አርብ መጋቢት 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው አለመመለሳቸውን የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አህመድ ሰኢድ ገለፀዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኩ በሕወሃት ታጣቂ ቡድን ከደረሰበት ውድመት ሙሉ በሙሉ ባለማገገሙ እና የአጎአ እድል በመሰረዙ በሥሩ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በቀደመው አቅማቸው ልክ እያመረቱ አይደለም ተብሏል፡፡
በመሆኑም 1 ሺህ 214 የፓርኩ ሰራተኞች አሁንም ወደ ሥራ ገበታቸው እንዳልተመለሱ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
በፓርኩ ውስጥ ሥራ ላይ ካሉ ሼዶች መካከል በተለይ ካልሲ እያመረተ ወደ አሜሪካ ገበያ ይልክ የነበረው ፍአንላይ የተባለ የቻይና ኩባንያ ከጦርነቱ በኋላ አገግሞ ሥራ ቢጀምርም፤ በጥቂቱ ብቻ እየሰራ በመሆኑ በርካታ ሰራተኞቹ ወደ ሥራቸው እንዳልተመለሱ ተገልጿል፡፡
የወንዶች ሙሉ ልብስ እያመረተ ለአሜሪካ ገበያ የሚልክ የቻይና አሜሪካ ኩባንያ እና የሴቶች ቦርሳ እያመረተ እንዲሁ 95 በመቶ ለአሜሪካ ገበያ የሚያቀርብ ኩባንያ ሥራቸውን የተሻለ እየከወኑ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት ከሰጠቸው የቀረጥና ኮታ ነፃ እድል ኢትዮጵያን ማስወጣቷ ተከትሎ ሁለቱ ኩባንያዎች የገበያ ችግር እንደገጠማቸው ሸገር ሬዲዮ ከኩባንያዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ሰምቻለሁ ሲል ዘግቧል፡፡
የገበያው ሁኔታ ሲስተካከልና በፓርኩ ውስጥ እየሰሩ ያሉ ኩባንያዎች በህወሃት አማካኝነት ከደረሰባቸው ውድመት አገግመው በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ፤ አሁን የተቀነሱ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰራተኞች ወደ ሥራቸው ይመለሳሉም ተብሏል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



