በጉባዔው ማብቂያ ላይም ባለ 5 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል
ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በ2ተኛ መደበኛ ጉባኤው ፓርቲውን እና አገሪቷን የሚመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ በስፋት ተወያይቶ ለፓርቲው ቀጣይ የትግል ምዕራፍ እስትራቴጂና አቅጣጫ ማስቀመጡን በዛሬው ዕለት አስታወቀ።
በዚህም መሰረት ፓርቲው በጉባዔው ማብቂያ ላይም ባለ 5 ነጥብ የአቋም መግለጫ ማውጣቱን ገልጿል።
ኦፌኮ በጉባዔው ተሳታፊዎች መውጣቱን ያስታወቀው ባለ 5 ነጥብ የአቋም መግለጫም እንደሚከተለው ቀርቧል:-
1/ በኦሮሞ ቄሮ እና ቀሬ መስዋዕትነት ከ4 ዓመታት በፊት የመጣው ለውጥ አገራችንን ወደ አዲስ የሰላምና ዲሞክራሲ ምዕራፍ ያሸጋግራል የሚል ተስፋ የነበረን ቢሆንም፣ የለውጡ ሒደት ተቀልብሶ፣ ወደ ዲሞክራሲ ሊደረግ የነበረው የሽግግር እድል በመባከኑ ምክንያት ወደ ተስፋ መቁረጥ ፣የእርስ በርስ ጦርነትና የአገር መፍረስ አደጋ የተጋረጠብን መሆኑ በጣም አሳዝኖናል።
አገራችንን ከመፍረስ አደጋ ለማዳን ሲባል፣ ወደ ዲሞክራሲያዊና ህብረ-ብሔራዊ ስርአዓት ግንባታ መስመር መመለስ አማራጭ የሌለው ብቸኛ መፍትሄ መሆኑን፣ ባለፉት አራት አመታት የተሰሩ ስህተቶችና እሱንም ተከትለው የመጡት አላስፈላጊ ውጤቶች ህያው ምስክሮች ናቸው። ስለዚህም ፓርቲያችን እና አመራሩ ባለፉት ጥቂት አመታት የያዟቸው አቋሞች ከፍተኛ መስዋዕትነት ያስከፈሉን ቢሆንም ትክክለኛ መሆናቸውን ዳግም እናረጋግጣለን።
2/ ባለፉት ሶስት አመታት በአገራችን የተከሰቱና ለአያሌ ንፁሃን ይህወት መቀጠፍ፣ ለከፍተኛ ንብረት ውድመትና፣ ለዜጎቻችን ክብር ውርደት የዳረጉን የእርስ በርስ ጦርነቶች እጅግ በጣም አዝነናል። ከጥቂት ወራት ወዲህ የጦርነት ነጋሪት ከመጎሰም በመውጣት ለእስር በእርስ ጦርነቶቹ ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ መንግስት ያደረገውን የአካሄድ ለውጥ በበጎ የምንመለከተው ነው፡፡
በዚሁ መሰረት በቅርቡ የፌዴራሉና የትግራይ ክልላዊ መንግሰት ጦርነትን ለማቆም ያሳለፉት ውሳኔ በፍጥነት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲለወጥ፣ ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታዎች ለህዝቡ እንዲደርሱና ግጭትም መልሶ እንዳይቀሰቀስ የሚያደርጉ ሥራዎች እንዲሰሩ በአፋጣኝ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለፌዴራል መንግስትም ሆነ ለትግራይ ክልላዊ መንግስት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
3/ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ያለውን ጦርነት ለማስቆም እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን የምናደንቅ ቢሆንም፣ ለባለፉት ሶስት አመታት በላይ ኦሮሚያን እያመሰ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት የሚገባውን ትኩረት ያለማግኘቱ በእጅጉ አሳዝኖናል። ስለዚህ የፌዴራሉ መንግሰት የሰላም እጂን ለትግራይ ክልል እንደዘረጋ ሁሉ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር የገባበትን ጦርበት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ላይ ሳይዘገይ እንዲደርስ እናሳስባለን። ሰላማዊ የሆነች ኦሮሚያ ሳትኖር አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ያላትን ኢትዮጵያን ማሰብ እንደማይቻል ሊሰመርበት እንደሚገባ አፅኖት ሰጥተን እናሳስባለን።
4/ ፓርቲያችን እየተካሄደ ላለው የእርስ በርስ ጦርነት መሰረታዊ ምክንያት የሆኑትን የፖለቲካ ልዩነቶች ለመፍታት እንዲቻል ብሔራዊ ምክክር እንዲካኼድ ሲማፀን ቆይቷል። ምክራችንን ሊሰማ የፈለገ አካል ግን አልነበረም። ዛሬ በሺህ የሚቆጠር ህይወት ከተቀጠፈና በቢሊዮኖች የሚገመት ንብረት ከወደመ በኋላ መንግስት
የብሔራዊ ምክክር አስፈላጊነትን አምኗል። ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ ባወጣናቸው የአቋም መግለጫዎች እንደገለፅ ነው፣እየተካኼደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት መሃል አሁን ባለው ተጨባጭ ብሄራዊ ምክክር ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች የሉም።
ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያላካተተና ገለልተኝነት እንዲሁም ተዓማኒነት በሌላቸው አካላት የሚመራ ብሔራዊ ምክክር የአገቱን ችግሮች ይፈታል ብለን አናምንም። የተሳካ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ቁርጠኝነቱ ካለ ግን ከዚህ በታች የተመለከቱት ጉዳዮች መፍትሄ ይሻሉ፥
ሀ/ በኹሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭት እንዲቆም በማድረግ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ፤
ለ/ ኹሉም የፖለቲካ እስረኞች በተለይም ደግም ባሁኑ ጊዜ በተለያዩ እስር ቤቶች ግፍ እየተፈጸመባቸው ያሉ የኦፌኮና የኦነግ አመራር አባላት የሆኑ የፖለቲካ እስረኞች ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ማድረግ፥
ሐ/ መንግስት የእርስ በርስ ጦርነቱ ላይ እየተሳተፉ ካሉ የታጠቁ ሃይሎች ጋር ድርድር በመጀመርና ግጭቶች እንዲቆሙ በማድረግ፣ ያሉትን የህግ ማነቆዎችንም ሙሉ በሙሉ በማንሳት ብሔራዊ ምክክር ላይ እንዲሳተፉ ሊጋብዛቸው ይገባል፡፡
መ/ የብሄራዊ ምክክሩ አዋጅ ሊዘጋጅ የሚገባው በጋራ ስምምነት ሆኖ ኮሚሽነሮችም ምክክሩ ላይ በሚሳተፉ አካላት ሊመረጡ ይገባል፡፡
5-በዚህ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከቄዬያቸው ተፈናቅለው ለአስከፊ ችጋር ተጋልጠው ይገኛሉ። ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የረድኤት ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ለተጎጂዎች ሊደርስላቸውና ህይወታቸውን ሊታደግ ይገባል። በተመሳሳይም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ድርጅቶች የሚለግሱት ህይወት አድን እርዳታዎች ለተጎጂዎች ባግባቡ መድረሳቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
በመጨረሻም በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ የትግል ጓዶቻችን በሙሉ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩና ከሁሉየኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር አጋርነታቸውን ይበልጥ እንዲያዳብሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) 2ተኛ መደበኛ ጉባዔ ተሳታፊዎች
መጋቢት 18/2014
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



