ራሔል ባፌ (ዶ/ር) ትውልድና ዕድገታቸው የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል በነበረውና አሁን ላይ አዲስ በተመሠረተው ደቡብ ምዕራብ ክልል ዳውሮ ዞን ነው። ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በዳዋ ከተማ ተከታትለዋል።
ራሔል የመጀመሪያ ዲግሪ በማኔጅመንት፣ ኹለተኛ ዲግሪ በቢዝነስ ማኔጅመንት ከቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በ‹ሊደርሺፕ› የሠሩት ራሔል፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በሊቀ መንበርነት እየመሩ ይገኛሉ። ከ30 ዓመት በላይ የፖለቲካ ተሳትፎ ያደረጉት ራሔል፣ በምክር ቤቱ እንቅስቃሴና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ማነው? ኃላፊነቱስ ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በዋናነት ኢትዮጵያ ውስጥ ዕውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአንድነት በአገር ጉዳይ ላይ የማገዝ፣ አብሮ የመሥራት፣ ‹መልቲ ፓርቲ ሲስተሙን› የማገዝ ሥራ ላይ ይገኛል። ኹላችንም አገራዊ በሆነ ነገር ላይ አንድ ላይ እንድንሆን፣ አንድ ላይ እንድንሳተፍ የተመሠረተ ነው። አንዲት አገር ናት እና ያለችን፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ሲሆን የሚለያየን ነገር አይኖርም።
የመጨረሻው ግባችን አንድ ነው። እሱም ነጻና ዴሞክራሲያዊ የሆነች፣ የበለጸገች አገር ማየት ነው። ስለዚህ መንገዱ የተለያየ ሊሆን ይችላል እንጂ መዳረሻው አንድ ነው። በዚህ አግባብ ኹሉንም ነገሮች በጋራ አብረን እንሥራ ከሚል ዕሳቤ ተቋቁሞ፣ ይህንን ሥራ የሚያግዝ ተቋም ነው።
የጋራ ምክር ቤቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ከማስተሳሰር በተጨማሪ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ምን እየሠራ ነው?
በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ ድምጽ ለመሆን ኹለገብ እንቅስቃሴዎች ያደርጋል። ፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ከሕዝብ የወጡ ናቸው፤ ከሰማይ አልወረዱም። ሙሉ በሙሉ ሕዝብ መርጧቸው ነው ወይ? ወክሉኝ ብለዋቸው ነው ወይ? እሱ ሌላ ጥያቄ ሆኖ፣ ግን አነሳሳቸው የሕዝቡን ሐሳብ ይዘው ነው። ስለዚህ ያንን የሕዝብ ድምጽ ማሰማት ነው።
በተጨማሪም፣ አብሮ በሚያሠራ ጉዳይ ላይ የጋራ የሆነ ነገር መሥራት መቻል፤ በዚህ አግባብ ነው የሚሠሩት። መንግሥት ማረም በሚገባው ነገር ወይም ፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ እንደ ግብዓት መግባት ያለበት ነገር፣ በሐሳብ የበላይነት የሚሠሩ ነገሮች ኹሉ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ በዚያ ዙሪያ በሙሉ አቅሙ ነው የሚንቀሳቀሰው፤ የጋራ ምክር ቤቱ።
ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ወዲህ አንድ ምርጫ ተካሂዷል። እስከ አሁን በነበረው እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ምን ስኬት አስመዝግቧል? ምንስ ድክመቶች ታይተውበታል?
ስኬት ብለን የምናየው ምርጫውን ሠላማዊ አድርገን፣ ማንም በምርጫ ምክንያት ሳይሞት፣ ጥፋት ሳይደርስ፣ አገርም እንደ አገር ደግሞ ቀውስ ውስጥ ሳትገባ ማለፋችን በጋራ ምክር ቤቱ ዕድሜ ትልቁ ስኬታችን ነው። ሌላው እንደ ጉድለት የምናየው ተቀራርበን ወደ አንድነት የመምጣትና ለሕዝብም ለምርጫው በሚመች መልኩ መቅረብ አለመቻላችን (የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም) እንደ ደካማ ጎን እናየዋለን።
የሕዝብ ድምፅ እንዲበተን አድርጓል። በገዥው ፓርቲም የተለያዩ የካድሬ ጥቃቶች እንዲፈፀሙ ክፍተት ሠጥቷል። ይሄ እንደ ድክመት የሚታይ ነው። እዚህ ላይ ግን በደንብ ተሠርቶ ቢሆንና ወደ ተሻለ ኅብረት መጥተን ቢሆን ኖሮ የተሻለ ውጤት ሊኖር ይችል ነበር ብለን እናስባለን።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ሐሳባቸውን የሚያንጸባርቁበት እንደመሆኑ፣ አሁን ባለው ወቅታዊ ኹኔታ ላይ ያለው አቋም ምንድን ነው?
የምክር ቤቱ አቋም በእርግጥ በመግለጫ ብቻ አይወሰንም፤ መግለጫዎችን ስናወጣ ለሕዝብም፣ ለመንግሥትም፣ ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብም ክፍተቶችን እናሳያለን። ያ ነገሮች እንዲታረሙ ያግዛል፤ አቋማችንንም ለማንጸባረቅ ይረዳል። ግን እንደ አገር ተማምረን ተነጋግረን ለመሥራት ከመንግሥት ጋር በጋራ በሚሠራ ነገር ኹሉ እንሳተፋለን።
በኢኮኖሚ ችግሮች እና በጋራ ሊፈቱ በሚችሉ ችግሮች ላይ በተጠያቂነት መንፈስ አብሮ መንቀሳቀስ ይቻላል። በዋናነት የአገርን ደኅንነት የማስጠበቅ፣ የሕዝብን ሠላምና ደኅንነት ማስከበር፣ ሉዓላዊ ዳር ድንበርን ማስጠበቅ የመንግሥት ዋና ኃላፊነት ነው። የመንግሥት ዋነኛው ሥራ ይሄ ቢሆንም፣ ብቻውን ግን የሚሠራው ሥራ የለም፤ ሕዝብ አስተባብሮ ነው። እዛ ላይ በቁርጠኝነት መንግሥት ተንቀሳቅሶ ድጋፍ ቢጠይቅ እንተባበራለን። በጋራ ምክር ቤቱ የሚፈለገውን ኹሉ እናደርጋለን።
ነገር ግን፣ ይሄ በዋናነት የፓርቲዎች ሳይሆን የመንግሥት ኃላፊነት ስለሆነ ያ ተሳክቶ እንዲመጣ እናግዛለን።
እርስዎ የገለጹልኝ እንደ ምክር ቤት የምታድርጉትን ድጋፍ ነው። ባለው ወቅታዊ ኹኔታ ላይ አቋማችሁ ምንድን ነው?
በእርስ በእርስ ጦርነት የሚፈታ ችግር የለም። በዚህ የጋራ ምክር ቤት ዕድሜ ምክር ቤቱ ለሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ እንነጋገር፤ የጋራ ምክክር ያስፈልጋል፤ ችግሮችን ተነጋግረን እንፍታ፣ ወደ ሕዝባችን እንመለስ፣ እንምከር፣ የሚል ዕሳቤ ሲያራምድ ነው የቆየው። አላደለንም እንጂ የጋራ ምክር ቤቱ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ኹኔታዎችን መቅደም አስቦ ነበር። በጣም ጥረት ተደርጎም ነበር፤ ግን አልተሳካም።
የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ዕሳቤ መነጋገርና ችግሮችን መፍታት ነው። መወያየት፣ መደራደር፣ ያለውን ነገር እየፈታን መሔድ እንጂ በጦርነት አናምንም። መጨረሻም ላይ ችግሮችን የምንፈታው በነዚሁ ነው። የትም አገር ያለው ልምድ ብዙ ዓመት የተካሄደ ጦርነትም እንኳ መጨረሻ ላይ በንግግር ነው የሚያልቀው። ስለዚህ ለምን ብዙ ዋጋ እንከፍላለን? ወደ ንግግሩ እንምጣ ነው የጋራ ምክር ቤቱ ጥያቄ። ይሄን ጥያቄ ደግሞ ለኹሉም ለመንግሥትም ለሌሎችም ጦር ላነሱ አካላት በመግለጫ አቅርበናል።
እንዲያውም የጋራ ምክር ቤቱ በዚህ ሲተች ነበር። ‹እንዴት እንነጋገር ይላል?› በሚል። አቋማችን ነገሮችን ተነጋግሮ መፍታት ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው። አሁን ደግሞ የእኛ ብቻ ሳይሆን እኛ አካል የሆነው ብልጽግናም መንግሥት እንደሚመራ ፓርቲነቱ በዚህ ስምምነት ነው አብሮ እስከመሄድ የመጣው። ይሄ በጋራ ምክር ቤቱ እየተሄደበት ያለ አቅጣጫ ነው።
ኢትዮጵያ ከገባችበት ጦርነት የምትወጣው ተቀራርቦ በመነጋገር ነው የሚሉ አካላት አሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተቀራርቦ መነጋገሩን የሚቃወሙ አካላት አሉ። አሁን ባለው ኹኔታ እነዚህን ሐሳቦች እንዴት ማስታረቅና ጦርነቱን በሠላማዊ መንገድ መቋጨት ይቻላል?
ይሄን በዋናነት እንደ እኔ ዕምነት ነው ማስቀመጥ የምፈልገው። እዚህ ጋር ተቀምጠን ቀላል ሊመስለን ይችላል፤ ግን ሕይወታቸውን ያጨለመ ነገር በእናቶች ላይ ተፈጽሟል፤ ሴቶች ላይ ተፈጽሟል፤ ሕፃናት ላይ ተፈጽሟል፤ በጣም የሚዘገንን ነገር ወታደሮች ላይ ተፈጽሟል። ይሄ ነገር በተለይ እንደ ሕዝብ ወደ ንግግር ስንሄድ ያልተፈወሰ ቁስል ነው። የተፈጸመው ነገር ከልቦና ቶሎ አይወጣም። ነገር ግን፣ ወደ ንግግሩ ካልገባን ሌላ እንጨምራለን እንጂ መፍትሔ አናመጣም። መጨረሻ ወደ ንግግሩ መሄዳችን ላይቀር ሌላ ሳንጨምር እሱ ፈጣሪ አምላክ ጣልቃ ገብቶ ያንን ሕመማችንን እንድንረሳ ከረዳን፣ ከሕመማችን አልፈን ማየት ከቻልን፣ ሕመሙ ይሄ ትውልድ ሲያልፍ አብሮት የሚሔድ ይሆናል። ግን ሌላ ለኹለተኛ ለሦስተኛ ትውልድ የሚሆን ሕመምና ጥፋት ካላሰብንና እንደው እግዚአብሔር ከረዳን አማራጭ አለመኖሩን ዐይተን ወደ ንግግር ከገባን እንተርፋለን ብዬ አስባለሁ።
አሁን እነዚህ ሐሳቦች መታረቅ የሚችሉት በዚህ አግባብ ነው። አይ ወደ ንግግሩ አንሂድ የሚሉም ቆም ብለው ማየት አለባቸው። ቁስሉንም የተሸከሙት በእኔ ይብቃ ማለት ካልቻሉ ብዙም ሳንሄድ ተጨማሪ ጦርነቶችን፣ ተጨማሪ ውድመቶችን እናደርሳለን። ግን ከዚያ በኋላ ወደ ንግግሩ ነው የምንሄደው። ያ ምን ይጨምራል የሚለውን እናስብ።
ስታስበውም በዚህ ትኩስ ሕመም ውስጥ ሆነህ ከሆነ ከባድ ነው። ለዚህ ነው እግዚአብሔር ከተጨመረበት ያልኩት። በዚያ ልክ ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ማሳየትና ማየት መቻል አለብን። በተለይ የፖለቲካ መሪዎች መውጫውን የማየት፣ መንገድን የመሔድ፣ የማስረዳትና የመምራት ኃላፊነት አለባቸው። ይህንን ማየት ከቻሉ እንዲሁም ሔደው ከሳዩ፣ ከዚህ ችግር ውስጥ ሳንዘገይ እንወጣለን ብዬ አስባለሁ።
በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አገራዊ ምክክር ሒደት ላይ እርስዎ የሚመሩት ምክር ቤት ተሳትፎ አድርጎ እንደ ምክር ቤት በሒደቱ ላይ ቅሬታ አንስቷል። መሠረታዊ ችግሩ ምንድን ነው?
የግልጸኝነትና አሳታፊነት ችግር ነው። ሒደቱ ግልጽ አልነበረም፤ አሳታፊ አልነበረም፤ ስለ ሒደቱ መስፈርትም አልነበረውም። እነዚህ ሦስቱ ዋና ነገሮች ናቸው። አንደኛ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። ኹለተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም ይሁን ሲቪክ ማኅበራትን፣ አገራዊ ምሁራንን (አገራዊ ምሁራንን ስል ኢትዮጵያዊ ሆነው አገር ውስጥም ከአገር ውጭም ያሉትን) ኹሉ ያሳተፈ ቢሆን፣ የሐሳብ ግብዓቶች ተካተው ቢሆን የተሻለ ይሆን ነበር።
ዋናው የብሔራዊ ምክክር መርህ ዕምነት መፍጠር ነው። መነሻው ላይ እምነት ካጣህ እንዴት ትሔዳለህ? ይሄ መሠረታዊ መርህ ነው። ስለዚህ ዕምነት ይኑር፤ ዕምነት ካለ ድግሞ ባለድርሻ አካል ኹሉ ሐሳቡን ይገዛዋል። እንደ አገር ደግሞ ካለብን ችግር አንጻር ይህንን ሞክሬ ይሰናከልና ሌላ ኹለተኛ፣ ሦስተኛ፣ አራተኛ ዙር እሞክራለሁ ብለን ልናስብ አይገባም። ለዘመናት ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋጋ እየከፈለ የመጣው። ከ1953 ከእነ መንግሥቱ ነዋይ ዘመን ጀምሮ፣ ስንት ምሁር፣ ስንት ወጣት ነው ያለቀው? እና አሁንም ያንን ዓይነት ችግር ከፊት ደግሰን መሔድ ያለብን አይመስለኝም።
በኢትዮጵያ አሁን ካለው ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የታጠቁ ኃይሎች መሳተፍ አለባቸው የሚሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። መንግሥት ደግሞ የታጠቁ ኃይሎች አይሳተፉም ብሏል። እንደ ምክር ቤት ይሄን ጉዳይ እንዴት ትመለከቱታላችሁ?
እኛ በኹለት አማራጭ እናያለን። አሁን መንግሥት ለኮሚሽኑ ሥራውን አስረክቧል። አሁን የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ካድሬዎች በየሚዲያው ወጥተው እገሌ ይሳተፋል፤ እገሌ አይሳተፍም የሚሉት በሙሉ ስህተት ነው። ይህ ውሳኔ መንግሥትን አይመለከትም።
ይሄን ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩም አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥትን አይወክሉም ማለት ነው?
አዎ! የመጀመሪያ ስለሆነ ኹሉም የመሰለውን ነው ያወራው። ግን ሚዲያዎች ከእንዲህ ዓይነት የውሸት መረጃ ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። የመንግሥት አካላትም ቢሆኑ በማይመለከታቸው ጉዳይ ላይ፣ በአገር ጉዳይ ላይ፣ ወደ ፊት እየገባንበት ባለ አገራዊ ምክክር ላይ፣ አወዛጋቢ ንግግር ወደ ሚዲያ ማውጣታቸው አግባብ አይደለም።
አሁን በዚህ መልኩ አይቀጥልም፤ አሁን ውሳኔው የምክክር ኮሚሽኑ ነው። ኮሚሽኑ በሚሄድበት አግባብ በምን መልኩ ያነጋግራል? በምን መልኩ ይሄድበታል? በምን መልኩ አካታች ያደርገዋል? አብረን የምናየው ይሆናል። ያ አንዱ ነው። ኹለተኛ ደግሞ ዕድለኞች ብንሆን ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ ቆሞ ምክክሩን ብንጀመር የተሻለ ነበር። ጦርነቱ ባልቆመበት ኹኔታ እየሄድንበት ነው።
ኃይሎችን ወደ ጦርነት የወሰዳቸውን መሠረታዊ ጉዳይ እየፈታን ከሔድንና መፍትሔ ካገኘን በረሃ ያሉ ተዋጊዎችም መሣሪያቸውን ቁጭ አድረገው የሚመጡበት አማራጭ ይኖራል። ዞሮ ዞሮ ችግሩ ከተፈታ የሚዋጉበት ምክንያት ያከትማል። እኔ እንደ ግለሰብ በዚያ መልኩም የሚፈታባቸው እድሎች ይታዩኛል። አንደኛ የጦርነቱ ምንጩ ሲደርቅ የሚፈታበት ኹኔታ ይመጣል። ኹለተኛ ኮሚሽኑ በራሱ አነጋግሯቸው ችግሩ የሚፈታበት ነገር ይኖራል። እነሱ በቃን እስኪ ይሄ ነገር እኛንም ይመለከተናል እንነጋገር ብለው መሣሪያ አስቀምጠው በማንኛውም ሰዓት ሊመጡ ይችላሉ።
ከየትኛውም ኮሪደር፣ አይደለም እነርሱ፣ ጎዳና ተዳዳሪ ያገባኛል ብሎ ቢመጣ እዚያ ጋር የገጠመውን ችግር መነጋገር መቻል አለብን። ልጆቻችንን ከጎዳና ላይ ማንሳትና ሰው ማድረግ እኮ እንፈልጋለን፤ እንደ አገር። ስለዚህ እነሱም አገርን ጠቅመው ራሳቸውንም ማሳድግ ይችላሉ። በዚያ ልክ ክፍት መሆን አለበት። ሰዎች ለመሳተፍ ከመጡ ፈቃደኝነቱ ደግሞ ወሳኝ ነው።
አገራዊ ምክክሩ አሁን የሚታዩ ችግሮችን በአግባቡ መፍታት የሚቻልበት በር እንዲከፍት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
እኔ በግሌ የማስበው ኮሚሽነሮቹ ወደ ሕዝብ መምጣት አለባቸው፤ እራሳቸውን ማስተዋወቅ አለባቸው። ቁርጠኝነታቸውን፣ ፈቃደኝነታቸውን፣ በምን መልኩ መድረኩን አካታች አድርገው ለመሔድ አስበዋል የሚለውን ለሕዝብ ግልጽ ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ። ሌላ ደግሞ መንግሥት ገና ከጅምሩ ያበላሸውን የተሳሳተ አካሔድም እያረሙ መሔድ ይጠበቅባቸዋል።
ስለዚህ አሁን ባለበት ደረጃ በእርግጠኝነት ዋና ዋና ጉዳዮችን ሕዝብን ወክለው ማየት የሚችሉ አካለት አሉ። በፌዴራል ደረጃ፣ ሲቪክ ማኅበራትን፣ በዋናነት የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሴት ሲቪክ ማኅበራትን እና ሴቶች (እነሱም የኢትዮጵያ ቢያንስ 50 በመቶ አካላት ናቸው) እኩል የሚሳተፉበት ነገር ቢኖር፣ ለወጣቶችም ምቹ ኹኔታ ቢፈጠር የተሻለ ነው (ከ 42 ተጠቋሚዎች ውስጥ አንድ ወጣት ብቻ ነው የነበረው)። በዚህ መልኩ ዕምነት ለመፍጠር እነዚህን ያልተካተቱ ሰዎችና ተቋማት ማነጋገር መቻል አለበት ይሄ ኮሚሽን።
ዝግ የነበሩ የጠረጴዛ ላይ ውይይቶችን እንደገና መክፈት አለበት። በእርግጥ ይሄ የመጀመሪያችን እንደመሆኑ በየገጠመኞቹ እየተማርን ይቀጥላል፤ መንግሥት በበኩሉ ያለውን ችግር ይፈታል ብለን እናስባለን። ለምን? መንግሥት በዋናነት እስከ ቀበሌ ድረስ አደረጃጀት ያለው አካል ነው። ካድሬዎቻቸው የዞን፣ ወረዳ፣ የክልል አስተዳደሮቻቸው ምን ያክል ዝግጁ ናቸው? የሎጅስቲክስ አቅርቦትና የደኅንነት ጥበቃ እንደሚያደርጉ፣ ከአንድ ለአምስትና፣ አንድ ለአስር ማነቆ ሕዝቡን ነጻ እንደሚያደርጉ ምንም መተማመኛ የለንም።
በዚያ መልኩ ኮሚሽነሮችም እንዳይቸገሩ ከመንግሥት ጋር ያለው ውይይት አሁንም መቀጠል አለበት። እየተነጋገርን መቀጠል አለብን ብዬ አስባለሁ። የጋራ ምክር ቤቱም በዚህ ሐሳብ እስከመጨረሻው ተስፋ ሳይቆርጥ፣ እየተገፋን ግን ገፍተን ሔደን አብረን ለመሥራት ጥረት እያደረግን ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን እስከማጋራት የደረሰ ግንኙነት ነበረው። አሁን አሁን ኃላፊነቱን አልተወጣም በሚል ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትችት በርትቶበታል። መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት እንደ ምክር ቤት እንዴት ትመለከቱታላችሁ?
እንደ እኔ ጥሩ ጅማሮ ነው። ቢያንስ ፖለቲካ ፓርቲዎችም እዚህ ውስጥ ሲገቡ አንድ አገር እንዳለችን በማሰብ ነው። ቢያንስ ዳቦ ፍለጋ አይደለም እዚያ ጋር የተሔደው። የሕዝብ ድምፅ እንሆን ይሆናል በሚል ነው። የሕዝብ ድምፅ ለመሆን ዕድሉን ይከፍታል። በእርግጥ ፖሊሲው የብልጽግና ፓርቲ ነው፤ ያንን ነው የሚያስፈጽሙት። ነገር ግን ሐሳቦችን ሊያመጡ ይችላሉ። በሐሳብ የበላይነት እስከታመነበት ድረስ በዚያ አጋጣሚ የሕዝብ ድምጽ የሚሠማበት ኹኔታ ይፈጠራል።
እንደ ፖለቲከኛ ማሰብ ያለብን፣ ስጦታ አይጠበቅም በፖለቲካ። መብት በስጦታ አይገኝም። መብትህን እራስህ ሠርተህ ታፈራዋለህ። ስለዚህ እዚያ ድረስ ነው መሔድ ያለበት። ይሄ በስጦታ መልክ የተሰጠ ነገር በተፈለገ ሰዓት ኹሉ ይወሰዳል፤ ሕዝቡ የሠጠህ ቦታ ሲሆን ግን አታጣውም። ሕዝቡ በቃ ብሎ እስከሚያወርድህ ድረስ አምስት ዓመት መብትህ ነው። ብልጽግና አሁን አምስት ዓመት መብቴ ነው ብሎ መናገር የቻለው ለዚያ ነው።
አሁን የመራራቁ ነገር ለምንድን ነው የሚታየው ካልከኝ በትንሹ መደማመጥ መጥፋቱን ነው የሚያሳየው፤ ይሄ ጥሩ ምልክት አይደለም። እንደ እኔ ዕምነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰቆቃ፣ የደም ጣር ጩኸት እግዚአብሔር ያዳመጠበት ሰዓት ነው። ግን በዚህ ሰዓት አላዳምጥም ያለ የመንግሥት አካል ቢኖር፣ አላዳምጥም ያለ የፖለቲካ መሪ ቢኖር ለራሱ መጥፎ ሥራ ነው። በዚህ መከራ ውስጥ እናልፋለን፤ ሕዝቡ ግን ወደድንም ጠላንም ነጻ ይወጣል። ጊዜውን ነው የምናራዝመው። ያ እንዳይሆን ኹሉም በተጠያቂነት መንፈስ መንቀሳቀስ አለበት ብዬ አምናለሁ።
ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ ከኃይልና ጦርነት አልተላቀቀችም። የፖለቲካ ምኅዳሩን ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ማሻገር የሚቻለው እንዴት ነው?
እኔ እንደሚመስለኝ አሁን የጀመርነው አገራዊ ምክክር አንደኛው መንገድ ነው። እሱ ውስጥ ገብተን በተቻለ መጠን ኹላችንም እንደ ሕዝብ በንቃት ተሳትፈን፣ የሚቻለው ጥረት ኹሉ ተደርጎ፣ ኹሉን አካተን፣ በምንሄድበት ሒደት ኹሉ ግለጽ አሠራሮች፣ ግልጽ ውይይቶችና ውሳኔዎች ኖረው በዚያ መልኩ ከሔድን የምንፈታበት ብቸኛ መንገድ ነው። ሌላ አማራጭ የለውም።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ አብዛኛውን ጊዜ እርስ በእርስ በመወነጃጀል ላይ የተመሠረተ ነው የሚል ትችት ከተለያዩ ወገኖች ይቀርብበታል። ፖለቲከኞች የኢትዮጵያ ችግር ፈጣሪ ተደርገውም ይወሰዳሉ። እርስዎ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ እንዴት ይገልጹታል?
እኔ እንደ ግለስብ ከጠየከኝ እንደውም ይገባቸዋል ብዬ ነው የማስበው። በጎሳ ደረጃ ባለመደራጀታቸው አደንቃለሁ፤ የኢትዮጵያ ችግር በጎሳ ደረጃ ተደራጅቶ ጥቃት የሚያደርስ ነው። አንዱ ጎሳ ተደራጅቶ ሌለው ጎሳ ላይ ጥቃት ሲያደርስ፣ ያ ደግሞ ሌላኛው ላይ ያደርሳል፤ በዚህ ደረጃ ነው። እኔ እንደውም ከክልል ወርዶ በጎሳ አለመሆኑ ፖለቲከኞቹን አደንቃለሁ።
የችግራችን መጠን እንደዚያ የጠለቀ ነው። ቢነጋገሩ፣ ቢነታረኩ ይሄ ሥርዓቱ የፈጠረው ነው። ለምሳሌ የወያኔ ሥርዓት የወንበሩ ማቆያ መንገድ ይሄ ብቻ ስለነበረ ለ27 ዓመት ታች ድረስ ነው በጣም የሠራው። አንዲት ቀበሌ ሳትቀር በሞግዚት አስተዳደር በማቆም ነው ይሄን ሥርዓት የተከለው። ያንን አሁን በአንድ ጊዜ ማጥፋት አንችልም። በዚህ በሦስትና በአራት ዓመት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ዐይተናል። ቢያንስ በአገር ደረጃ ወደ መስማማት መጡ እኮ ፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በዞን ደረጃ ቀርቶ በክልል ደረጃም መስማማት ከባድ ነበር።
አሁን ላይ በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው ያሉት። ብታምነኝም ባታምነኝም የክልል ፓርቲዎች ራሳቸው ዕይታቸው አገራዊ ነው፤ ሥማቸው ነው ክልላዊ።
ኮታ ከመሙላት የዘለለ እውነተኛ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አለ ብለው ያምናሉ?
እኔ አላምንም፤ በግሌ። እስከ አሁን በኮታ ወይም በውለታ መጥተናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሃምሳ ሃምሳ ሆኖ ነበር በወንዶችና በሴቶች መሀል ያለው ልዩነት። አሁን ግን ወደ 30 ቤት የገባበት ኹኔታ አለ፤ ምክንያቱም ሴቶች ያንን በጥረታቸው ሠርተው አላገኙትም ነበር። እዛ ወንበር ላይ ለመቆየትም በነጻ የሠጠውን ክፍል አስደስተው ወንበራቸው ላይ መቆየት ይኖረባቸዋል። በዚያ ምክንያት ብዙ ነገር አይተናል።
ወለጋ ላይ 17 ሴቶች ሲጠፉ፣ አንድም ቀን ሴት ሚኒስትሮቻችን ስለ እነዚያ ሴቶች ሲናገሩ አልሰማንም። አንድም ቀን የሴቶች መብት ካልተጠበቀ በቃን ሲሉ አላየንም። ስለዚህ ይሄ የሚነግረን አድርጉ የተባሉትን ነው ተቀብለው የሚያደርጉት። ስለዚህ ሴቶች መብታችን የምንቀበለው ሳይሆን የምንፈጥረው ሊሆን ይገባል። ግን ያንን የተቀማነውን መብት መልሰን ለማግኘት ሴቶች ብቻ ሳንሆን ወንዶችም እኩል ለዚህ መብት መከበር ሊሠሩ ይገባል። ማንም በስጦታ መብትን አይሰጥም፤ በመሠረታዊነት ሴቶች የአገር መሠረቶች ናቸው።
ዘጠኝ ወር ተሸክማ፣ ሥጋዋንና ደሟን አካፍላ መውለድ ለመደፈር ካበቃት፣ ለመታረድ ካበቃት ከዚህ የወረደ አገር አይኖርም። በድህነት ነበር የምንታወቀው አሁን የተዋረድንበት ዓመት ነው። በድህነት ብንጠራ ይሻለን ነበር፤ በዚህ ዓይነት አስነዋሪ ሰብዕና በዓለም ከምንገለጥ። ይሄ ገና ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል።
ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014



