በጎፋ ዞን 70 ሰዎች ካለፍርድ ለ6 ወራት ታስረዋል

0
563

• የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት በጎፋ ዞን ፍትሕ መምሪያ አልተከበረም ብሏል

በደቡብ ክልል፣ በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ ገልማና ገንዳ ቀበሌዎች መካከል ነዋሪ የሆኑ 70 ሰዎች፣ ከትምህርት ቤት ስያሜ ቅሬታ ጋር በተያያዘ የወረዳው አስተዳደርና አመራር ከወረዳው ፖሊስ ጋር በመሆን ይዟቸው፣ ለስድስት ወራት ያህል ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማረፊያ ቤት እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

አቤት ባዮቹ፣ መስከረም 7/2011 በወረዳው አስተዳደርና ፖሊስ ተይዘው የተከሰሱበት ክስና ምክንያት ሳይነገራቸው፣ በዛላ ወረዳ ፖሊስ ማረፊያ፣ በጊዜ ቀጠሮ አንድ ወር ያህል ከቆዩ በኋላ ያለምንም ክስና የጊዜ ቀጠሮ ለስድስት ወር ያህል በእስር መቆየታቸውንና የዋስትና መብት ለመጠየቅም ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ዕድል ያለማግኘታቸውን በቤተሰቦቻቸው በኩል ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል።

አቤት ባዮቹ የታሰሩበት ምክንያት በገንዳ ቀበሌ ውስጥ የሚገኘው ትምህርት ቤት በእኛ ስም ይጠራ በሚል ጥያቄ፣ በኹለቱ ቀበሌዎች በተነሳው ኹከት፣ በንብረትና በሰው አካል ላይ በደረሰው ጉዳት ተጠርጥረው ነው። በወቅቱ በተወሰኑ ሰዎች ቅስቀሳ አለመግባባት ተፈጥሮ መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚህ ጸብ መነሻነት የዛላ ወረዳ አስተዳደርና አመራር ከወረዳ ፖሊስ ጋር በመሆን የኹለቱን ቀበሌ ሕዝብ እናስታርቃለን በማለት ስብሰባ ጠርቶ፣ ከስብሰባው ቦታ አፍኖ በመውሰድ እንዲታሰሩ ማድረጉን የደረሰን መረጃ ያሳያል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19(4) እና 37(4) መሰረት፣ ማንኛውም ሰው በተጠረጠረበት ወንጀል ፍርድ ቤት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሲወስን፣ የሕግ አስከባሪ አካላት ምርመራውን አጣርተው የተያዘውን ሰው በተቻለ ፍጥነት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በማድረግ እና የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብቱን የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው በግልጽ ይደነግጋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ የወንጀለኝ መቅጫ ሕግ ሥነ ስርዓት 109(1) ዐቃቤ ሕግ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ተጠናቆ ከቀረበለት ቀን አንስቶ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ በተጠርጣሪው ላይ ክስ የመመስረት ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት የሚገልጽ ቢሆንም፣ ይህንን በመጣስ በእነዚህ ሰዎች ላይ የተፈጸመው ኢሰብኣዊ ድርጊት እንዳሳሰበው የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን አስታውቋል።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ከሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ተጠይቀው፣ ምላሻቸውን የሰጡት የጎፋ ዞን ፍትሕ መምሪያ ዐቃቤ ሕግ አንዱዓለም ጀማል፣ ከዛላ ወረዳ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ላይ ክስ ሳይከፈት የቆየበት ምክንያት ሌሎች በወንጀሉ የተሳተፉ ሰዎች ስላልተያዙ፣ ፖሊስ የቀሩትን ተጠርጣሪዎች ለመያዝ እየሞከረ ስለሆነ፣ የምርመራ መዝገቡ ቆይቷል ብለዋል። አሁን ግን ያልተያዙት ተጠርጣሪዎች ተለይተው፣ በተያዙት ሰዎች ላይ ምርመራ መዝገብ ከወረዳ ፖሊስ በደብብቤ ቁጥር ዘውኮ/506 በቀን 8/4/2011 በተጻፈ ሸኚ ደብዳቤ መሰረት የፖሊስ ምርመራ መዝገብ ደርሶን ተቀብለናል በማለት በዚሁ መሰረት ክስ እንደሚመሰርቱ ምላሽ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ባደረገው ማጣራት የተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ምርመራ መዝገብ ተጠናቆ ለዐቃቤ ሕግ ጥቅምት 9/2011 ቢተላለፍም፥ ዐቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ እስከዚህ ሳምንት መጨረሻ ድረስ ምንም ዓይነት ክስ እንዳልመሰረተባቸውና ተጠርጣሪዎቹም ጥቅምት 9/2011 ጀምሮ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በሳውላ ማረሚያ ተቋም እንደሚገኙ አረጋግጧል።

የዛላ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 00312/2011 በጥቅምት 9/2011 በሰጠው ውሳኔ፣ ወይም ትዕዛዝ ላይ የምርመራ መዝገቡ እንደተጠናቀቀ እያወቀ በየወንጀለኝ መቅጫ ሕግ ሥነ ስርዓት ቁጥር 109(1) መሰረተ ዐቃቤ ሕግ በ15 ቀናት ውስጥ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ክስ መመስረት እንዳለበት ሳይወስን ወይም ትዛዝ ሳይሰጥ፣ በደፈናው ታራሚዎቹ ወደ ማረሚያ ተቋም እንዲዛወሩ ብቻ መወሰኑ፣ የአቤት ባዮች የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲጣበብ ማድረጉን ኮሚሽኑ አስታውቋል። አክሎም፣ የአቤት ባዮች የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን የዛላ ወረዳ ፍርድ ቤት በጥቅምት 9/2011 በሰጠው ትዕዛዝ እንዲጣበብ አድርጓል ሲል ተችቷል።

ጥናቱን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የምርመራ፣ ጥበቃና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ባስተላለፈው ውሳኔ፣ የአቤት ባዮችን የጠፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት በጎፋ ዞን ፍትሕ መምሪያ አልተከበረም፣ የአቤት ባዮችን የጠፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት በዛላ ወረዳ ፍርድ ቤት እና በሳውላ ማረሚያ ተቋም ተጥሷል ብሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here