10 ሺዎቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ምን አሉ?

0
1156

በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀው ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የወጡ 10 ሺሕ ተማሪዎች፣ በበጎ አድራጎት በየክልሉ በመዘዋወር በተለያዩ ዘርፎች ማኅበረሰቡን ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል።
በጎ ፈቃደኞቹ በየክልሉ በመዘዋወር የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ማኅበረሰባቸውን ማገልገላቸውን የሰላም ሚኒስቴርም በየወቅቱ በሚሰጠው መግለጫ አመላክቷል። በጎ ፈቃደኞቹ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡ ሲሆኑ፣ ለማኅበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ከመሠማራታቸው በፊት የ10 ቀናት ሥልጠና ተሰጥቷቸው። ለ10 ወራትም በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውረው ማኅበረሰቡን አገልግለዋል።

የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሆኑት እነዚህ ወጣቶች ለማኅበረሰቡ ከሰጡት አገልግሎት መካከል፣ ሠላምን መስበክ፣ አንዱ ብሔር የማያውቀውን ቋንቋ ለሌላኛው ማሳወቅ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት መሥራት፤ የዘማቾችን ሰብል ማረም፣ መኮትኮትና መሰብሰብ፤ እናት አባት የሌላቸውን ሕጻናት መርዳት፣ ለሕክምና ብር አጥተው የተቸገሩ ሰዎችን ማሳከም፣ ለተፈናቃዮች ድጋፍ በማሰባሰብ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማበርከት እና የመሳሰሉት እንደነበሩ ሲገለጽ ቆይቷል።

ዕርዳታን በተመለከተ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር በገንዘብ 318 ሚሊዮን 822 ሺሕ 510 ብር፣ በዓይነት 12 ሚሊዮን 52 ሺሕ 510 ብር፣ በድምሩ 325 ሚሊዮን 874 ሺሕ 956 ብር ድጋፍ አሰባስበዋል። ይህንንም የሰላም ሚኒስቴር በፌስቡክ የተረጋገጠ ገጹ ይፋ አድርጎ ነበር።

በአገልግሎቱ የተሳተፉ የመጀመሪያ ዙር በጎ ፈቃደኞች ኃላፊነታቸውን ከተወጡ ከኹለት ወር በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ኹለተኛና ሦስተኛ ዙር በጎ ፈቃደኞቹም የመጀመሪያዎቹን አርአያ በመከተል ማኅበረሰቡን እያገለገሉ መሆኑ በተለያዩ ድረ-ገፆችና የሚዲያ ተቋማት እየተነገረ ነው።
ቢሆንም ግን የመጀመሪያ ዙር በጎ ፈቃደኞቹ ማኅበረሰቡን በበጎ ፈቃደኝነት በማገልገላቸው ከሚያገኙት እርካታ በተጨማሪ፣ መንግሥት በገባላቸው ቃል መሠረት ተስፋ ጥለውበት የነበረው ሁሉ አለመሳካቱ ቅር አሰኝቷቸዋል።

የበጎ ፈቃደኞቹ ተስፋ እና ቅሬታ
በሠላም አምባሳደርነት የመጀመሪያውን ዙር አገልግሎት ያጠናቀቁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለአዲስ ማለዳ በተናገሩት መሠረት፣ በበጎ ፈቃድ ማኅበረሰቡን በማገልገላቸው ለወደፊት የሥራ ዕድል የሚያገኙበት ኹኔታ እንደሚመቻችላቸው ተስፋ ሰንቀው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በወቅቱ ይህንኑ ቃል ገብተውላቸው እንደነበር ተማሪዎቹ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ 10 ወር በነጻ ያገለገሉ በጎ ፈቃደኞቹ ኃላፊነታቸውን ቢወጡም፣ መንግሥት የገባላቸውን ቃል አለመፈጸሙ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው እና መፍትሔ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ እየገለጹ ነው።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ እንደሚሉት ቅሬታ የፈጠረባቸው ማኅበረሰቡን ማገልገላቸው ሳይሆን፣ ኃላፊነታቸውን ከተወጡ በኋላ መንግሥት እፈጥርላችኋለሁ ያላቸውን የሥራ ዕድል አዘጋጅቶ አለማግኘታቸውና ቤተሰባቸውን መርዳት ባለባቸው ወቅት በድጋሚ የቤተሰብ ሸክም በመሆናቸው ነው።

የተወለዱበትን አካባቢ ለቀው ወደ ሌላ ቦታ በመሔድ ለተከታታይ 10 ወራት ማኅበረሰቡን ያገለገሉት ተማሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፣ በበጎ አድራጎት ሥራ ተሠማርተው ማገልግላቸው ማኅበረሰቡ ከዋለላቸው ውለታ አንጻር ኢምንት ነገር ቢሆንም፣ ሥራውን ከመጀመራቸው በፊት መንግሥት የገባላቸውን ቃል አለመፈጸሙ ግን አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው ነው።

ቅሬታ አደሮብናል የሚሉት ተማሪዎቹ፣ ‹‹ቃል ገብቶ አለመፈጸም በሞራል ላይ መጫወትና ትውልዱ በመንግሥት ላይ ያለውን ዕምነት መሸርሸር ነው›› ሲሉ የተሰማቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መከካል ወጣት አበባው ፀጋዬ ይገኝበታል። አበባው ተወልዶ ያደገበት ጎንደርን ለቅቆ ወደ ሲዳማ ክልል ሐዋሳ ዙሪያ ወረዳ ለ10 ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥቶ ማጠናቀቁን ይናራል። ነገር ግን መንግሥት ለሁሉም የገባላቸውን ቃል ተግባራዊ አለማድረጉ፣ እንደ ግለሰብ ቀላል የማይባል የሥነ ልቦና ጉዳት እንዳደረሰበት ተናግሯል።

‹‹የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመጀመራችን በፊት መንግሥት ‹እናንተ ማኅበረሰቡን አገልግሉ። እኛ ደግሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎታችሁን ጨርሳችሁ እንደተመለሳችሁ በቀጥታ ወደ ሥራ የምትገቡበትን ኹኔታ እናመቻቻለን።› ብለው ተስፋ ሰጥተውን ነበር ሲል አስታውሷል።
አበባው ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው፣ ‹‹መንግሥት ‹እንኳን ለእናንተ ለቀሪው ሥራ ፈላጊም የሥራ ዕድል ልንፈጥር ነው። ከእነርሱ ቀድማችሁ ይህን ዕድል የምታገኙት እናንተ ናችሁ› ብለውን ነበር።›› ይላል።

ከዚህ ባለፈ፣ የተሰጣቸውን የምስክር ወቀረት (ሠርተፍኬት) ይዘው ሥራ ለመወዳደር ሲያቀኑ፣ እንኳን ቅድሚያ ሊያገኙ ‹እናንተን ከሌላው ሥራ ፈላጊ በእኩል እናስተናግዳለን እንጂ የተለየ ነገር ልናድርግላችሁ አንችልም› እንደተባሉም ነው ቅሬታ አቅራቢው ወጣት የገጠመውን የገለጸው።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን አጠናቅቄ ከተመለስኩ ከኹለት ወር በላይ ሆኖኛል የሚለው ሌላው ወጣት ሲሳይ ዓለሙ ነው። ሲሳይም በበኩሉ ‹‹መንግሥት የገባልን ቃል ተግባራዊ አላደረገም።›› ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።

በበጎ ፈቃድ ሥራ ተሠማርተው ከነበሩት ወጣቶች የተገኘው ምላሽ እንደሚያሳየው፣ በወቅቱ ሥራ ሲሠራ የነበረ ሥራውን አቋርጦ፣ የሚወጡ የሥራ ቅጥሮችን በመከታተል ሲወዳደር የነበረም ይህን ተግባር ወደ ጎን ትቶ፣ ሁሉም ሙሉ ሐሳባቸውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ላይ ማሳረፋቸውን ነው። ነገር ግን ከአገልግሎቱ ሲመለሱ የሚገቡበት ሥራ አለመግኘታቸው አስከፍቷቸዋል።

ይህን በተመለከተም ወጣት ሲሳይ ሲናገር፣ ‹‹ዲግሪ ያለሥራ ልምድ ኢምንት በሆነባት አገር፣ የአንድ ዓመት የሥራ ልምድ ማጣት በሕይወት ላይ የዕቃ ዕቃ ጨዋታ መጫወት ነው›› ሲል በመከፋት ተናግሯል።

አስከትሎም፣ ወደ በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከመሔዱ በፊት ትንሽም ብትሆን ሥራ ጀምሮ እንደነበር ያስታውሳል። መንግሥት የሥራ ዕድል ይፈጠርላችኋል የሚል ተስፋን ሲሠጥ ግን ሥራውን እንዳቋረጠ የገለጸው ሲሳይ፣ ይህን ባያደርግ ኖሮ አሁን ላይ የአንድ ዓመት የሥራ ልምድ ባለቤት ይሆን እንደነበር በቁጭት ይናገራል።

ውድዬ ወንድምነህ የተባለው ወጣት በበኩሉ ‹‹መንግሥት ወጣቱን ለፖለቲካ ማራመጃ እንደማጣፈጫ ቅመም እየተጠቀመበት ነው። ለ10 ሺሕ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠርኩ ብሎ በሐሰት ብጣሽ ሠርቲፊኬት ስጦታ ሪፖርት አድርጎ ወጣቱ ግን ቤተሰብ ጋር ተደርቦ የሰቆቃ ኑሮ እየኖረ ነው።›› ብሏል።

የተሰማቸውን ቅሬታ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የበጎ ፈቀድ አገልግሎት ተሳታፊዎቹ፣ ለአገልግሎት በተሠማሩበት ወቅት ለምግብ ተብሎ ሦስት ሺሕ 276 ብር በየወሩ ቢሰጣቸውም፣ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ሊያሟላላቸው ባለመቻሉ ከቤተሰቦቻቸውም ጭምር ተጨማሪ ገንዘብ ያስልኩ እንደነበር ነው የተናገሩት።

‹‹ሥራ ይዘን ራሳችንን ከማስተዳደር በዘለለ ቤተሰብን መርዳት ከሚጠበቅብን የዕድሜ ክልል ወስጥ ያለን ወጣቶች ነን። ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት በኋላ መንግሥት የሚያዘጋጅልንን የሥራ ዕድል ተስፋ አድርገን ብንቆይም፣ ቃሉ ወደ ተግባር ባለመቀየሩ በድጋሚ ቤተሰብ ላይ ወድቀናል። ይህም ከባድ ሕመም ፈጥሮብናል።›› ያለው ሌላው ወጣትና የአገልግሎቱ ተሳታፊ የነበረው አዲሱ ጫኔ ነው።

አዲሱ በሰጠው አስተያየት፣ ‹‹የተሳተፍነው በመልካም ተግባር በመሆኑ ተግባራችንን ስናጠናቅቅ ልንረካ ሲገባ፣ የተገባልን ቃል አለመፈፀሙ ግን መልካምንትን እስከመጥላትና በመንግሥት ላይ ያለንን ዕምነት እስከማሳጣት አድርሶናል።›› ብሏል።

የመጀመሪያውን ዙር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ካጠናቀቅን ከኹለት ወር በላይ ሆኖናል የሚሉት ተማሪዎቹ፣ መንግሥት የገባልንን ቃል ሊተገብርልን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። በዋነኝነትም የሚከተሉት ፍሬ ሐሳቦች ትኩረት እንዲሰጣቸው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ መንግሥት በመጀመሪያ ደረጃ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ጉዳይ፣ ቀጥታ መንግሥታዊ በሆኑ ድርጅቶች ሥራ ማግኘት ባንችል እንኳ በተገባልን ቃል መሠረት የሥራ ዕድል መፍጠሩ ላይ ነው ብለዋል።

ኹለተኛውን አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ሐሳብ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ለሥራ ቅጥር ሲወዳደሩ በቅድሚያ ዕድሉ እንደሚሰጣቸው በተነገራቸው መሠረት እንዲስተናገዱ ነው። እንደ ገለጻቸው ከሆነ፣ አስካሁን እየተስተናገዱ ያሉት እንደማኛውም ተወዳዳሪ በመሆኑ የ10 ወር ድካማችንን ከንቱ አድርጎታል ብለዋል።

ሌላኛውና ቅሬታ አቅራቢዎቹ መንግሥት በአጽንኦት ሊያስብበት ይገባል ያሉት ነጥብ፣ ከእነርሱ ቀጥለው በተመሳሳይ ሥራ የተሠማሩት ኹለተኛና ሦስተኛ ዙር በጎ ፈቃደኞች ኃላፊነታቸውን ተወጥተው ሲጨርሱ በእነርሱ የደረሰ የሥነ ልቦና ጉዳት እንዳይደርስባቸው ቃል የተገባላቸው ነገር በቅድሚያ እንዲዘጋጅላቸው ነው።

የመጀመሪያ ዙር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ እንደሚሉት ከሆነ፣ የተገባላቸው ቃል እንዲፈጸምላቸው የሚመለከተውን አካል ቢጠይቁም ‹‹እሺ›› ከማለት ውጭ መሬት ላይ የወረደ መፍትሔ እንዳልሰጣቸው ነው።
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል አዲሱ ጫኔ በበኩሉ ለሰላም ሚኒስቴር ጥያቄ እንዳቀረበና ‹የሥራ ዕድል እንፈጥርላችኋለን› የሚል ምላሽ እንደሰጡት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

መፍትሔው
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ መንግሥት የገባልንን ቃል ሊፈጽምልን ይገባል ይላሉ። ከሌሎች ሥራ ፈላጊዎች ቅድሚያ የቅጥር ዕድል እንደሚሰጠን የተነገረን ቃል ቢካድም እንኳ፣ በማኅበር ተደራጅተን ሥራ የምንጀምረበት ዕድል ይፈጠርልን። ለኹለተኛና ሦስተኛ ዙር ወጣቶችም ጉዳዩ ከወዲሁ ይታሰብበት ሲሉ አሳስበዋል።

የሰውን ልጅ ሥነ ልቦና ከሚጎዱት ነገሮች መካከል ቀድሞ በተስፋ ሲጠበቅ የነበረን ጉዳይ ጊዜው ሲደርስ አለማግኘት መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። አንድን ነገር ይደረግልኛል እያሉ በተስፋ መጠበቅ በመጨረሻ ጉዳዩ ሳይሳካ ቢቀር በሥነ ልቦና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ይላሉ፣ የሥነ ልቦና አማካሪ ነጋሽ እንዳልካቸው።

በበጎ አድራጊዎቹ ላይ ተከሠተ የተባለው የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲህ አይነት አጋጣሚ ሲኖር ሊፈጠር የሚችል ነው ሲሉ ለአዲስ ማላዳ የገለጹት ነጋሽ፣ ኹለት ዓይነት የመፍትሔ አቅጣጫ ሊኖረው ይችላልም ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን ሠጥተዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ ችግሩ የሚቀረፈው መንግሥት የገባውን ቃል ሲፈጽም ነው። በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ በጎ ፈቃደኞቹ መንግሥት የገባላቸውን ቃል ሳይተገብርላቸው ሲቀር ሥነ ልቦናቸው እንደተጎዳ ከማሰብ ወጥተው፣ መልካምነት ለራስ ነውና ወገናቸውን በማገልገላቸው ያገኙትን እርካታ ደጋግመው ማሰብም ከችግሩ ሊያወጣቸው ይችላል ሲሉ ነው ሙያዊ ምክራቸውን የለገሱት።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ያሉ ወጣቶችን በተመለከተም ይህ ችግር እንዳይፈጠር አንድም መልካም በማድረግ ብቻ የሚገኘውን እርካታ ከወዲሁ አስበው መጓዝ፣ አንድም መንግሥት የሚገባውን ቃል ለመፈጸም ከወዲሁ መዘጋጀቱ ተመራጭ መሆኑን ነው ነጋሽ የተናገሩት።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልክት ምላሽና አስተያየት ለማግኘት ወደ ሰላም ሚኒስቴር የተለያዩ ኃላፊዎች ጋር በተደጋጋሚ ብትደውልም፣ ስልካቸውን ለማንሳት ፈቃደኛ ሊሆኑ ባለመቻላቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here