አርብ መጋቢት 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ዐቃቤ ህግ በቡድን ሆነው በጦር መሳርያና በተሸከርካሪዎች በመታገዝ ከባድ የውንብድና ወንጀል ፈፅመው ክስ የመሰረተባቸው ሦስት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ22 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ በፌዳራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ከባድ የውንብድና እና የግድያ ወንጀል ችሎት ተወስኖባቸዋል።
ታደለ ክንፈ߹ አንዱዓለም ጣሰውና ዋሲሁን ባየ የተበሉት ተከሳሾች የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 (1) (ሀ) እና (ለ) ߹35 እንዲሁም 671 (2) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፋቸው ነው በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ክስ የተመሰረተባቸው።
ተከሳሾቹ በቡድን በመሆን የጦር መሳርያ እና ተሸከርካሪዎችን በመጠቀም ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለማግኘት በማሰብ፤ ተከሳሾች ጫት እየቃሙ በነበረበት ወቅት የተጠና እና የሚዘረፍ ቤት ስለተገኘ እራሳችሁን አዘጋጁ ተባብለው በመስማማት ሰኔ 24/2012 ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ሲሆን ወደ ግል ተበዳይ መዓዛ ሃሚድ መኖርያ ቤት ጩቤና ሽጉጥ እንዲሁም በየግላቸው የቤት አውቶሞቢል߹ ቪትዝና ላዳ መኪኖችን ይዘው ያመራሉ።
በማስከተልም፤ ወደ ግል ተበዳይ መኖርያ ቤት በመግባት የዐቃቤ ህግ ምስክርና የጥበቃ ሰራተኛ የነበረውን ግለሰብ በፕላስተርና በፎጣ አፉን አፍነው እጅና እግሩን በማሰር ወደ ሰርቪስ ክፍል አስገብተው በያዙት ጩቤና ሽጉጥ በማስፈራራት መሬት ላይ እንዲቀመጥ ካደረጉት በኋላ፤ በመኖርያ ቤት ውስጥ የነበረችውን ዘቢባ ናስርንና የግል ተበዳይ መዓዛ ሃሚድን ወደ ሳሎን ወስደው በጩቤና በሽጉጥ በማስፈራራት አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 127 ሺህ 988 ብር የሚያወጡ ሞባይሎች߹ወርቅ እና ጥሬ ገንዘብ በመውሰዳቸው፤ በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ ተመሰርቶባቸዋል።
ተከሳሾችም በፌዳራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ከባድ የውንብድና እና የግድያ ወንጀል ችሎት ቀርበው፤ ክሱ ደርሷቸውና ተነቦላቸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠየቁ የወንጀል ድርጊቱን እኛ አልፈፀምንም ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሾችን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ የሚያስረዱ ዘጠኝ የምስክሮች ቃል የሰነድና ገላጭ ማስረጃዎችን በማቅረብ አሰምቷል።
ሆኖም ተከሳሾች በዐቃቤ ህግ ማስረጃ የቀረበባቸውን ክስ በመከላከያ ማስረጃ መከላከልና ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል፡፡
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ መጋቢት 21/2014 ባስቻለው ችሎት ተከሳሾችን ያርማል፤ አሁን አሁን እየተባበሰ የመጣውን ከባድ የውንብድና ወንጀል እየፈፀሙ ያሉና ለመፈፀም የሚያስቡ ወንጀለኞችን ያስተምራል ሲል እያንዳንዳቸው በ22 ዓመት ፅኑ እስራትና እንዲቀጡ መወሰኑን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



