መነሻ ገጽአንደበት“ችግሩ እስካልተቀረፈ ድረስ መንግሥት ከደሙ ንጹሕ ነኝ ሊል አይችልም”

“ችግሩ እስካልተቀረፈ ድረስ መንግሥት ከደሙ ንጹሕ ነኝ ሊል አይችልም”

ግዛቸው ሙሉነህ ትውልድና ዕድገታቸው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ንጃ በሚባል ወረዳ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በእንግሊዝኛ፣ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከዚሁ ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን አግኝተዋል። ሥራቸውን በመምህርነት የጀመሩት ግዛቸው ወደ ፖለቲካው በመቀላቀል በአማራ ክልል ከወረዳ እስከ ክልል በተለያዩ የሥራ መደቦች አገልግለዋል። አሁን ላይ የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ከቢሮ ኃላፊው ጋር በክልሉ ወቅታዊ ኹኔታዎችና አጠቃላይ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አደርጓል።

መንግሥት ለውጥ ላይ ነኝ ቢልም አማራ ክልልን ባለፉት ሦስት ዓመታት መረጋጋትና ሠላም የሰፈነበት ማደረግ አልተቻለም። ክልሉን የተረጋጋ ማድረግ ያልተቻለው ለምንድን ነው?
አማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በተለይም ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል አካባቢ ለረዥም ጊዜ ጦርነት ላይ ነው ያሳለፈው። በለውጡ ውስጥም በለውጡ ኃይልና ለውጥ በማይፈልገው ኃይል መካከል የነበረ ግብ ግብ አለ፤ በዚህ ጊዜ በጣም የጸጥታ መረበሽ የነበረበት ኹኔታ አለ። በኋላ ደግሞ ለውጡን የማይቀበለው ኃይል ለውጡን በተለያየ መንገድ ለማደናቀፍ በሚያደርገው እንቅስቃሴ መካከል የጥቅም ግጭቶች ይካሄዱ ነበር።

የጥቅም ግጭቶች ብቻ ብለህ ቀለል አደርገህ የምታልፈው ብቻ ሳይሆን፣ አማራ ክልልም ሆነ በአገራችን ላይ የተፈጠረው ግጭትና ችግር ትላንትና የመጣ አይደለም። ይሄ ባለፉት 50 ዓመታት በተሠራ የፖለቲካ አሻጥር እንቅስቃሴ ውስጥ ቀስ በቀስ እያደገ፣ በተለይም ደግሞ የዴሞክራሲ ዕጦት፣ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መጓደል፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበርና አጠቃላይ የታሪክ ትርክቱ በተዛባ መንገድ በመቅረቡ በአገራችንም ይሁን በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የወንድማማችነትና የአንድነት መሸርሸር ገጥሞናል።

የወንድማማችነትና አንድነት መሸርሸር ብቻ ሳይሆን ጽንፈኝነት በስፋት ተቀርቅሯል። ጽንፈኝነት እያቆጠቆጠ መጣ፤ ግለኝነት እየበረታ የመጣበት ኹኔታና በሒደቱ ሰው ለሰው፣ ብሔር ለብሔር የማጋጨት እንቅስቃሴዎች ቀስ በቀስ እየጎለበቱ የመጡበት፣ ኃይማኖችትን ከኃይማኖት የማጋጨት እንቅስቃሴዎች እያደጉ የመጡበትና አጠቃላይ ፍትሐዊነት በመጥፋቱ ምክንያት የተፈጠሩና እነዚህን ተከትሎ ያጣናቸው በርካታ ዕሴቶች አሉ። የኃይማኖች ዕሴቶችን ጨምሮ በሕወሓት የአገዛዝ ዘመን እንዲሸረሸሩ የሆነበት፣ ፈሪሃ እንግዚአብሔር እየላላ የመጣት፣ ሰው ዕምነቱን እንኳን የማይፈራበት፣ ሰው ለሰው የማይራራበት ኹኔታዎች ተፈጠሩ። እነዚህ በሒደት እያደጉ መጥተው ባለፉት ጊዜያት በአማራ ክልልም ይሁን ኢትዮጵያ ላይ አለመረጋጋቶች እንዲከሰቱ ያደረጉና በአንዳንድ አካባቢዎች በጣም መሰረታዊ የሚባሉ ችግሮች ነበሩ።

በለውጡ ማግስት ለውጥ ፈላጊ እና ለውጡን የሚቃረን ኃይል መካከል የሚፈጠር ቅራኔ አለ። ለውጥ የማይፈልጉ አካላት ደግሞ እዚህ አገር ውስጥ ያሉት ብቻ አይደሉም፣ በግልጽ ለመናገር ሕወሓት አለ። የሕወሓት ቡድን፣ ይሄ ኃይል ከውስጥ ባንዳዎች በመሸመት፣ ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር በማበር ለዘመናት ከዚህ ድሃ አገር የዘረፈውን ገንዘብ ተጠቅሞ ለውጡን ለመገዳደር እንቅስቃሴ አድርጓል። እንቅስቃሴ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ ጦርነት እንዲፈጠር በር የከፈተበት ኹኔታ አለ።

በዚህ ምክንያት ደግሞ ይሄንን የምናስኬድበት መንገድ ጊዜ ስለወሰደ እንደተባለው ችግር ተፈጥሮ ነበር፤ አለመረጋጋት ነበር። አሁን ላይ ከጥቂት ወራት ወዲህ ያለው ኹኔታ ጥያቄውን ባነሳኸው ኹኔታ ሳይሆን የተረጋጋ ኹኔታ ነው ያለው። በአማራ ክልልም በአገሪቱም ትልልቅ ሥራዎችን መሥራት የተጀመረበት፣ በተነጻጻሪ መደበኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር እና በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ መውሰድ ያስፈልጋል።

አሁን ያን ያክል ብዙ ችግር አለ የሚባል አይደለም። ያ ማለት ሙሉ በሙሉ ሠላም ነው ተብሎ የሚደመደም አይደለም። አንዳንድ ችግሮች አሉ፤ በተለይ ከጦርነት ማግስት የሚመጡ አንዳንድ ጉድለቶች ይኖራሉ። የድል ሽሚያዎች ይኖራሉ፤ የሌብነት እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ፤ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ አንዲህ ዓይነት ነገሮች የሚጠበቁ ናቸው። እነዚህን ለመምራት እየሠራን ነው ያለነው። በተለይ ደግሞ ጽንፈኝነት የሚያቆጠቅጥባቸው አንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ትንኮሳዎች ያሉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ መፈናቀሉም እስካሁን ያላቆመ ስለሆነ ሙሉ ሠላም ነን ብለን የምነደመድመው ሳይሆን ቸግሮች አሉ። ነገር ግን በአንጻራዊነት እስካሁን በሕወሓት የተያዙ አካባቢዎች ማኔጅ ለማድረግ እየተሞከረ ነው።

ከዚያ ውጭ አንዳንድ ጥሩ ያልሆኑ ምልክቶች አሉ ። በግለሰቦች የሚነሱ፣ በቡድኖችም ጭምር የሚነሱ መልካም ያልሆኑ፣ ግን ደግሞ ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ፣ እያደጉ ሲሄዱ ሰውን ሊያማርሩ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ። የሰው ሕይወት የሚጠፋባቸው፣ ግጭቶች የሚነሱባቸው ኹኔታዎች አሉ። መሀል አገር ላይም ጭምር፣ አንዳንድ ባልተገባ መንገድ የሚንቀሳቀሱ፣ የራሳቸው ፍላጎት ባላቸው አካላት የሚፈጸሙ ድርጊቶች አሉ። እነዚህም ማረም እንዳለ ሆኖ አሁን ላይ በክልሉ ሠላማዊ ኹኔታ እንዳለ በደንብ መሰመር አለበት።

ክልሉ ካሉበት ውስጣዊ ችግሮች በተጨማሪ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ሞትና መፈናቀል ከለውጡ በኋላ ተባብሶ ቀጥሏል። ለምንድን ነው የዜጎችን ሞትና መፈናቀል ማስቆም ያልተቻለው?
የተሸከምነው ዕዳ አጭር አይደለም። እያወራረድነው ያለነው ሒሳብ ለዘመናት የኖረ ነው፣ ብዙ ዕዳ ነው እኛ ላይ መጥቶ የተጫነው። አሁን ባለው ትውልድ ላይ የመጣው ዕዳ ብዙ ነው፤ ከእውነታው አኳያ እውነታውን ከማየት ልክ የሚሞቱና የሚፈናቀሉ ዜጎች አሉ። ይሄ ፍጹም ትክክል ያልሆነ ነው፤ መቆም ያለበት ነው። ነገር ግን መንግሥት ዝም ብሎ አልተቀመጠም። አንዳንዱ ነገር ዕዳው በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ፣ ጠላቶቻችንም በዚያው ልክ ስለሆኑ፣ ፍልሚያ ውስጥ ስለሆነ ያለነው፣ መሆን ያልነበረባቸው ድርጊቶች ሲፈጸሙ እናያለን። ይሄ መኮነን ያለበት ደርጊት ስለመሆኑ የሚያሻማ አይደለም።

ከሥራ አኳያ ግን ሥራ እየተሠራ ነው ያለው። በነገራችን ላይ በሚዲያም እሰማዋለሁ በተለይ በዲጂታል ሚዲያው ላይ ከመንግሥት አኳያ ብዙ ይወራል። መናገርና ሠርቶ ማሳየት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። መታወቅ ያለበት፣ መንግሥት አርፎ አልተቀመጠም። ሕዝቡን ዕረፍት የሚነሳ የተሰጠን የጠላት ስምሪት ብዙ ከመሆኑ አንጻር ችግሮችን መቋቋም አልቻልንም። ችግሩን መቋቋም አለመቻል ብቻ አይደለም የተባባሪነት ችግር አለ። ችግሩ አስቸጋሪና ውስብስብ ነው፤ የውጭም የውስጥም ነው፤ የተባባሪነትና የባለቤትነት ጉድለት አለ። የክልሎችን ብቻ ሳይሆን አማራ ክልል ውሰጥ ያሉ ችግሮችን መንግሥት እንዲቀርፍ ከተፈለገ ኹሉም አካል መተባበር አለበት። መላው የአማራ ሕዝብ መተባበር አለበት፤ አክቲቪስቱ መተባበር አለበት፤ ሚዲያው መተባበር አለበት፤ የኃይማኖቸ አባቶች መተባበር አለባቸው፤ ኹሉም በራሱ ስለ ሠላም መቆም አለበት።

ይሄን በማድረግ በኩል መሠረታዊ የሚባል ችግር አለ። አንዲያውም አንዳንዱ ሲናገር ገብቶት አይመስለኝም የሚናገረው። በምንም ተዓምር መንግሥት ላድርገው ቢል በመንግሥት ብቻ የሚሆን አይደለም። ለረጅም ዘመን አመለካከት ላይ የተሠራ ሥራ አለ፤ አመላካከት ላይ ካልቀየርከው በቅጣት ብቻ የምታድነው አይደለም። በነገራችን ላይ የሚቆም አይደለም፤ አሁንም ይቀጥላል። እየቀነስን ለመሔድ ካልሆነ፣ ጥላቶቻችን አስካልጠፉ ድረስ የሚቆም አይደለም። ጠላቶቻችን ደግሞ እንዲህ በቀላሉ የሚጠፉ አይደሉም፤ ጊዜ ይፈልጋል። ማጥፋት ስል አመለካከታቸውን ካስጣልን ጠላት ቀንሷል ወይም ጠፍቷል ማለት ነው።

እንደዚያ ካልሆነ ሕዝብን ገድለህ አትጨርስም። ዕርምጃ ወስድህ፣ አስረህ ልትጨርስ አትችልም። ለዚህ ነው ሥራው ትብብር የሚያስፈልገው። ከዚያ ውጭ በክልሎች መካከል የነበረው ተቀራርቦ የመሥራት ጉዳይም በጣም ጉድለት የነበረበት ነው።

በተለይ ችግሮች ጎልተው የሚታዩባቸው ክልሎች የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ለማስጠበቅ ጥረት አድርገዋል ማለት ይቻላል?
የመጀመሪው ጉዳይ፣ አማራ ክልልም፣ የፌዴራል መንግሥትም፣ ሌሎች ክልሎችም በተፈጠረው ችግር ምክንያት ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው። በዋናነት ችግሩ የተፈጠረባቸው ክልሎች፤ ምክንያቱም መንግሥት የመጀመሪያው ኃላፊነቱ የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት ማስጠበቅ አለበት። ስለዚህ ችግሩ እስካልተቀረፈ ድረስ መንግሥት ከደሙ ንጹሕ ነኝ ሊል አይችልም።

ቅድም ያልኩት መተባበር ያስፈልጋል የሚለው እንዳለ ቢሆንም፣ የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ በቀዳሚነት የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ለሚፈጠሩ ቸግሮች መጀመሪያ ኃላፊነት መውሰድና ችግሮቹን መፍታት ያለባቸው ክልሎች ናቸው የሚለው ምንም ጥያቄ የለውም። በቤኒሻንጉል ጉምዝ ለሚፈጠር ችግር ኃላፊነቱን መውስድ ያለበት የክልሉ መንግሥት ነው፤ አማራ ክልል በአጋርነት ሊሠራ ይችላል። ለኦሮሚያም በተመሳሳይ።

ችግሩ ሠፊ ከመሆኑ አኳያ እነዚህ ክልሎች አልሠሩም ማለት አይቻልም። ክልሎቹ እየሠሩ ነው ችግሩ እየተፈጠረ ያለው። ይሄ አሉባልታውን መንግሥት እራሱ ተባባሪ ነው የሚለውን መውሰድ አይቻልም። ምክንያቱም እኛ በቅርበት ይሄንን እየሠራን ነው ያለነው። ክልሎች ብዙ ዋጋ ሲከፍሉ እናያለን ነገር ግን ውጤታማ ነው ወይ የሚለው ስንወስድ ግን ውጤታማ አልነበረም። ይሄንን በጋራ ገምግመናል። አሁን ላይ ከኦሮሚያም ጋር ከቤኒሻንጉልም ጋር በጋራ እየሠራን ነው። እየተመካከርን ነው ያለነው። ኹሉም ነገር በሚዲያ ስለማይገለጽ ነው እንጂ በየመድረኩ ዝርዝር ግምገማ እንገመግማለን። ገምግመንም አቅጣጫዎችን እናስቀምጣለን፣ ገምግመን ከወጣን በኋላ ግን እነሱም ልክ ወደ ሥራ ሲገቡ የመተባበርና የጸንፈኝነት ችግር ስላለ በተፈለገው ልክ ውጤታማ ነበር ወይስ ስንል አይደለም። አሁንም የሚፈናቀል ሰው አለ፤ አሁንም መተጋገዝና መተባበር ይፈልጋል።

እንደዚያ ካልሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ የኦሮሚያን ክልል መንግሥት፣ የአማራን ክልል መንግሥት በመሳደብ ይሄ ችግር ሊፈታ አይችልም። ምናልባት የዜጎችን ስቃይና ሞት እናበዛው ካልሆነ በስተቀር። ስለዚህ መተባበር ይጠይቃል፤ በተለይ በፖለቲካ ‹ኤሊቱና በአክቲቪስቱ› በኩል። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመሰዳደብ ችግሩ ሊፈታ አይችልም።

- ይከተሉን -Social Media

ኦነግ ሸኔ ሰዎችን በመግደሉ የሚያገኘው ፖለቲካዊ ጥቅም አለ። ንጹሕ ሰዎችን ነው እየገደለ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጥፋቸው። ይሄን በማድረግ መንግሥትን በመረበሽና ብጥብጥ በመፍጠር የሚያገኘው ፖለቲካዊ ጥቅም ስላለ እንጂ፣ በተለየ መንገድ ሰዎችን በመግደል የሚያገኘው ጥቅም ስላለ አይደለም። በፌስቡክ መሰዳደብ የዜጎችን ሕይወት መታደግ አይቻልም። የሚቻል ቢሆን ኖሮ ድሮ ነበር የሰዎች ሞት የሚቆመው። ማስቆም የሚችለው መተባባር፣ በጋራ መሥራት፣ በወንድማማችነት መንፈስ ችግሮችን መመልከት፣ የጋራ ጠላታችንን በጋራ መዋጋት ያስፈልጋል።

ክልሉ በሰሜኑ ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎችንና ውድመቶችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም ምን እየሠራ ነው?
በጦርነቱ ምክንያት ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለመድኃኒት ዕጥረትና ለምግብ ተረጅነት የተጋለጠበት ኹኔታ እንዳለ ካሁን በፊትም ገልጸናል። በተለያዩ ጊዜያት መፈናቀሎችም ስላሉ በአጠቃላይ በአማራ ክልል ወደ 11.6 ሚሊዮን ሕዝብ ድጋፍ ይፈልጋል። ይሄ ሕዝብ በየወሩ 1.3 ሚሊዮን ኩንታል እህል ይፈልጋል።

ከዚያ ውጭ በአካባቢው የትምህርት ተቋማት፣ የጤና ተቋማትና፣ ድልድዮች፣ የኃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ውድመቶች ተከስተዋል። እነዚህ መልሰው መገንባት አለባቸው በሚል፣ ሕዝቡም ደግሞ መልሶ መቋቋም ስላለበት ሠፊ ሥራ እየተሠራ ነው። የመጀመሪያው እስካሁን በሠራነው ሥራ ሰው ወደ መደበኛ ሕይወቱ ተመልሷል የሚለው መሰመር አለበት። አብዛኛው ሰው ወደ ቤቱ ተመልሶ መደበኛ ሕይወቱን ለመቀጠል እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፤ ግን የተፈናቀለበት ወቅት የሚያመርትበት መሆኑን ተከትሎ አርሶ አደሩ የሚበላው የለውም።

የተፈናቀለው ሕዝብ ከብቶቹ ስለተዘረፉ ማረስም አይችልም፤ እራሱን መመገብም አይችልም። ለእነዚህ አሁን ድጋፍ እያቀረብን ነው። ከዚህ አኳያ መልሶ ግንባታ ላይ አየተሠራ ነው፤ ይሁን እንጂ ኹሉም በአንድ ጊዜ አይገነባም። ለምሳሌ ሥራ ያልጀመረ የጤና ተቋም የለም፤ ነገር ግን በተሟላ አይደለም አገልግሎት የሚሰጡት። ምክንያቱም ትልልቅ ማሽኖች ስለተዘረፉ እነሱን ለመተካት ጊዜ ይወሰዳል። ይህንን ሥራ የሚመራ ተቋም ተቋቁሞ በየደረጃው ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከዚህ አንጻር ጦርነት ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች ጭምር አቻ ተቋሞቻቸውን እንዲደግፉ ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሠራ ነው። ሌሎች ክልሎችም፣ የፌዴራል መንግሥቱም እንዲደግፍ እየተደረገ ሥራው እየተሠራ ነው ያለው። አብዛኛው ነገር በጥሩ መንገድ የሚገኝ ነው። ነገር ግን ከፍተኛ ገንዘብ የሚፈልግ ሥራ ነው። አንዳንዶቹ የወደሙ መሠረተ ልማቶች፣ የተሠረቁ ማሽኖች፣ የተሠበሩ ድልድዮች፣ የመድኃኒት አቅርቦቱ፣ የትምህርት ተቋማት በገንዘብ ሲተመኑ በጣም በጣም ትላልቅ ገንዘብ ነው የሚጠይቁት።

ይሄንን የፌዴራል መንግሥት ባለው አቅም፣ የክልሉ መንግሥት ባለው አቅም፣ ዕረጅ ድርጅቶች ባላቸው አቅም እየሞከርን ነው ያለነው። ከፍተኛ ገንዘብ ቢያስፈልግም በጥሩ መንገድ እየሔደ ነው። ስለዚህ በዚህ ዓመት ብቻ ወይም በሚቀጥለው ዓመት ብቻ የምንጨርሰው አይደለም፤ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ነው። ይሄንን ለማድረግ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ድርሻ ወስዶ መሥራት አለበት። የክልሉ መንግሥትም መሥራት አለበት። ማኅበረሰቡም ነጋዴውም ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች አሁንም እየተፈናቀሉ ነው። ዜጎችን ከጥቃት መጠበቅ ለምን አልተቻለም? ጦርነቱንስ እንዴት ነው መቋጨት የሚቻለው?
የአሸባሪው ኃይል አመለካከቱ ካልተቀየረና አንዳንዶቹም ለሕግ ካልቀረቡ ከረብሻና ከብጥብጥ እታደጋለሁ ብሎ ማለት የዋህነት ነው የሚሆነው። እነዚህ ኃይሎች ዓላማቸው አገር መበጥበጥ ነው፤ ካፈርኩ አይመልሰን ዓይነት ነገር። ጦርነቱ አላለቀም፤ አልተቋጨም፤ አሁንም ትንኮሳዎች አሉ። በኃይል ተይዘው ያሉ አካባቢዎች አሉ፤ አላማጣም ኮረምም እንደተያዙ ናቸው። በሰሜኑም እስከ አዲርቃይ ደረስ የጠላት ኃይል ያለበት ነው።

ጠላት የያዛቸው አካባቢዎች ላይ መያዝ ብቻ ሳይሆን ሕዝብ ያፈናቅላል፤ይገድላል። በተመሳሳይ አሁን ትግራይ ክልል ውስጥ ሰው እየተፈናቀለ እየመጣ ነው። ቅድም ያልኩህ ቁጥር እነዚህንም ጨምሮ ነው። የጦርነቱን ዝርዝር በተመለከተ የክልል መንግሥት ድርሻ አይደለም። ለምንድን ነው የቆመው የሚለውን የፌዴራል መንግሥት ነው መመለስ የሚችለው።

ጦርነቱ በምን መልኩ ይቋጭ ይሆን የሚለውን በተመለከተ፣ የፌደራል መንግሥት አማራጮችን ከፍቶ እየጠበቀ ነው ያለው። የውጭውንም ጫና ለመቋቋም፣ የወዳጅ አገሮችንም ምክር ሰምቶ ተጋግዞ ጦርነቱ እንዲቋጭ ነው የምንፈልገው። ከእኛ አኳያ ግን እንደ አማራ ክልል ጦርነቱን ፈልገን አይደለም የገባንበት። የአማራ ሕዝብ ጦርነት አይፈልግም፤ የአማራ ሕዝብ የሚፈልገው ልማት ነው። የአማራ ሕዝብ የወሰንና የማንነት ጥያቄው እንዲመለስልት ነው የሚፈልገው። በእነዚህ ላይ አይደራደርም። በማንነትና በወሰን ጥያቄዎች ላይ የአማራ ሕዝብ አይደራደርም።

- ይከተሉን -Social Media

አነዚህን ፍላጎቶች የሚያስጠብቅ የትኛውም መፍትሔ እስከ መጣ ድረስ ወደ ጦርነት አንገባም። አሁንም በትዕግስት እየጠበቀ ነው የአማራ ሕዝብ። ትንኮሳ ሲደረግም እየተከላከለ መፍትሔ እየፈለገ ነው። ጦር ጠማኝ ብሎ ጦር የሚገጥም ሕዝብ አይደለም የአማራ ሕዝብ። ወንድሞቹ ጋር የሚጣላ አይደለም፤ ጦርነት ጎጅ እንደሆነ ይረዳል፤ እኛም እንረዳለን። እንደ መንግሥት ጦርነት አውዳሚ ነው፤ ከወዲያም ከወዲህም እየጎዳን ነው ያለው። ከትግራይ በኩልም ጉዳት ያደርሳል ከእኛም በኩል ጉዳት ያደርሳል። ስለዚህ ሲደመር የአገር ጉዳት ነው የሚሆነው።

የአማራ ሕዝብ ጸቡ ከሕወሓት ቡድን ጋር ነው። የአማራ ሕዝብ ሠላም ይፈልጋል፤ የትግራይ ሕዝብም ሠላም ይፈልጋል፤ በጋራ መልማት ይፈልጋል፤ በማንነቱ ከመጣህበት ነው ሕዝብ የማይወደው። የአማራ ሕዝብ በማንነቱ ተገፋ፣ ተጎሳቆለ። ጦርነቱ በሠላማዊ መንገድ መጠናቀቁ አይቀርም። ጦርነት ዕድሜ ልኩን ሊቀጥል አይችልም። የአማራ ሕዝብ ሠላም ነው የሚፈልገው። ጦርነት ምን ያደርጋል? ግን ደግሞ በማንነትና ወሰን ጉዳዮች አንደራደርም።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና ሠራተኞች የክልሉ ሕዝብ ችግር ላይ በወደቀበት ወቀት የፓርቲውን ገንዘብ በብድር ሥም መውሰዳቸው ተሰምቷል። ከዚህ አንጻር የክልሉ አመራሮች የተዓማኒነትና የሕዝብ ወገንተኝነት እስከምን ድረስ ነው?
ብልጽግና ማለት ዐሥርና አስራ አንድ ሰው ማለት አይደለም። አማራ ብልጽግና ብለን ስናወራ የተወሰኑ አማራሮችን ማለት አይደለም። የአማራ ብልጽግና ማለት 1.9 ሚሊዮን አባላት ያሉት ነው። ይሄ ኃይል ነው ብልጽግና ማለት። ስለ ብልጽግና ገንዘብ ስናወራ ስለ አማራ ሕዝብ ገንዘብ አይደለም እያወራን ያለነው፤ የሕዝብ ገንዘብ ተብሎ መወራቱ ስህተት ነው። በ1.9 ሚሊየን አባላት መካከል ጥቂቶቹ ሊሳሳቱ ይችላሉ፤ የጥቂቶቹ ስህተት ግን የብዙዎቹ ብልጽግና አባላት ተደርጎ መወሰዱ ስህተት ነው።

ከዚያ ቀጥሎ ታማኝነት ማለት፣ የክልል አመራር ከ200 በላይ ነው፣ ገንዘቡን ወሰዱ የሚባሉት ደግሞ ከአመራር አኳያ ስድስት የማይሞሉ ናቸው። ‹ፖለቲካሊ ፍሮንት› ላይ ያሉት ኹለት ሦስት የሚሆኑት ናቸው፤ ከዚያ ውጭ ያለው በቀጥታ መሪነት የሚያረጋግጥም አይደለም። ከዚህ አንጻር ብልጽግና ታዓማኝነቱን አጥቷል፣ ብልጽግና ለሕብረተሰቡ የመናገር ሞራል የለውም ብሎ መናገር ድንቁርና ነው። ይሄ የማነሳው በሚዲያ ስለምሰማው ነው። ይህ ሕዝብ መናቅ ነው፤ ሌላውን አመራር መናቅ ነው፤ ይሄ መታወቅ አለበት።

ኹለተኛ ነገር የስርቆት ባህሪ (ኢለመንት) የለውም ይሄ ነገር። የአሠራር ስህተት ነው የገጠመው። ስርቆት ቢሆን እንደዚህ አይሰረቅም። የአሠራር ስህተት ግን ገጥሞታል፤ አሠራሩ ይታረም ብሏል ፓርቲው። አሠራሩ ይታረማል፣ በአሠራሩ መሰረት የሚጠየቀው ይጠየቃል። የአሠራር ስህተቶች መታረም አለባቸው፤ የአሠራር ስህተቱ ኦዲት ተደርጎ የሚታረመው ይታረማል። ከዚያ ውጭ የአማራን ፖለቲካ ለመረበሽና ለማስናቅ የተደረገ ጫጫታ፣ የወሰዱ ሰዎችም ቀድመው የጮኹበት ነው። ይሄ የአማራን ሕዝብን፣ የበላይ አመራሩንም የሚወክል አይደለም። ስህተት ነው ማለት ነው።

ጫጫታው፣ በአመራሩ ውስጥ ልዩነት እንደተፈጠረ የሚወራው፣ በዚህ የተፈጠረ አንድ ነገር የለም አመራሩ ውስጥ የማረጋግጥልክ። ነገሮችን ከጥቅሙ ጉዳቱን ዕያየን ነው መምራት ያለብን።

ሕወሓት ወደ ትግራይ ከተመለሰ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች የፋኖ አባላት ጋር እስከ መገዳደል የደረሰ ግጭት እየታየ ነው። ግጭቶችና መገዳደሎች የተፈጠሩበት ምክንያት ምንድን ነው?
እዚህ ጋር የተዛባ አመለካከት አለ፣ በተሳሳተ መንገድ የሚረጭ፣ ይሄ ለምን እንደሆነ ይገባኛል። የመጀመሪያው ጉዳይ የክልሉ መንግሥት ለፋኖ ክብር አለው በደንብ መታወቅ ያለበት። ፋኖነት መጠሪያውም የጋራችን ነው፤ የአማራ ክልልም ብቻ አይደለም የፋኖ ስም፣ ጀግኖች ያኔ በወቅቱ በውጭ ጠላት ወረራ ጊዜ አገርን አናስወርርም ብለው፣ እምቢ ብለው ፋኖ ሆነው የዘመቱ ጅግኖች መጠሪያ ነው። ይሄ ታሪካዊ ሥማችን ነው። ስለዚህ በዚህ ታሪካዊ ሥማችን እየተጠቀመ፣ የአሁኑ ዘመንም በአያቶቹ ሥም እየተጠቀመ በሕልውና ዘመቻው ወቅት ከፍተኛ ተጋድሎ ፈጽሟል። አብሮ ታግሏል፤ አብሮ ታግሏል ብቻ አይደለም አሁንም ምሽግ ውስጥ ነው ያለው ትክክለኛው ፋኖ። አሁንም እየታገለ ነው ያለው ፋኖ። ይሄ መታወቅ አለበት መጀመሪያ።

ስለዚህ ለዚህ ዕውቅና የመስጠትና የመደገፍ ሥራ የመንግሥት ሥራ ነው። ከሌሎች በተለየ አያየውም መንግሥት። ከዚያ ውጭ ግን በማኅበራዊ ሚዲያ የማያቸው ነግሮች፣ አንደኛ መንግሥት ፋኖ ላይ ያደረገው ዘመቻ የለም። ስለ ፋኖ ከሆነ የምናወራውን ፋኖን ያስተባብራል እንጅ መንግሥት ፋኖ ላይ የወሰደው ተልዕኮ የለም። በጣም በድፍረት እኮ ነው የሚነሳው። መንግሥት ፋኖን ለምን ብሎ ይገላል? የገደልነውም፣ የምንገለውም እንዲህ ዓይነት ሐሳብ መንግሥት የለውም።

- ይከተሉን -Social Media

ግጭቶች ተፈጥረው ከፋኖም ከመንግሥትም የተገደለ ሰው የለም?
ውሸት ነው። እነሱን ፋኖዎች የምትል ከሆነ ተዛባህ ማለት ነው፤ ፋኖ እስረኞችን የሚበትን አይደለም። እስረኛን ለምን ያስፈታል ፋኖ? ፋኖ እስረኞች ያስፈታል እንዴ? መንግሥትን ይጻረራል እንዴ ፋኖ? ይሄ ከሆነ ፋኗችሁ ሚዲያ የሚራገበው ከሆነ ፋኖ አይደለም እሱ፣ እሱን ፋኖ አንለውም። ይሄንን ፋኖ ብለህ እነአጋየን ኹላ አብረህ ለተምካቸው። ምሽግ ያሉ ጀግኖችን፣ ለሞቱት ፋኖዎች ጭምር ክብር አለመስጠት ነው። እስረኛ ልፍታ ብሎ መጣ፣ እኛ ይሄን ፋኖ አንለውም፤ ይዛባላ ፋኖ እንዳንለው። ታች ጋይንት እስረኛ ለማስፈታት ታጥቆ ኃይል መጣ፣ ይሄን ወንበዴ ቡድን ነው። ይሄንን መንግሥት ሥርዓት ማስከበር አለበት፣ ይሄን ዝም ብንል ወዴት ነው የምንሄደው? መቀጠል ይችላል እንዴ ክልሉ? ይሄ ሕይወት መቀጠል ይችላል? አይቻልም እኮ፣ ስለዚህ ልክ አይደለም።

ይሄንን ፋኖ እያልን ከሆነ በጣም እየተዛባን ነው ማለት ነው። ስለዚህ እስረኛ ለማስፈታት ሲል ስርዓት ለማስከበር የተኩስ ልውውጦች ነበሩ፣ በዚህ መሀል ሕይወቱ ያለፈ ሰው አለ። ከጸጥታ ኃይሉም፣ ከኹለቱም መሆን ያልነበረበት ነው። ማንም ሰው የሆነ ኹሉ አንዲሞት አንፈልግም። ነገር ግን ሥርዓት ማስከበር አለብን። የአማራ ክልል ማላገጫ መሆን የለበትም።

ሕገ ወጥ መሣሪያ ይዞ የሚያዘዋውር አካል ፋኖ ነው ከተባለ ስህተት ነው። በከተማ መሀል መሣሪያ የምታዘዋውርና ብሬን ተሸክመህ የምትገባ ከሆነ፣ ይሄ የፋኖ ሥራ አይደለም። ፋኖ ሥነ ምግባር ያለው ነው፤ መኪና ሸጠው እኮ ፋኖ የሆኑ ሰዎች አሉ። ንብረታቸውን በሬያቸውን ሸጠው እኮ የሚታገሉ አሉ። ፋኖ በጦርነት ጊዜ አብሮ ገብቶ መንግሥትን የሚደግፍ፣ በሠላም ጊዜ ሥራውን የሚሠራ ነው።

ግጭቶች አሉ፤ የጎረምሶች ግጭት፣ የመዝረፍ ፍላጎቶች፣ መሣሪያ የማዘዋወር ፍላጎቶች፣ በሕገ ወጥ ድርጊቶች የመሳተፍ ፍላጎት፣ እነዚህም በፋኖ አይደለም የምገልጻቸው። እኔ የማወራህ የመንግሥት አቋም ነው፤ የግሌ አይደለም። እነዚህ ፋኖዎች አይደሉም። እነዚህ ሽፍቶች ናቸው ወይ ወንበደዎች ናቸው። መንግሥት ሥርዓት ማስያዝ አለበት። ሕዝቡ ገና አልገባውም፤ ቀላቅሏል። ፋኖንም ከምኒሜና ሌባው ጋር ቀላቅሎታል። የጸጥታ ኃይሉን የሆነ ያልሆነ ሥያሜ ሰጥቶታል። ስለዚህ ትንሽ ይሄን እስከትለይ ድረስ መረጋጋት፣ ማወያየት ያስፈልጋል።

እነዚህ ሰዎችን እኮ እኛ ይሙቱ፣ ይሰደዱ እያልን አይደልም። እንዲህ ዓይነት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ካሉ በዚህ አጋጣሚ እራሳቸውን ያርሙ። እራሳቸውን አርመው የሚፈልጉትን ጥያቄያቸውን በዴሞክራሲዊ መንገድ ያቅርቡ። ሚኒሻ መሆን የሚፈልግም ካለ ሚኒሻ መሆን ይቻላል፤ መስፈርቱን እስካሟላ ድረስ። በተለይ የታገሉ ፋኖዎቻችንን እኛ ሥራ እንፈጥራለን፣ እናግዛለን፣ እንደግፋለን፣ ከዚያ ውጭ ግን በፋኖ ስም መነገድ አይቻልም።

የክልሉ መንግሥትና የፋኖ አባላት ወደፊት የሚኖራቸው ግንኙነት ምንድን ነው የሚሆነው?
ቅድም እንዳልኩት መልካም ሥም ነው ፋኖ። ፋኖ ጠላትን የሚዋጋ ነው፤ ፋኖ አገሩ እንዲከበር የሚፈልግ ነው፤ ፋኖ ለሕግ ተገዥ ነው። ከመንግሥት በላይ ሳይሆን፣ መንግሥትን የሚገዳደር ሳይሆን፣ ከመንግሥት በታች ሆኖ የሚያገለግል ነው። በበጎ ፈቃድ የሚሠራ ሥራ ነው ይሄ። የአያቶቹ ታሪክና ተግባር ተዋርሶት ፋኖ የሆነ ማለት ነው። ይሄ መልካም ነገር ነው፤ ይሄንን የመሰለውን ነገር መንግሥት ይደግፋል፤ ያደራጃል፤ አማራ እንዲከበር ይሄንን ይደግፋል። አንዲህ ዓይነቶችን ዕውቅና ይሰጣል፤ ሲታገሉ ለሞቱትም ካሳ ይከፍላል። እንደሌላው ኹሉ፣ በየተሠማሩበት ሥራ ኹሉ መንግሥት ለሌሎች አካላት የሚያደርገውን ድጋፍ ለእነዚህም ያደርጋል፤ ይሄ የመንግሥት አቋም ነው።

ፋኖዎችን ስምምነት አለን እናገኛቸዋልን። ወደፊትም ውይይቶች ይኖሩናል፤ ከአሁን በፊትም ውይይት አድርገን ነበር። እነዚህ አካላት መልክ መያዝ አለባቸው፤ ። ሥርዓት አስካከበሩ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ መንግሥት ያደርጋል። ከዚህ ውጭ ያለው ነው ችግር። የመንግሥት ፍላጎት ተቀራርቦ መሥራት ነው። ስህተቶችን ማረም። መንግሥት ደግሞ ስልጣን አለው አይደል ሕግ ሲያስከብር ሕግ እንዲከበር ተባባሪ ነው መሆን ያለብህ።

መንግሥትን አትንካኝ እኔ ነኝ ጀግና ልትል አትችልም። እንደዚህ ዓይነት አገርም የለም በዓለም። እንደዚህ ከሆነ ቢተው ነው የሚሻለው፤ ከተውክ ደግሞ ትርምስ ነው የሚፈጠረው፤ ትርምስ ደግሞ አገር ያጠፋል። አቅም ስለሌለው አይደለም መንግሥት ነገሮችን በትዕግሥት የሚያልፈው። የተዛባ አመለካከት ስላለ፣ የተለያየ ፍላጎት ስላለ ቅድሚያ መረዳዳትና ግንዛቤ ይቀድማል።

ሰው መሞት የለበትም፤ ግጭት መነሳት የለበትም፤ ምክንያቱም እኛ አይተነዋል ከዚህ ቀደም። ከአሁኑ ቀደም የተፈጠሩ ግጭቶች ጥቅም ነው ያጣንባቸው፣ ትልቅ ነገር ነው አማራ ያጣባቸው። ይሄንን በጠላት ፈርጀህ፣ ይሄንን በወዳጅ ፈርጀህ እርስ በእርስህ መጋጨት ትክክል አይደለም። ስለዚህ መጀመሪያ በደንብ ጠንከር ብሎ መምከሩ ላይ፣ ማስተማሩ ላይ ትቀድምና ቀጥሎ ደግሞ ሕጋዊ ዕርምጃውን ማስከተል ነው።

አሁን ይሄን ስላልኩ ብዙ የሚጮህ አለ፣ የሚጮሁት ለአንዳች ፍላጎት (ፕርፐዝሊ) ነው። ሥርዓት አልበኝነት የሚፈልግ ኃይል ነው የሚጮኸው። በሥርዓት አልበኝነት ውስጥ ገንዘብ የሚነግድ ኃይል አለ፤ በሰው ደም ገንዘብ የሚያገኝ አለ።

ሌላው በማናውቀው ነገር ትንታኔ ባንሰጥ ጥሩ ነው። አሁን በማናውቀው ነገር ላይ ትንታኔ መስጠት ነው የበጠበጠን። ስለ ፋኖ የሚተነተነው 90 በመቶ ውሸት ነው። መንግሥት ያልያዘውን አቋም የመንግሥት አቋም ነው ይባላል። የመንግሥት ፍላጎት ያልሆነ እንደ መንግሥት ፍላጎት ይወጣል። መንግሥት ሠላም ነው የሚፈልገው። መንግሥት የሚፈልገው ፋኖ ለሠላም ዘብ እንዲቆም ነው። ጦርነት ባለ ጊዜ ወደ ጦርነት ጠላትን እንዲመታ ነው፤ፋኖ ባልተፈቀደ ቦታ መሳሪያ ይዞ የሚንቀሳቀስ ኃይል አይደለም። ማንኛውም የታጠቀ ኃይል በመንግሥትም ከተፈቀደለት የጸጥታ ኃይል ውጭ መሳሪያ ታጥቆ ሕዝብ በሚበዛበት አካባቢ ፣አጋለግሎት መስጫ አካባቢ መንቀሳቀስ ተገቢነት የሌለው ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች