ስስ የላስቲክ ዕቃ መያዣዎችን መጠቀም ከ2500 ብር በላይ የሚያስቀጣ ሕግ ሊጸድቅ ነው

Views: 305

አፈር ውስጥ ገብተው በቀላሉ የማይበሰብሱ እና መጠናቸው ከ0.03 ሚሊሜትር በታች የሆኑ ስስ የላስቲክ ዕቃ መያዣዎችን (ፌስታሎችን) ሲጠቀሙ የተገኙ ግለሰቦች ከ2 ሺሕ 500 ብር ጀምሮ ቅጣት ሊጣል እንደሆነ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ሙሉ በሙሉ እንዳይመረቱና ከውጪ እንዳይገቡ በታገዱ የማይበሰብሱ ስስ ፌስታሎችን ሲጠቀም የተገኘ ግለሰብ የሚቀጣበትን አዲስ አዋጅ አርቅቆና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ እየተገመገመ ሲሆን፣ በቅርቡ እንደሚጸድቅም ይጠበቃል ሲል ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በኮሚሽኑ የደረቅ እና አደገኛ ቆሻሻ ሕግ ተከባሪነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ግርማ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በ1999 የወጣው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ ለ13 ዓመት ያገለገለ ከመሆኑ ጋር፣ ተያይዞ ክፍተቶች ስለነበሩበት መሻሻሎች እንዳስፈለጉ ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም ከዚህ በፊት ከላይ ወደ ታች የነበረው አተገባበር ከታች ወደ ላይ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በዚህም ከዚህ ቀደም አምራቾችን ይቆጣጠር የነበረው ሕግ፣ ምርቱን ለማምረት ብዙ ቦታ ካለማስፈለጉ ጋር ተያይዞ በቤት ውስጥ በድብቅ ስለሚመረቱ ቁጥጥሩን ደካማ እንዳደረገው አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ሕግ ተጠቃሚው ላይ ቅጣት በመጣልና እንዳይጠቀሙ በማድረግ አምራቾችን ከገበያ ማውጣት የሚል ዘዴ የመጠቀም ሂደት እንደሆነ አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም የሕግ አተገባበሩን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋና ዓላማ በአገሪቱ የሚከሰተዉን ከፍተኛ የአካባቢ ብክለት ለመግታት ኅብረተሰቡ ለአካባቢ ብክለት አደገኛ የሆኑ እና የማይበሰብሱ ፌስታሎችን እንዳይጠቀም ለማድረግ ነው ብለዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ከሌሎች አገሮች ልምድ በመነሳት መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሩ ከዚህ በፊት የነበረው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ አምራቾች ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ ሲቀሩ በሕግ የሚጠየቁበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዉ፣ አዲስ የተዘጋጀዉ አዋጅ አምራቾችን ብቻ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ የቀድሞዉ አዋጅ የነበረበትን አምራቾችን ብቻ ተጠያቂ የማድረግ ሥራን የሚያስቀርና ተጠቃሚውንም ተጠያቂ የሚያደርግ አዋጅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ግርማ እንደገለጹት፣ አዲሱ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገምግሞ ከጸደቀ በኋላ አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም በአገሪቱ ያለ ግለሰብ እንደሚጠየቅ አመላክተዋል። አዋጁ ተግባራዊ የሚሆነው የሕዝብ ተወካዮች ከሚጸድቅበት ቀን ጀምሮ ለስድስት ወራት የእፎይታ ጊዜ እንደሚኖረውና ከስድስት ወር በኋላ ተግባራዊ እንደሚደረግ አክለው አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ ኅብረተሰቡም ሆነ አምራቾች ይህ አዋጅ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር ሌሎች አማራጮችን መፈለግ የተሻለ ነገር እንዲፈጥሩና አማራጭ የምርት ውጤቶችን መጠቀም እንዲያስችል ታስቧልም ብለዋል። በተለይም አምራች ተቋማቶች አሁን እያመረቱ ያለውን ሕገ ወጥ ፌስታል ኅብረተሰቡ ቅጣት ፈርቶ መጠቀም ሲያቆም፣ ማምረት አቁመው ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወደተሻለ ምርት እንዲሸጋገሩ ይጠበቃል ብለዋል።

የስስ ላስቲኮች ማምረቻ ማሽኖች ቀላልና ከቦታ ቦታ በቀላሉ መንቀሳቀስ ስለሚችሉ ሕገ ወጥ ምርቱን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። አዋጁ ተግባራዊ ሲሆን ኅብረተሰቡንም የቅጣቱ አካል እንደሚሆን የጠቆሙት ግርማ፣ አዋጁ ተጠቃሚዎች ሌላ አማራጭ እንዲጠቀሙ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

በአገሪቱ ባሉ በተከለሉ የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታዎች ላይ 14 በመቶ የሚሆነው የማይበሰብስ ፌስታል መሆኑን የገለጹት ግርማ፣ አርሶ አደሩ በማይበሰብሱ የፌስታል ቆሻሻ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ ነው ሲሉ አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com