መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየጠቅላይ ሚኒስትሩ የአራት ዓመት የቁልቁለት መንገድ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአራት ዓመት የቁልቁለት መንገድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሥልጣን ተረክበው ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩ እነሆ ዛሬ ድፍን አራት ዓመት ሞልቷቸዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ “የመፍትሔ አካል” በሚል ምክንያት ሥልጣናቸውን ከለቀቁበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን እየመሩ በሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዘመን ዘርፈ ብዙ ተለዋዋጭ ሁነቶች በኢትዮጵያ ተከስተዋል።

እስካሁን በነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአራት ዓመት የሥልጣን ዘመን ከሕዝባዊ ድጋፍ እስከ ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ በውጭ መንግሥታት አድናቆት ከማግኘት እስከ መነቀፍ፣ ከኢሕአዴግ ክስመት እስከ ብልጽግና ውልደት፣ ከብልጽግና ውልደት እስክ ጦር መማዘዝ የደረሱ ተለዋዋጭ ሁነቶች በኢትዮጵያ ምድር ተፈራርቀዋል።

የኢትዮጵያን ሕዝብ በደስታ ሰልፍ ከማስወጣት እስክ አንገት ማስደፋት የደረሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአራት ዓመት ውጣ ውረድና በአራት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ ሁነቶችን በማስታወስ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

በኢትዮጵያ በተለይ ከ2008 ጀምሮ የወቅቱ መንግሥት በነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር(ኢሕአዴግ) ሥርዓት ላይ ከተለያዩ ወገኖች ሕዝባዊ ተቃውሞዎች እየበረቱ የመጡበት ጊዜ ነበር። የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተከሠቱ ችግሮችን ማስቆም ባለመቻላቸው በ2010 በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን የተረከቡት።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኢሕአዴግ ሊቀ-መንበርነትና ከጠቅላይ ሚኒስትርነት በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ያቀረቡት ምክንያት፣ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን አለመረጋጋት እና የፖለቲካ ችግር ለማስወገድ የሚወሰደው መፍትሔ አካል ለመሆን በማሰብ መሆኑን በወቅቱ በሰጡት መግለጫ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ በወቅቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ፣ መጋቢት 24/2010 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ ዛሬ ማለትም መጋቢት 24/2014 አራት ዓመት አስቆጥረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመረጡበት ዕለት 36 ደቂቃ በሚረዝመው ንግግራቸው “ከኹሉ አስቀድሜ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን በተከሠተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የመፍትሔ አካል ለመሆን፣ የአገር ክብርና ብሔራዊ ጥቅምን በተሻለ ኹኔታ አዲስ አመራር ሊጠብቅ ይችላል ብለው በማሰብ ለአኅጉራችን ምሳሌ በሆነ መልኩ ሥልጣን በፈቃዳቸው ላሸጋገሩት ለክቡር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከፍ ያለ አክብሮቴን እገልጻለሁ” በማለት ነበር የጀመሩት።

በወቅቱ ስለነበረው የሥልጣን ሽግግር ሲያብራሩ “ይህ የሥልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ ዕድል ነው” ብለው ነበር። ጠቅላዩ በንግግራቸው “ሕዝብን አለቃው አድርጎ የሚንቀሳቀስ ሥርዓት እየገነባን መሆኑን ያመላክታል፤ ወቅቱ ከስህተታችን ተምረን አገራችንን የምንክስበት ወቅት ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ አንድ ኢትዮጵያዊ አባት አሉት ብለው ያሰሙት “እኛ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን” የሚል ንግግር በወቅቱ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲቀነቀን ነበር።

ከሙገሳና ሽልማት እስከ ወቀሳ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውረው ሕዝባዊ ውይይቶችን አድርገው ነበር። በየመድረኩ ኢትዮጵያዊነትን ሲሰብኩ የነበሩት ጠቅላዩ፣ ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ድጋፍና አድናቆት ሲጎርፍላቸው ነበር። ከአገር ውስጥ እስከ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ በወቅቱ ባቀነቀኑት ኢትዮጵያዊነት ተቀባይነትን ያገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የነበረው ችግር እንዲፈታ ባቀረቡት ጥሪ ሠላም መፍጠራቸው ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ዝናን አስገኝቶላቸው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሾሙበት ዕለት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲፈታ ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሠላም እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ተከትሎ በ2012 የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ መሆን ችለዋል። በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል በተፈጠረው ሠላም ከዓለም ዐቀፍ ተቋማት እስከ ዓለም መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አድናቆትና ሙገሳ ሲጎርፍላቸው ነበር።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀናቸው፣ ከኤርትራ ጋር ሠላም በመፍጠራቸው፣ በውጭ ሆነው በትጥቅ ትግልና በሠላማዊ ትግል ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ማድረጋቸው እና እስረኞችን መፍታታቸው ተደጋጋሚ የድጋፍ ሰልፎች እንዲደረጉላቸው ምክንያት ሆኗል።

በተሾሙበት ዕለት ባሰሙት ንግግር ላይ ያነሷቸው ሐሳቦች በወቅቱ የኢትዮጵያውያንን ቀልብ የሳቡ እንደነበሩ ብዙዎች ይገልጻሉ። በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተጎጅ ለሆኑ ዜጎች ይቅርታ የጠየቁት ዐቢይ “ለተፈጠሩት ችግሮች ዕልባት በማበጀት ሕዝባችንን እንደምንክስም ጭምር በዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ” ብለው ነበር።

“ዴሞክራሲ ሲገነባ መንግሥት የዜጎቹን ሐሳብ በነጻነት የመግለጽ መብት ማክበር አለበት። ዴሞክራሲን ከዜጎች ሠላማዊ እንቅስቃሴ፣ ከመንግሥት መሪነት፣ ደጋፊነትና ሆደ ሠፊነት ውጭ ማዳበር አይቻልም። በመሆኑም፣ መንግሥት የዜጎችን ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል በጽናት ይሠራል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሥልጣን ከተረከቡ ዛሬ አራተኛ ዓመታቸው ነው። ብዙዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የገቡትን ቃል በተግባር ማሳየት አለመቻላቸውን እና ከአራት ዓመት በፊት መንግሥታቸው የዜጎችን ሠላማዊ እንቅስቃሴ ለማረጋገጥ የገባውን ቃል አሁን ላይ መተግበር አለመቻሉን በማንሳት ይወቅሷቸዋል።

በወቅቱ “መንግሥት ሕግን ማክበር አለበት፤ ማስከበርም ግዴታው ነው፤ ታጋሽነትም ኃላፊነቱ ነው። የመንግሥት ታጋሽነት ሲጓደልም ዴሞክራሲ ይጎዳል። በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ የሕግ የበላይነት መከበር ይገባዋል…ሕዝባችን የሚፈልገው የሕግ መኖር ብቻ ሳይሆን የፍትሕ መረጋገጥንም ጭምር ነው… ሕግ ኹላችንንም እኩል የሚዳኝ መሆን አለበት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እስካሁን በነበረው የአራት ዓመት የመሪነት ጊዜያቸው የሕግ የበላይነትን ማስከበር አለመቻላቸው እና ያኔ የመንግሥት ግዴታ ነው ያሉትን ሕግ ማስከበር ዛሬ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የግድያ፣ ዝርፊያና ማፈናቀል ሲፈጸም መንግሥታቸው ሕግ ማስከበር አለመቻሉ በብዙዎች ዘንድ ትችት አስከትሎባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመረጡ ባደረጉት ንግግርና ከሕዝብ ጋር በተወያዩባቸው መድረኮች፣ ለሕዝብ የገቧቸውን ቃሎች መፈጸም አለመቻላቸውን ተከትሎ ከቀድሞ ደጋፊዎቻቸው ጭምር ትችት እየቀረበባቸው ነው። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ዕልባት ያገኛሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ተባብሰው መቀጠላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ላይ ዕምነት የለንም እስከ ማለት የደረሱ ትችቶች እንዲቀርቡ ሆኗል።

በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስተዳደር መፍትሔ ያገኛሉ የተባሉ የጸጥታ ችግሮች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎ፣ ባለፉት ዓመታት በተለይ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በመቶ የሚቆጠሩ ግጭቶች ተከስተው በሺሕዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ዜጎች መገደላቸውን እስካሁን የወጡ የግጭት ሪፖርቶች ያመላክታሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡ በኹለት ዓመት ብቻ የሰሜኑን ጦርነት ሳይጨምር እንደ አገር 113 ግጭቶች ተፈጥረው ለንጹኃን ዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም ምክንያት መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸው ከዓመት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸው ነበር።

- ይከተሉን -Social Media

በተለያዩ ክልሎች በታጠቁ ኃይሎች በየጊዜው የሚገደሉና የሚፈናቀሉ ዜጎች ችግር አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ ዐቢይ ከአራት ዓመት በፊት ሥልጣን ሲረከቡ የነበራቸውን የሕዝብ ድጋፍና የውጭ ተቀባይነት የቀነሰ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማስጠበቅ ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ ኃላፊነቱን በአግባቡ አለመወጣቱን ተከትሎ የሚቀርቡበት ትችቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረቱ ነው። ነገር ግን፣ አሁንም በተለይ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ታጣቂ ኃይሎች በንጹኃን ዜጎች ላይ የሚያደርሱትን ግድያና መፈናቀል ማስቆም አልተቻለም።

ከአራት ዓመት በፊት በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩና የመንግሥት ተፎካካሪ የሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች አገር ውስጥ ገብተው በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈቃድ ያገኙ ቢሆንም፣ ፓርቲዎቹ አሁን ላይ ከዐቢይ አስተዳደር ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል። ትጥቅ ፈትተው ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል የተባሉ አካላት በዚህ ወቅት በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከነትጥቃቸው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ከአራት ዓመት በፊት የነበረው ስምምነት አሁን ላይ ውጤት አልባ እንዲሆን አድርጎታል የሚሉ አካላት አሉ።

ከለውጥ መንገድ ወደ ጦርነት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ብዙም ሳይቆዩ የለውጥ አስተዳደር ያሉትን የመንግሥት አስተዳደር ሲያዋቅሩ ነበር። እራሱን “የለውጥ ኃይል” ብሎ የሚጠራው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር፣ በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን የነበሩ ችግሮችን “በመደመር” መንገድ እንደሚፈታ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር።

እራሱን “የለውጥ ኃይል” ብሎ የሚጠራው የዐቢይ አስተዳደር፣ በኢሕአዴግ ዘመን የነበሩትን ችግሮች ይቀርፋል ያለውን ከመደመር ሐሳብ እስከ ብልጽግና ፓርቲ የደረሰውን መንገድ ተጉዟል። ሒደቱም ተቋማትን እንደገና ከማደራጀት ጀምሮ በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን ሙስናና ወንጀል ፈፅመዋል የተባሉ ባለሥልጣናትን እስከ ማሰር የደረሰ ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንገድ የኢሕአዴግ ዘዋሪ ነው ከሚባለው ሕወሓት ጋር ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩነት መፍጠሩን ተከትሎ፣ በኹለቱ መካከል ከፍተኛ ቅራኔ ተከሰተ። ኢሕአዴግን እስከ ማክሰም የደረሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር መንገድ በሕወሓት ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥመውም ልዩነቶችን ተነጋግሮ መፍታት አልቻለም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንገድ፣ ከጅምሩ በብዙዎች ዘንድ ቅጥ ያጣውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር መስመር ያስይዛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። አስተዳደሩ አዲሱን የለውጥ መንገድ ለመከተል የሚያደርገው ሙከራ የኢትዮጵያ ችግርን ያቃልላል ተብሎ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጀመሪያ የተጓዙበት መንገድ በሐሳብ ደረጃ ጥሩ እንደነበረ ብዙዎች ያምናሉ። ይሁን እንጂ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የነበሩት ተስፋዎችና መልካም ጅማሮዎች እየከሰሙ ወደ ቀድሞው ሥርዓት የመመለስ ዝንባሌዎች እየታየ መምጣቱን ብዙዎች ይገልጻሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት በወቅቱ በየመድረኩ ይቀነቀን የነበረው የለውጥ ሐሳብ በተግባር አለመታየቱና የኢትዮጵያ ችግሮች ተባብሰው መቀጠላቸውን ነው።

አዲሱ አስተዳደር ኢሕአዴግን አክስሞ ብልጽግና ሲመሰርት በሕወሓት በኩል ስምምነት አለመኖሩ ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት ጦርነት አባባሽ ምክንያት መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ። በዐቢይ አስተዳደር የተመሠረተው ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመት ከመራው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር(ኢሕአዴግ) መፍረስ በኋላ የተፈጠረ ፓርቲ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ከአስተዳደር ለውጥ እስከ ብልጽግና ውልደት የደረሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ፣ የሕወሓትን ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት አስከ ማቋረጥ የደረሰ ነበር። የሰሜኑ ጦርነት እስከተጀመረበት እስከ ጥቀምት 24/2013 ድረስ በቃላት ጦርነት የዘለቀው የኹለቱ ፓርቲዎች ሽኩቻ፣ ኢትዮጵያ ባሉባት ችግሮች ላይ ሌላ ችግር የፈጠረ መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ።

“ኢትዮጵያን አበለጽጋለሁ” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር፣ ከሕወሓት ጋር የተፈጠረውን ልዩነት በወቅቱ ተነጋግሮ መፍታት ባለመቻሉ ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ አድርጓል የሚሉ ሰዎችም አሉ። አስተዳደሩ በበኩሉ የሰሜኑን ጦርነት “የፌዴራል መንግሥት ተገዶ የገባበት ጦርነት ነው” ይላል።

የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ከአምስት ወር ያስቆጠረ ሲሆን፣ በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልል አስካሁን በተካሔደው ጦርነት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ዜጎች ሕይወታቸውን እንዲያጡና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግር እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል። ጦርነቱ በቀጥታ በተካሔደባቸው ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለችግር ከመጋላጣቸው ባለፈ አገሪቱም ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እያስተናገደች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ በቀጥታ ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ቁጥር በአፋር፣ በአማራና በትግራይ ክልል ዘጠኝ ሚሊዮን ዜጎች፣ በድርቅ የተጎዱና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 5.7 ሚሊዮን ዜጎች፣ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚሹ የዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ ያመላክታል። እንደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ መሠረት በአሁኑ ስዓት በኢትዮጵያ 14.7 ሚሊዮን ዜጎች በጦርነትና በድርቅ ምክንያት ለተረጅነት ተጋልጠዋል።

በሌላ በኩል፣ የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶ፣ ሕዝቡ በከፍተኛ ደረጃ የሚማረርበት ኹኔታ ላይ ደርሷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአራት ዓመት በፊት “መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ዕጥረቱን ለማረጋጋት፣ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለመጠበቅ፣ የሕዝቡን የነፍስ ወከፍ ገቢ ለመጨመር፣ ድህነትን ለመቀነስ ሞክሯል። የዋጋ ንረትና ኑሮ ውድነት፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት አለመመጣጠን፣ የውጭ ዕዳ ጫና እና አገር ውስጥ ቁጠባ ልዩነት እየጎላ መጥቷል። በርካታ ሥራዎች ይሠራሉ፤ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስቀጠል እንተጋለን” ብለው ነበር። ይሁን እንጂ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የኑሮ ወድነቱና የውጭ ምንዛሬ ዕጥረቱ ከዓመት ዓመት እየተባባሰ መምጣቱን፣ በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት የሚፈተነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና በየዕለቱ እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነት ያሳያል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠንሳሽነት ኢሕአዴግን አክስሞ በምትኩ የተመሠረተው ብልጽግና “የኢትዮጵያን ብልጽግና አረጋግጣለሁ” እያለ ቢናገርም፣ “የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ቀርቶ፣ የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማስከበር አልቻልም” በሚል ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትችት እየበረታበት ነው። በእርግጥም የዐቢይ አስተዳደር የመሪነት መንበሩን ከኢሕአድግ ከተረከበበት ጊዜ በኋላ በኢትዮጵያ የሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ ተብሎ ቢታሰብም ተባብሰው መቀጠላቸውን ብዙዎች ይስማማሉ።

አስተዳደሩ የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር የሆነውን የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማረጋገጥ አለመቻሉን ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ሰብዓዊ መብት ተቋማት እያስተጋቡት ነው። በተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው የሚሞቱ ዜጎችን ሕይወት መታደግ ባለመቻሉ የበረታ ትችት የሚቀርብበት ብልጽግና አሁንም የዜጎችን ሞት ማስቀረት አልቻለም።

ለአራት ዓመት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የዘለቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር፣ አሁን ላይ በሰሜኑ ጦርነት፣ በተለያዩ አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች በሚፈጥሩት የጸጥታ ችግር፣ በኑሮ ውድነት፣ በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት፣ በድርቅና በመሳሰሉ ችግሮች እየታመሰ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ከመከራ ማላቀቅ ይጠበቅበታል።


- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች