የማን አባል ነሽ?

0
1325

ከቀናት በፊት ለመሳተፍ እድል ባገኘሁበት አንድ ትልቅ የሚባል፣ አንጋፎች የተሳተፉበት ጥበባዊ መድረክ ላይ የተነሳ ሐሳብ ሳምንቱን አብሮኝ ነው የከረመው። ነገሩ እንዲህ ነው፤ ሴቶች በየሙያ ማኅበራቱ እየተገነጠሉ ለምን ‹የሴቶች…ማኅበር› ይፈጥራሉ የሚል ጥያቄ ተነስቶ ነው። እንደሚታወቀው በበርካታ የሙያ ማኅበራት የሴቶች ብቻ የሆኑ፣ ወንዶችን በተባባሪነት የሚያሳትፉ ማኅበራት ይገኛሉ።

እነዚህን ማኅበራት የማይደግፉ አሉ። ለምን ሴቶችም ከጀማው ጋር ሆነው፣ ወንዶችም ባሉበት ተሳትፈው ሕግና ደንብ በሚፈቅደው መሠረት በማኅበራቸው የሚፈልጉትን አይከውኑም የሚሉ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ‹የለም! ሴቶች ጥያቄያቸው ለብቻ ትኩረት ተሰጥቶት መስተናገድ ያለበት ነው። ሁሉንም ከሚያሳትፈው ኅብረት ሳንጎድል፣ የራሳችንንም ድምጽ የምናሰማበት እድል ያስፈልጋል።›› የሚሉ አሉ።

በእለቱ በመድረኩ ሁለቱን ሐሳቦች የሚያስታርቅ ሐሳብ ተሰጠ። ይህም ‹የሴቶች› የሆኑ ማኅበራት ቢመሠረቱና ቢንቀሳቀሱ ክፋትና ጥፋት የለውም፣ ማጣጣልም አይገባም። በሌላ በኩልም ሁሉም ባለበት አውድ መታገልና ከሰፊው ውስጥ አሸንፎ መውጣትም ይቻላል። ስለዚህ እንደ ዕይታ መቀበል የምንችለው ነው የሚል ነው፤ አስታራቂው መኻከለኛ ነጥብ።

በዚህ ሐሳብ መሠረት አድርጌ ልንገርሽ! እህቴ! ኹለቱም መብትሽ ነው፤ ትችያለሽ። ዋናው ለውጥ ለማምጣት መሥራትሽና ጥረት ማድረግሽ ነው። ከእህቶችሽ ጋር ብቻ ተደራጅተሸም ይሁን ወይም ወንዶችም በሚሳፉባቸው ማኅበራት አባል ሆነሽ፣ ትክክለኛውን ነገር አድርጊ። መብትሽን አታስነኪ፣ አቅምሽን አውጪ።

‹ምንድን ነው ሴቶች ሴቶች እያሉ መሰብሰብ!› እያሉ የሴቶችን መሰባሰብ የሚያጣጥሉ ሰዎች አሉ። ይህ ሊባል የሚችለው ምንአልባት ተጨባጭ ለውጥ የለም ብለው በሚያምኑ ሰዎች ይሆናል። ያንን በማሳየት ግን ሐሳባቸውን ማስለወጥ ትችያለሽ። አሸናፊነት እኔ እበልጣለሁ ወይም እኔ እሻላለሁ ማለት ሳይሆን የራስን ሐሳብ በሌሎች ላይ ማሳደር ነው የሚል ብሂል ሰምቻለሁ። ትክክል ሳይሆን አልቀረም!

አትችይም የሚሉሽን እንደምትችይ አሳይተሽ ሐሳባቸውን ካላስቀየርሽ በቀር፣ በእህቶችሽም ጋር ተደራጂ ከመላው ዓለም ሕዝብ ጋር፤ ለውጥ አይመጣም። እንደምትችይ እያወቁ ማመን የማይፈልጉትን ከራሳቸው የሕሊና ሙግት ጋር ታቆያቸዋለሽ። እንዳያሙሽ ማድረግ የምትችይው፣ እንዲቀበሉና እንዲለወጡ ለነገ ሴት ልጆችሽም የተሻለ ዓለም መፍጠር የምትችይው በአደረጃጀት ሳይሆን በሥራሽ ነው። እና የማንም የምንም አባል ሁኚ፣ ብቻ ግን ባለሽበት አብሪ፣ ለውጥ አምጪ።

የሴቶች የመብት ትግል መች ይሆን የሚያቆመው የሚል ጥያቄን አንስተን ከጓደኞቼ ጋር ተወያይተን እናውቃለን። መቼም የሚያቆም አይመስልም። ሲያቆም ግን በእርግጠኝነት ሴቶች ሴት መሆናቸው፣ ወንዶችም ወንድ መሆናቸው ሳይሆን ሁለቱም ሰውነታቸው ቀድሞ የሚታይበት ጊዜ ነው የሚሆነው። የዛ ሰው ይበለን!
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here