በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ያግዛል የተባለን የተሽከርካሪ ፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ለመግጠም የሚያስችለውን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱን የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን አስታወቀ።
ለመንገድ ትራፊክ አደጋ መበርከት ምክንያት ከሚባሉት ውስጥ ቀዳሚው ከተወሰነው የፍጥነት ገደብ በላይ ማሽከርከር ነው ያለው ባለሥልጣኑ አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን ቀንሰው በጥንቃቄ በማሽከርከር አደጋውን መቀነስ እንዲችሉ ከማስገንዘብ ተሻግሮ መሣሪያዎቹን መግጠም የግድ ማለቱን ጠቁሟል።
በተሽከርካሪ ላይ የሚገጠመው የተቀናጀ የተሽከርካሪ ፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ከዓለም ዐቀፍ ስርዓት አቅጣጫ (GPS) ጋር የተጣመረ ሆኖ እንደተሽከርካሪው ሁኔታ ወደ ሞተሩ የሚገባውን ነዳጅ ወይም አየር በመቀነስ በሕግ ከተደነገገው በላይ እንዳይፈጥን የሚቆጣጠር መሆኑንም አሳውቋል፡፡
መሣሪያው የምርት ዘመናቸው እንደ አውሮፓውያኑ 2000ና በኋላ ያሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ይተገበራል፡፡ በሌሎቹ ላይ ባለሥልጣኑ በቀጣይ ይወስናል ተብሏል፡፡
በዚህ ሳምንት በኹለት ቦታዎች ብቻ በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ከ20 በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011