አርብ መጋቢት 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአማራና አፋር ክልሎች በህወሃት ቡድን ከፍተኛ ውድመት አጋጥሞት የነበረውን የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችና የኦፕቲካል ፋይበር ገመዶች የመጠገን ሥራ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሰታወቀ።
በክልሎች የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ለመጠገን ለመለዋወጫ አቅርቦት የወጣውን ወጪ ሳይጨምር ለሥራው ብቻ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ተገልጿል።
የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ጥገናው በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ለተወሰኑ ሰዓታት ኤሌክትሪክ በማቋረጥ ሲሠራ ቆይቶ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገልጿል፡፡
ከደብረሲና – ሸዋሮቢት – ከሚሴ – ኮምቦልቻ – አቀስታ – ዓለም ከተማ ባለ132 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር፤ ከደብረብርሃን – ኮምቦልቻ – ሠመራ እና ከኮምቦልቻ – አላማጣ እስከ ቆቦ ድረስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመር እንዲሁም ከደብረታቦር እስከ ጋሸና ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር በሚያልፍበት አካባቢ የሚገኙ ከተሞችና መንደሮች ላይ ከህዳር 24/2014 ጀምሮ በተደረገው ጥገና አካባቢዎቹ ኤሌክትሪክ መልሰው እንዲያገኙ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ከደሴ – ወልዲያ የ ባለ 66 ኪሎ ቪልት መስመር ጥገና በማካሄድ የወልዲያና አካባቢው ኃይል እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡
የመልሶ ጥገና ሥራውን ከተቋሙ ስምንት ሪጅኖች የተውጣጣ የጥገና ቡድን በከፍተኛ ርብርብ ሲያከናውን መቆየቱም ተገልጿል፡፡
በአማራና አፋር ክልል የደረሰውን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ለመጠገን ለመለዋወጫ አቅርቦት የወጣውን ወጪ ሳይጨምር ለሥራው ብቻ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n





