የEBC የኦሮምኛ ክፍል ሀላፊ በላቸው ጀቤሳና በግል ሥራ የሚተዳደረው አለማየሁ ቂጤሳ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ዓቃቢህግ መልስ ሰጠ

0
1309

ማክኞ መጋቢት 27 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ባሳለፍነው መጋቢት 9 ቀን 2014 የሸገር ውሀ አምራች እና አከፉፉይ ድርጅት ባለቤት ዶ/ር ሀሰን መሀመድ ግማሽ ሚሊዮን ብር ጉቦ ተቀብለዋል ብሎ ዓቃቢህግ የሙስና ወንጀል ክስ ያቀረበባቸው 1ኛ ተከሳሽ የኢትዮጲያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን (EBC) የኦሮምኛ ክፍል ሀላፊ በላቸው ጀቤሳና በግል ሥራ የሚተዳደረው 2ኛ ተከሳሽ አለማየሁ ቂጤሳ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ዓቃቢህግ መልስ ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ ከዚህ በፊት የክስ መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ አቅርበው የነበረ ሲሆን፤ በዚህም 1ኛ ተከሳሽ በላቸው ጀቤሳ የቀረበበት ክስ የግልጽነት ችግር እንዳለበት የጠቀሰ ሲሆን፤ 2ኛ ተከሳሽ በኩል ደግሞ የቀረበበት ክስ ተደራራቢ መሆኑን እና የወንጀል ተሳትፎ እያንዳንዱ በዝርዝር በክሱ እንዳልተካተተ ተገልጾ ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም በዚህ በቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ ዓቃቢህግ ምላሹን እንዲያቀርብ ለትላንት መጋቢት 26 ቀን 2014 በተሰጠው ቀጠሮ መሰረት የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ መልስ ዓቃቢህግ በጽሁፍ አቅርቧል።

በዚህ ባቀረበው መልስ ላይ 1ኛ ተከሳሽ “ክሱ ግልጽነት ይጎለዋል” ሲል ያቀረበውን የክስ መቃወሚያ በመለከተ ዓቃቢህግ በክሱ የሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 10(1) ላይ በስህተት ተካቷል የተባለው (ሀ) የሚል ንዑስ አንቀጽ የሚታረም መሆኑን ጠቅሶ፤ ከዚህ ከተካተተው ንዑስ አንቀጽ ውጪ ግን ክሱ ግልጽነት የማይጓለው መሆኑን በመልሱ አብራርቷል።

የቀረበባቸው ክስ ጋር በተያያዘ በአዋጁ አንቀጽ 10 (1) የተጠቀሰው የጉቦ መቀበል ወንጀል የሚያቋቁማቸው ፍሬ ነገሮች ግን፤ የወንጀል አፈጻጸም በማየት ጉዳዩን የሚያከብዱ ማስረጃዎች በመገኘታቸው በድንጋጌው ንዑስ አንቀጽ 2 ሊቀርብ መቻሉን በምላሹ ገልጿል።

2ኛ ተከሳሽ አለማየሁ ቂጢሶ በክሱ ላይ ዝርዝር ተሳትፎው እንዳልተገለጸ ጠቅሶ፤ ክሱ ተደራራቢ በመሆኑ እንዲሻሻል ያቀረበውን የክስ መቃወሚያን በተመለከተም ዓቃቢህግ ምላሽ ሰጥቷል።

በምላሹም የውሀ አምራች ድርጅት ባለቤት ከሆኑት የግል ተበዳይ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል ውሀው ውስጥ ሶፍት የሚመስል ባዕድ ነገር አግኝተናል ለ1ኛ ተከሳሽ መስሪያ ቤት ጥቆማ አድርሻለው በማለት፤ በስልክን ማናገሩን እና በመጨረሻም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ለቡ ጋርመንት አካባቢ በአንድ ካፊ በመገናኘት ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን 500 ሺህ ብር በጥሬና በቼክ መቀበላቸው በቀረበው ክስ ላይ መዘርዘሩን ገልጿል።

2ኛ ተከሳሽን ተሳትፎና የስልክ ልውውጥ ያደረገባቸው ስልክ ቁጥሮች ጭምር በክሱ በሰነድ ማስረጃ የተያያዘ መሆኑን የጠቀሰው ዓቃቢህግ፤ እያንዳንዱ ዝርዝር በማስረጃ የሚረጋገጡት ፍሬ ነገሮች በሙሉ በክሱ እንዲካተቱ እንደማይጠበቅ ምላሽ ሰጥቷል።

በተጨማሪም የተከሳሹን የወንጀል ተሳትፎ የሚያሳዩት ወንጀሉ የተፈጸመበት ቦታና ጊዜ በመሰረታዊነት የሚያሳዩት የወንጀለኛ መቅጪያ ሥነሥርዓት ህግ ቁጥር 111 እና 112 በሚያዙት አንቀጽ የቀረበ መሆኑን ጠቅሷል።

ተደራራቢ ክስ ነው በተባለው መቃወሚያን በተመለከተ ደግሞ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር የተሳተፈ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት በሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 10(1) ጉቦ መቀበልን የሚያሟሉ ፍሬ ነገሮች መገለጹን ዓቃቢህግ አብራርቷል።

ጉቦ መቀበልን የሚያመላክት ጉዳይ ንዑስ አንቀጽ 1 ሥር የተቀመጡ መሆኑን በመጥቀስ፤ የወንጀል ክብደትን የሚመለከተው ደግሞ ንዑስ አንቀጽ 2 መሆኑንም በሰጠው የክስ መቃወሚያ ምላሽ ላይ ገልጿል።

በዚህ መልኩ የተገለጸው ድንጋጌ ሊሻሻል እንደማይችል የጠቀሰው ዓቃቢህግ፤ በተከሳሾች የቀረበው የክስ መቃወሚያው ውድቅ እንዲደረግለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የተከሳሽ የክስ መቃወሚያን እና የከሳሽ ዓቃቢህግ ምላሽን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሚያዚያ 11ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።
___
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here