አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ተፈጽሟል አሉ

0
542

ዕረቡ መጋቢት 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ የትግራይ ተወላጆች ላይ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተፈጽመዋል አሉ።

ኹለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚሉት ከሆነ፤ ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀምሮ የአማራ ኃይሎች እና ባለስልጣናት በምዕራብ ትግራይ ባሉ የትግራይ ተወላጆች ላይ ከጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ መጠነ ሰፊ ወንጀሎች ፈጽመዋል።

ኹለቱ የመብት ተሟጋቾች በዛሬው ሪፖርታቸው ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይል ምዕራብ ትግራይ እንዲሰማራም ጠይቀዋል።

ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች ተቋማቱ ዛሬ ይፋ ያደረጉት እና ” ‘ከዚህ ምድር እናስወግዳችኋለን’፡ በሰብዓዊነት የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት በኢትዮጵያዋ ምዕራብ ትግራይ ዞን” የተሰኘው ሪፖርት የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት ምዕራብ ትግራይ የሚንቀሳቀሱ የአማራ ልዩ ኃይል እንዲሁም ሚሊሻዎች “የዘር ማጽዳት እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን” መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ግኝቶችን ይዟል።

“የኢትዮጵያ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች በምዕራብ ትግራይ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎችን ክብደት ለማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል” ሲሉ የአምነስቲ ዋና ጸሃፊ አግነስ ካላማርድ ወቅሰዋል።

“የሚመለከታቸው መንግሥታት እየተካሄደ ያለው የዘር ማጽዳት ዘመቻን ማስቆም ብሎም ከአካባቢው የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችን በፈቃዳቸው እና ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ማስቻል አለባቸው” ሲሉ ዋና ጸሃፊዋ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም ፍትህ ለተበዳዮች እንዲሰጥ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ሪፖርቱ በጦርነቱ የመጀመሪያ ጥቂት ወራት ውስጥ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ጭምር የዳሰሰ ሲሆን፤ የትግራይ ሚሊሻዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪ ሲቪሎች በማይካድራ ከተማ አካባቢው ነዋሪ በሆኑ እና ለቀን ስራ በመጡ የአማራ ተወላጆች ላይ “የጦር ወንጀሎችን” መፈጸማቸውን አስታውሷል።

ተቋማቱ በዝርዝር ካጠኗቸው ልዩ ክስተቶች መካከል በተከዜ ድልድይ አካባቢ በጥር ወር 2013 ፋኖ በመባል በሚጠራው ሚሊሻ ተፈጽሟል ሲሉ የገለጹት ጭፍጨፋ ይገኝበታል።

ጥር 9 አዲ ጎሹ ተብላ በምትጠራው አነስተኛ ከተማ የፋኖ ሚሊሻዎች ነዋሪዎችን ከሰበሰቡ በኋላ ወንዶቹን በመምረጥ አስረዋል ያለው ሪፖርቱ፤ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በበኩላቸው 60 የሚጠጉ የትግራይ ተወላጅ ወንዶችን የተከዜ ድልድይ ጋር ወስደው ረሽነዋል ይላል።

“መንግሥት በምዕራብ ትግራይ ጥቃት የሚፈጽሙ የሚሊሺያ አደረጃጀቶችን ሊያፈርስ እንዲሁም ጥቃት የፈጸሙ አማራ ልዩ ኃይል እና የፌደራል ሃይሎች አባላትን ሊያስወጣ ይገባል” ሲሉ ተቋማቱ በሪፖርታቸው አሳስበዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች የሰላም አስከባሪ ኃይል ምዕራብ ትግራይ እንዲሰማራ ጠይቀዋል።

ኹለቱ ተቋማት ላለፉት 15 ወራት ያካሄዱትን ምርመራ ውጤት ተከትሎ በአካባቢው ያለውን አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለማስቆም በአፍሪካ ሕብረት የሚመራ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ ጠይቀዋል።

ተቋማቱ ትላንት ረቡዕ መጋቢት 27 ይፋ ባደረጉት ሪፖርታቸው በኹለቱም ተዋጊ ኃይሎች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶችም የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ምዕራብ ትግራይ በአስቸኳይ ማሰማራትን ያጠቃለለ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ መብት ተሟጋቾቹ ከሆነ የሰላም አስከባሪ ኃይል በስፍራው መሰማራት፤ የሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ፣ የሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ እና በትግራይ አደጋ ላይ የወደቁ ሰዎችን ለመድረስ ቁልፍ እርምጃ ይሆናል ብለዋል።

በአካባቢው ያለው ችግር ውስብስብ እና በቀላሉ የማይፈታ ስለሆነ ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ በኹለቱም ወገን ያሉ ሲቪሎችን ሊከላከል ይችላልም ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

“ይህ የተለመደ ወይም በቀላሉ የምንሰጠው ምክረ ሃሳብ አይደለም። ነገር ግን የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና የጸጥታ ኮሚሽን የኢትዮጵያን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ተወያይቶ አያውቅም። የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትም ተጨባጭ እርምጃ አልወሰደም። ይህንን ምክረ ሃሳብ የምንሰጠው የጉዳዩን አሳሳቢነት እንዲረዱት መነሻ ሃሳብ ለመስጠት ነው” ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሸናል የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አጥኚ የሆኑት ፍሰሃ ተክሌ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙሪያም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የፊት ለፊት ውይይቶችን ጨምሮ ምክረ ሃሳቡን እንደሚያቀርቡ ፍስሃ አስታውቀዋል።

የኹለቱን ተቋማት ሪፖርት ተከትሎ ቢቢሲ የኢትዮጵያ መንግሥት አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን በዘገባው አመላክቷል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here