነሱበት ያለውን የ2013 የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት እንደገና መርምሮ ለተማሪዎች አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ አያይዞ ጠይቋል።
የተለያዩ አካላት በፈተናው ውጤት ዙሪያ የሚሰጧቸው ሐሳቦች ሕዝቡን ግራ እያጋቡ እና የተማሪዎችን ሥነ ልቦና እየጎዱ መሆኑን ጠቅሶም፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት በችግሩ ዙሪያ ግልጽ ማብራሪያ መስጠት እና ባስቸኳይ የእርምት ዕርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ኢሰመጉ አሳስቧል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ ትምህርት መምህሩ ጥሩሰው ተፈራ (ፕ/ር)፣ ዝቀተኛ ውጤት ያመጡት አብዛኞቹ ተማሪዎች በጦርነት ቀጠና ውስጥ የቆዩ መሆናቸውን አመላክተው፣ እነዚህ ተማሪዎችም በቅጡ ማሰብ አይችሉምና አሁንም እንደገና እንዲፈተኑ መደረግ አለበት ባይ ናቸው።
ፈተና ከመሰጠቱ በፊት ከማኅበረሰቡ ጋር ምክክር ያስፈልግ ነበር የሚሉት መምህሩ፣ ለየት ያለ የጦርነትና የበሽታ ጊዜ የቆዩ በመሆናቸው አሁንም የተለዬ የአጭር ጊዜ መርሃ ግብር (crush program) ተዘጋጅቶላቸው እንደገና ሊፈተኑ ይገባል ነው የሚሉት።
በመኖርና አለመኖር ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ፈትኖ ውጤት በመስጠት አላለፉም ማለት ተገቢ አይደለም። ይህን ክፍተት ተጠቅመው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ቢገቡ ውጤታማ የማይሆኑ ልጆች፣ የተሻለ የሚያስመዘግቡትን ዕድል መዝጋት የለባቸውም ሲሉም ተናግረዋል።
በጦርነት ቀጠና ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች ኹኔታዎች እንኳን ለመማር ለሌላም አመች ስላልነበሩ ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለዋል ማለት እንደማይቻልም ነው ያነሱት። ለዚህም መንግሥት ችግሮች በተከሰቱባቸው ዞኖች ጣልቃ በመግባት ቅሬታዎችን ለማስተካከል የተለየ ሥራ እንዲሠራ አሳስበዋል።
ሰለሞን በላይ (ዶ/ር) በጉዳይ ላይ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ሐሳብ፣ ምን እየተካሄደ እንዳለ ግልጽ አይደለም። አስቀድሞ የትምህርት ሥርዓቱ የተሳሳተ በመሆኑም እያወራን ያለነው በአንድ ስህተት ላይ ሌላ ስህተት ነው ብለዋል።
ዋናው ነገርም ምን ያህል ተማሪዎች አለፉ የሚለው አይደለም። አልፈውስ የት ሊደርሱ ነው? ተምረው የተሻለ ቢያውቁም ለስደትና ለሌላ አገር ሎሌነት ነው የሚዳረጉት ሲሉ ዕይታቸውን አስቀምጠዋል።
በመጀመሪያው ዙር ከተፈተኑ 554 ሺህ 682 ተፈታኞች ውስጥ 25 በመቶ የሚሆኑት የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎችን የሚቀላቀሉ ሲሆን፣ በኹለተኛው ዙር ከተፈተኑ 53 ሺሕ 997 ተማሪዎች ውስጥ 28 ከመቶ የሚሆኑት ወደ መንግሥት ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ ይደረጋል ሲል ትምህርት ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል። ይህም ከተፈተኑት አጠቃላይ 600 ሺሕ በላይ ተማሪዎች 152 ሺሕ የሚሆኑት ዩኒቨርስቲ ገብተው ይማራሉ ነው የተባለው። ይህም በአገሪቱ ያለውን የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው።
ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች ካሉ አገሮችም የወረደ የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነት እንዳላት የጠቆሙት ጥሩሰው ተፈራ (ፕ/ር) ናቸው። እርሳቸውም ብዙ የትምህርት ተቋማት ከአቅም በታች መሆናቸውን አንስተው፣ የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ቆመ ቀር መሆን የለበትም፤ በየጊዜው ተደራሽነቱንና አቅሙን የሚያሳድግ፣ ለማኅበረሰቡ ችግሮችም ምላሽ የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
የነገ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ
ሜላት ፈንታው በቆቦ ከፍተኛ አጠቃላይ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪ ነች። የማለፊያ ውጤት አምጥታ ወደ ዩኒቨርስቲ የምትሄድበትን ቀን እየተጠባበቀች ቢሆንም፣ እኔን ጨምሮ ብዙ ጓደኞቻችን በትምህርት ሥርዓቱ ደስተኞች አይደለንም ትላለች።
መማር ያለባቸው ተማሪዎች ቀርተው፣ በተጭበረበረ አሠራር ወደ ዩኒቨርስቲ የገቡ በርካታ ተማሪዎች አሉ የምትለው ሜላት፣ ከምንም በላይ ደግሞ ዩኒቨርስቲ ሲባል ትዝ የሚለን ግጭት በመሆኑ በቀጣይ ሞተን ወይም ተመርቀን እንደምንወጣ ስለማናውቅ ወደ ካምፓስ ለመግባት የሚያጓጓን ነገር የለም ትላለች።
ገብተን በአግባቡ የምንማር አይመስለኝም። ማን ሻንጣ ይዞ ገብቶ ማን በሠላም እንደሚመለስ አናውቅም። ስለዚህም በዚህ ወቅት ዩኒቨርስቲ መግባት የሚያስደስት አለመሆኑን ነው የገለጸችው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በትምህርት የሚያምን ትውልድ እየቀነስ መሔዱና የትምህርት ሥርዓቱም በአግባቡ የተቃኘ አለመሆኑ ይነሳል። በየክልሎች ስለታሪክ የሚሰጠው ትምህርትም ወጥ ባለመሆኑ ሕዝቦች ከመተጋገዝና አብሮ ከማደግ ይልቅ በልዩነቶቻቸው ላይ ትኩረት አድርገው ሲገፋፉ እንዲኖሩ እንዳደረጋቸው በየጊዜው የሚነገር ነው።
በኢትዮጵያ የተከሠቱ አብዛኛው ችግሮች የዘመናዊው ትምህርት ተደራሽነት ከጨመረ በኋላ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። የትምህርት ሥርዓቱ የተቀረጸው አገርን በሚገነባ መልኩ አለመሆኑን የሚያመላክት በመሆኑም፣ ፈጣን ዕርምጃ ተወስዶ መሠረታዊ ማስተካከያ እንዲደረግለት ጥያቄዎች እዚህም እዚያም ሲቀርቡ ቆይተዋል።
የነገ ትውልድ የተሻለ የሚሆነው ዛሬ ላይ በሚያገኘው ትምህርት መሆኑ የሚታወቅ ነው። የተከፋፈለና በሙስና የተዘፈቀ ትውልድ የሚወጣው የትምህርት ሥርዓቱ ሊስተካከል ባለመቻሉ ነው።
ስለነገ ከመነጋገር በፊት ለመሆኑ ትምህርት ዛሬ ላይ አለ ወይ ሲሉ የሚጠይቁት መምህር ሰሎሞን፣ አንድ ተማሪ ከታች ጀምሮ ከአካባቢው ጋር የተያያዘ በጣም አስፈላጊ ነገር እየተማረ ከመጣ፣ የትኛውም ክፍል ላይ ትምህርቱን ቢያቋርጥ ለራሱም ሆነ ለሕዝብ ጥቅም ይሰጣል ነው የሚሉት። አሁን ባለው የመማር ማስተማር ሒደት ትልቁ ግብ ማንበብና መጻፍ ነው፤ የቱ ጎበዝ ሰዓሊ፣ የትኛው ጎበዝ ሙዚቀኛ እንደሚሆን ለማረጋገጥ የምንከተለው ዘዴ (multi intelligent approach) ባለመኖሩም፣ ስለነገ ትውልድ መልካም ዕጣ ፈንታ ትምህርትን ተጠቅሞ መናገር እንደማይቻል ነው ያስገነዘቡት።
የትምህርት ሥርዓቱም ሆነ የምዝና ሥርዓቱ የተበላሸ መሆኑን አንስተው፣ በዩኒቨርስቲ ውስጥ የኹለተኛ ድግሪ ተማሪዎች ሆነው በአማርኛም ሆነ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ከአስተማሪ ጋር መግባባት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በዚህም ትምህርት ለኢትዮጵያ እንዴት ነው የሚያገለግለው የሚለው እስካልተመለሰ ድረስ ችግሮች ተባብሰው ይቀጥላሉ በማለት አመላክተዋል።
በትምህርት ዘርፉም ከሚኒስቴር ተቋማት እስከ ታች ያሉ ትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን ድረስ የሚሰጠው ሹመት የፖለቲካ ተጽዕኖ ስላለበት ጎጅና አሳፋሪ እንደሆነ ገልጸው፣ የትምህርት ሥርዓቱን ኃላፊነት ወስዶ ማስተካከል ያለበት መንግሥት መሆኑን አጽንኦት ሠጥተውበታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014