ሐሙስ መጋቢት 22 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት በዋለዉ ችሎት ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ባቀረበዉ የዋስ ይገባኛል ጥያቄ ላይ ዉሳኔ ለማሳለፍ ለመጋቢት 27 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ተገለፀ፡፡
የተራራ ኔትዎርክ በይነ-መረብ መገናኛ ብዙሃን ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከታሰረ ዛሬ መቶ 10 ቀናት እንደሆነው የገለፁት ቤተሰቦቹ፣ እስካሁን ክስ እንዳተመሰረተበትና የዋስ ይግባኝ ጥያቄዉም ዉሳኔ እንዳልተሰጠው ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ መጋቢት 1 ቀን 2014 በገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት፣ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ አቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ጋዜጠኛው ላይ ክስ እንዲመሰርት ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
ጋዜጠኛዉም በጠበቃዉ በኩል መጋቢት 02 ቀን 2014 በዋስ እንዲለቀቅ የዋስ መዝገብ ከፍቶ ነበር፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዋስ መዝገቡን ከተመለከተ በኋላ ለመጋቢት 08 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን፤ በዕለቱም ፍርድ ቤቱ በድጋሜ ለመጋቢት 13 2014 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
መጋቢት 13 ቀን 2014 የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዝገቡን አይቶ ድጋሜ ለ15 ቀን ቀጠሮ እንደሰጠው ቤተሰቦቹ ተናግረዋል፡፡
በመጋቢት በ15 ቀን 2014 ፍርድ ቤቱ በዋለዉ ችሎትም መዝገቡን ተመልክቶ የፖሊስ ምርመራ ዉጤት ይምጣልኝ በማለቱ ለትናንት ለመጋቢት 20 ቀን 2014 ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡
በትናንትናው ዕለትም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዋለዉ ችሎት የፖሊስ የምርመራ ዉጤት እንደደረሰዉ ቢገልጽም፤ ፋይሉ መመርመር ስላለበት ለመጋቢት 27 ቀን 2014 ዉሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ መስጠቱን ተራራ ኔትዎርክ ዘግቧል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



