በምሽት ነዳጅ በርሜል ሲሸጡ የተገኙ ሦስት ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለፀ

0
904

ሐሙስ መጋቢት 22 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በፈጠሩና በምሽት በበርሜል ነዳጅ ሲሸጡ የተገኙ ሦስት የነዳጅ ማደያዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገባቸው ምርቶች መካከል ነዳጅ መሆኑን የገለጸው ቢሮው፤ ከሥርጭት ጋር ተያይዞ አንዳንድ ማደያዎች የሚፈጥሩትን እንግልትና አሻጥር ፈር ለማስያዝ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወስድና ብልሹ አሰራርን እንደማይታገስ ገልጿል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አደም ኑሪ ከነዳጅ ማደያ ባለሃብቶች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ከሥርጭት ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ማደያዎች የሚፈጠረው ብልሹ አሰራር፥ የምርት ሥርጭት ፈተና መሆናቸውን አብራርተዋል።

አክለውም ያልተገባ ጥቅም በመፈለግ እጥረቱን በሚያባብሱ የነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስረድተዋል።

ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በፈጠሩና በምሽት በበርሜል ነዳጅ ሲሸጡ የተገኙ ሦስት ማደያዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰዱንም አደም ኑሪ ተናግረዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል የነዳጅ አቅርቦትን በማሳደግና ቁጥጥሩን በማጠናከር ሌሊት ነዳጅ በሚሸጡት ላይ የመጠን ማሻሻያ እንደሚደረግና፤ በዘመናዊ የመረጃ ዘዴ ማደያዎች እለታዊ መረጃን ለቢሮው እንዲያሳውቁ ማድረግ የሚያስችል አሰራር የሚዘረጋ መሆኑንም የጋራ መግባባት ላይ መድረሱን ከቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

በከተማዋ ከ134 የነዳጅ ማደያዎች 117 ማደያዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
______________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here