ከመንግሥት ጋር ጦርነት ማካሔድ እንደ ሽብር እንዳይቆጠር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

0
597

መደበኛ እና መደበኛ ባለሆነ መልኩ ከመንግሥት ጋር ጦርነት ማካሔድ የሽብር ድርጊት ሆኖ እንዳይቆጠር የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑ ታወቀ።

ሕጉ ይፋ የሆነው በሥራ ላይ ያለው ፀረ-ሽብር አዋጅን ሙሉ ለሙሉ ይተካል የተባለው ሥያሜው ወደ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ተብሎ የተቀየረው ረቂቅ አዋጁ ባለፈው ሐሙስ፣ የካቲት 21 ባለድርሻ አካላት፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች ለውይይት በቀረበበት ወቅት ነበር።

ይሁን እንጂ ጦርነትን ከመንግሥት ጋር የሚካሔድ ድርጅትን እንደ አሸባሪ እንዳይቆጠር ማድረጉ የበለጠ ጠብ አጫሪነትን ሊያበረታታ ይችላል ሲሉ ተሳታፊዎች በውይይቱ ወቅት ግልፀዋል።

ታዋቂው ፀሐፊና አክቲቪስት ስዩም ተሾመ በሰጡት አስተያየት ይህ ዓይነቱ ሕግ በረቂቅ አዋጁ መካተቱ ድርጀቶችንም ሆነ ግለሰቦችን ወደ ጦርነት እንዲገቡ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

ይህ ዓይነት ሕግ በምዕራቡ ዓለም በተለይም በአሜሪካ ዘንድ ተቀባይነት ቢኖረውም ሙሉ ለሙሉ ኮፒ ማድረጉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራትን የበለጠ ችግር ውስጥ ሊከት እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ ረቂቅ አዋጁ ለማዘጋጀት አባል የሆኑት አምሃ መኮንን እንደገለፁት፤ ይህ ዓይነቱ ሕግ የተካተተው ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶቹ መሰረት በማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በፈረመችው በጄኔቫ ኮኔቬንሽን ፕሮቶኮሎች መሰረት ከመንግሥት ጋር ጦርነት ያካሄደ ድርጅት እንደአሸባሪ መቆጠር እንደሌለበትና ረቂቅ አዋጁም በዚህ መሰረት የተዘጋጀ መሆኑ በስብስባው ወቅት ተገልጿል።

ከዚህ ባሻገር ረቂቅ አዋጁ አሁን በሥራ ላይ ያለውና ዜጎች መብትና ነፃነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል በሚል የሚተቸው የፀረ ሽብር አዋጅ አንፃር የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊና ሰብኣዊ መብቶች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም በሥራ ላይ ያለው የፀረ ሽብር አዋጅ ላይ በግልፅ ያልተቀመጡ ሕጎች በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ማስተካከያ እንደተደረገባቸው ተገልጿል።
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ለአስፈፃሚው አካል የበለጠ ኃይል ከመስጠት ይልቅ የዜጎች መብት እንዳይጣስ የሚጠቅሙ ሕጎችን እንዳከተተ አርቃቂ ኮሚቴው ገልጿል።

እንደ አምሃ ገለፃ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የንፁሃንም ሆነ የተጠርጣሪዎች መብት እንዳይጨፈለቅ የሚያደርግ አንዳችም ሕግ እንዳልተካተተበትና ይህንን ለመቅረፍ በአዲሱ ሕግ እንደተሞከረ ባለፈው ሐሙስ በነበረው ውይይት ወቅት ገልጸዋል።

ለአብነትም ያህል በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በወንጀል ሥነ ስርዓት ሕግ መሰረት በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት እንደሚችል ተገልጿል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም ረጅም ጊዜ ይወስድ የነበረውና ዜጎችን ለእንግልት የዳረገው የረጅም ጊዜ ምርመራ ለማስቀረት አዲሱ ረቂቅ አዋጅ አንድ ሰው በሽብር ወንጀል ተጠርጣሮ ከተያዘበት ወቅት አንስቶ የምርመራ ጊዜው ከአራት ወራት መብለጥ እንደሌለበት ተገልጿል።

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በሰብኣዊ ተግባር ላይ የተሠማሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች በሽብር ወንጀል ለተጠርጠሩና ለተከሰሱ ሰዎች የሚሰጡት ድጋፍ አያስቀጣም የሚል አንቀጽም አካቷል።

ሽብር ወንጀሎችን ሊከታተሉ የሚችሉ ተቋማትን ኃላፊነት በግልፅ ያስቀመጠው ረቂቅ አዋጁ፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በሽብር ወንጀል የተጠረጠርን ሰው መያዝ እንደማይቻል የሚገልፅ አንቀፅ አካቷል።

የሽብር ወንጀል የሚከታተሉ መርማሪዎች በሰብኣዊ መብት አጠባበቅ ዙሪያ መደበኛና መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ ሥልጠና የወሰዱና መልካም ሥነ ምግባር እንዲሁም በምርምራ ሥራ ልምድና ክህሎት ያላቸውን መሆን አንዳለባቸው ረቂቅ አዋጁ አካቷል።

ከሕግ አስፈፃሚ አካላት ጋር በተያያዘ ማንኛውም በወንጀል መከላከል፣ ምርመራ፣ ክስ ወይም ዳኝነት ሥራ ላይ የተሰማራ ሰውን ግዴታውን እንዳያከናውን ያደረገ ወይም በዚህ ሥራ ላይ የተሰማራውን ሰው ቤተሰብ ላይ የዛቻና የኃይል ድርጊት ወይም ማንኛውም የማስገደጃ መንገድ የተጠቀመ ሰው ከሦስት እስከ ሰባት ዓመት ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቶች በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ወይም የተከሰሰ ሰው ከአያያዙ ጋር በተያያዘ በሚያነሳው በመብት ጥያቄ ቅድሚያ በመስጠት በመርመር እና ተገቢውን ማስተካከያ እንዲደረግ አግባብነት ያለውን ትዕዛዝ መስጠት አለበት የሚል አንቀጽ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ተካቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here