ሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ባልሆኑ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የእውቅና ፈቃድ እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እውቅና ፈቃድ በተሰጣቸው የማስተማሪያ ህንጻ፣ ከባቢያዊ ሁኔታና የማስተማሪያ ግብአት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ አስቸኳይ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በዚህም ተቋማቱ እውቅና ፈቀድ በተሰጣቸው የማስተማሪያ ህንጻ፣ ከባቢያዊ ሁኔታና የማስተማሪያ ግብአቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ማሻሻያ አድርገው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ድረስ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡
ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግም ተገቢውን ማስተካከያ ባላደረጉ ተቋማት ላይ የእውቅና ፈቃድ እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም አስረድቷል፡፡
በተጨማሪም በቀጣይ በሚያከናውናቸው የእውቅና ፈቃድ እና የእውቅና ፈቃድ እድሳት አገልግሎቶችም በዚህ አግባብ ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ገልጿል፡፡
ተቋማት የመማር ማስተማር ተግባሮቻቸውን ሲያከናውኑ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ስለመሆናቸው ልዩ ትኩረት መደረግ እንዳለበት በአዋጅ ቁጥር 1152/2011 በአንቀጽ ቁጥር 41 ንዑስ አንቀጽ 1-3 ላይ ተደንግጎ ተቀምጧል።
________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



