የሕክምና ባለሙያዎች እንግልት

Views: 218

ሰሚራ አሕመድ ትባላለች (ሥሟ የተቀየረ) በአንድ የመንግሥት ሆስፒታል ውስጥ በከፍተኛ ነርስ ሙያ እንደምትሠራ ትናገራለች። ሰሚራ በቅርቡ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ብሎም በአገራችን ኢትዮጵያ የተሰራጨውን የኮሮና ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከወትሮው በተለየ መልኩ የሥራ ጫና በዝቶባታል። ሕዝብን እና አገርን ለማገልገል በገባችበት የሙያ ሥነ ምግባር እና ቃለ መሃላ ውስጥ ዋነኛው እና ትልቁ ነውና በደስታ ከምትከውናቸው የሕይወት ጥሪዎቿ ዋነኛው ነው።

‹‹ወገን እና አገርን ማገልገል እኮ መታደል ነው›› የምትለው ሰሚራ፣ በተለይም ደግሞ ሰዎች ከነበሩበት የሕመም ስሜት አገግመው እና ፈውስ አግኝተው ሲመለሱ የምታገኘው እርካታ በዋጋ የሚተመን እንዳልሆነ ትናገራለች።

ይህ በቅንነት የምታገለግለው ኅብረተሰብ እና በፍቅር የምትከውነው ሙያ ታዲያ ከሰሞኑ ለዕለት ተዕለት ሕይወቷ እክል እየሆነባት ነው። ከወዳጅ ዘመድ ከመገለል ጀምሮ በቤት አከራዮቿ እስከ መገላመጥ አድርሶባታል። ከጊዜያት ወዲህ በተለይም ደግሞ ባለፉት ጥቂት ቀናት፣ ኹለቱ ኢትዮጵያውያን ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ችግሩ ይበልጥ እንደባሰባት ትናገራለች።

‹‹ሰው እንደዚህ ይሸሸኛል ብዬ አስቤ አላውቅም። በተለይ ደግሞ ወዳጅ ናቸው ያልኳቸው እና ያመንኳቸው ሰዎች እጅግ እስከ መጸየፍ ድረስ ደርሰዋል። የአከራዮቼን ነገርማ አታንሳው›› ስትል ትጀምራለች፤ ሰሚራ ስለ ጉዳዩ ስትናገር። ለወትሮው ከምትሠራበት ሆስፒታል ደጅ ላይ ታክሲም ሆነ የከተማ አውቶብስ ተሳፍራ በቀላሉ ወደምታመራበት ትሔድ እንዳልነበር፣ አሁን ግን ታክሲ ከነጭራሹም በሆስፒታሉ አካባቢ ሰዎችን ቆማ ማሳፈር እንዳቆሙ ታስረዳለች።

ለዚህ ደግሞ እንዴት መረዳት እንደቻለች ስታስረዳ ‹‹መጀመሪያ አካባቢ በትራፊክ ፖሊሶች ምክንያት ታክሲዎች በስፍራው ቆመው ሰው ማሳፈርም ሆነ ማውረድ እንዳይችሉ ተደርገዋል ብዬ ስላሰብኩኝ ረጅም መንገድ በእግሬ ተጉዤ ታክሲ ለመያዝ እሞክር ነበር። ነገር ግን በቅርቡ ታክሲ ውስጥ እኔ ስገባ መውረጃ ስፍራዋ የደረሰች ሴት አሳለፍከኝ በሚል ከረዳቱ ጋር ተሰዳድባ ስትወርድ ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎች እሷን አግዘው ለምን እንደዛ እንዳደረገ ሲቆጡት ደረስኩኝ። ረዳቱም በልበ ሙሉነት ሆስፒታሉ አካባቢ ከቆመ የሆስፒታል ሠራተኞች ሊሳፈሩ ስለሚችሉ እና ማሳፈር እንደማይፈልግ ከወረርሽኙ ጋር አገናኝቶ ሲመልስ ቅስሜ ነው የተሰበረው›› ስትል ለአዲስ ማለዳ ትናገራለች።

ሰሚራ ስሜቷ እንደተጎዳ እና በሰዎች ላይ ያላት አመለካከት እንዲቀየር እንደተደረገ ትናገራለች። በተለይም ደግሞ የአመለካከት ችግሩ ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ጀምሮ እስከ ቅርብ ወዳጆቿ ድረስ መዝለቁ የችግሩን አሳሳቢነትና ግዝፈት ከወረርሽኙ በላይ ልቆ እንደሚታያት ትናገራለች።

‹‹ሰዎችን ጥንቃቄ ማድረግና አካላዊ መራራቁን በትክክል መተግበራቸው እጅግ የሚደገፍ እና የሚመከር እርምጃ ቢሆንም ማግለል ግን ከባዱ ነገር ነው። በተለይም ደግሞ ከማግለል የሚገኘው ትርፍና ወረርሽኙን ለመግታት ከሚደረግ አካሄድ ጋር የሚያደርገው አስተዋጽኦ ይኖራል ብዬ አላምንም›› ትላለች። ለዚህ ደግሞ ሰሚራ ከወደ ጓደኞቿ እና ሥራ ባልደረቦቿ በኩል የምትሰማቸው ችግሮች እጅግ ሁኔታው እየከበደ መምጣቱን ነው።

ይልቁንም ደግሞ በእሷ በኩል ከቤት አከራዮቿ ዘንድ የምትሰማው እና የምታየው ችግር በንክኪም ባይሆን የርቀት ሰላምታ እንኳን እንደነፈጓት ትናገራለች። ይህ በሰሚራ ላይ ብቻ የደረሰ መገለል እና መድሎ እንዳልሆነ ከባለ ታሪካችን ባልደረቦች እና ገጠመኞቻቸው መረዳት ችለናል።

‹‹በእኔ በኩል ሰዎች ለምን ሰላም አይሉኝም ወይም አያቅፉኝም ሳይሆን ቢያንስ የስልክ ጥሪዎቼን ቢያነሱ እና ቢያዋሩኝ ምንም የሚፈጠር ነገር የለም። በቅርብ የምንተዋወቅ ጓደኛማቾች እና በሌላ ሥራ መስክ የተሰማሩ ጓደኞቼ እንኳን ስደውልላቸው ወይም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ስጽፍላቸው መመለስ ካቆሙ ቆይተዋል›› ትለናለች ባለ ታሪካችን ሰሚራ።

በተለይ ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ የግልም ሆነ የመንግሥት የጤና ተቋማት በሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ጫና በማኅበረሰቡ እየደረሰ እንደሆነ ሰሚራ ለአዲስ ማለዳ ትናገራለች። ‹‹እንግዲህ በመሃል አዲስ አበባ ነው እኔ ላይ የደረሰውን የነገርኩህ። ነገር ግን በተለያዩ ስፍራዎች ከከተማ ወጣ ያሉ ክፍለ አገራት ላይማ ጭራሽ ይብሳል። የማውቃቸው የሕክምና ባለሙያዎች ከተከራዩበት ቤት እስከ መባረር እንደደረሱም ሰምቻለሁ›› ትላለች።

ሰሚራ አያይዛም ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በምትገኝ ከተማ የምትኖር አንዲት የሕክምና ባለሙያ ሥራ ከሄደችበት የተከራየችበትን ቤት አከራዮቿ ሰብረው በመግባት የቤት እቃዎቿን ከአጥር ውጪ በማውጣት ወደ ጊቢ እንዳትገባ እንዳደረጓት እና በኋላም በሕግ አካላት አደራዳሪነት ማምሻውን እንደተመለሰች ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች።

በተለያዩ ጊዜያት በተለይም ደግሞ የመጀመሪያ ሞት ከተመዘገበበት ቀን በኋላ በሕክምና ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰው ጫና እጅግ እየከፋ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ በተለያዩ መንገዶች ያነጋገረቻቸው የሕክምና ባለሙያዎች አረጋግጠዋል።

ይህን ጉዳይ በሚመለከት ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እና በጤና ሚኒስቴር በኃላፊነት የሚገኙ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በዋነኛነት ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም በየዘርፉ ያሉ ባለ ድርሻ አካላት ተገቢውን ግንዛቤ ለሕዝቡ አላደረሱም ብለው ያምናሉ። አያይዘውም የአሁኑ ወረርሽኝ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መሰራጨቱ እየታየ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ትንሽ የዘገየን ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ሲሉም ያክላሉ።

የሥራ ኃላፊው በመቀጠልም ከዓመታት በፊት በኤች አይ ቪ ኤድስ ምክንያት በርካቶች ከአካባቢያቸው እና ከወዳጆቻቸው ተገልለው ለአዕምሮ መታወክ እና ለሌሎች ተጨማሪ የጤና እክሎች ተዳርገው እንደነበር አውስተዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ግንዛቤ ማስጨበጫዎች ዘግይተው መጀመራቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዳስከፈለ እና በኋላም ላይ በትልቅ መነሳሳትና እንቅስቃሴ በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፈጠሩን ይናገራሉ።

ነገር ግን ይህ ዓለም ዐቀፋዊ ወረርሽኝ ጊዜ ካለመስጠቱ እና አፋጣኝ በሽታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለግንዛቤ ይደረስበታል ተብሎ የሚተው ባለመሆኑ፣ ኹሉም ኅብረተሰብ ከመገናኛ ብዙኀን የሚተላለፉትን መልዕክቶች በትክክል አውቆ እና ተረድቶ መንቀሳቀስ እንደሚኖርበት ያሳስባሉ። አያይዘውም በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ የሚደርሰውን እንግልት ግን በየደረጃው ያለው የጸጥታ አካል መቆጣጠርና እንዲሁም በዋናነት ኅብረተሰቡ ደግሞ መተባበርና ከጎናቸው መቆም ይኖርበታል ሲሉ ያስገነዝባሉ።

ሰሚራ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገችው ቆይታ አሁንም ይህ ነገር እየባሰ እንደሚመጣ ብታስብም፣ በቅርቡ በመንግሥት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትንሽም ቢሆን መፍትሔ ይዞ ይመጣል የሚል ሐሳብ አላት። ‹‹መንግሥት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በጣም ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ። ቢያንስ ከቤት የማንባረርበት እና በአከራዮቻችን ጥቃት የማይደርስብን ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በትክክል የጤና ባለሙያዎችን የሚመለከት ሕግ በዝርዝር ሊያስቀምጥ ይገባል›› ስትል በአጽንኦት ታስቀምጣለች።

ሰሚራን እንደማሳያ አነሳን እንጂ በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ የሆነችውን ራምላ ኢድሪስን ማንሳት ይቻላል። ከምትሠራበት ከጳውሎስ ሚሊኒየም ሪፈራል ሆስፒታል ወደ ፒያሳ በመሄድ ነበር ወደ ቤቷ የሚወስዳትን ታክሲ የተሳፈረችው። ታዲያ በአጋጣሚ ከባልንጀራዋ የተደወለላትን የስልክ ጥሪ በታክሲ ውስጥ በማስተናገድ በምትሠራበት ሆስፒታል ስለተገኘው የኮሮና ታማሚ በምታወራበት ወቅት ከተሳፋሪዎች ትውረድልን ወይም እኛን አውርደን በማለት ተቃውሞ በመነሳቱ፣ የተሳፈረችበት እና ወደ ጀሞ ትሄድ የነበረችው ራምላ መሃል መንገድ ላይ በግድ እንድትወርድ መደረጓን አስታውቃለች።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሥነ አእምሮ ሕክምና ክፍል ባልደረባዋ ዶክተር ኢየሩሳሌም ኃይሌ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሲሰጡ፤ ራሳቸውን አደጋ ውስጥ ጥለው በዚህ የጭንቅ ወቅት አገርን እና ወገንን እያገለገሉ ያሉትን የሕክምና ባለሙያዎች በዚህ መንገድ ውለታቸውን ልንከፍላቸው አይገባም ሲሉ አስተያየታቸውን ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ እንደሌላው የሥራ መስክ ሠራተኞች እነሱም የሚሳሱላቸው ቤተሰቦች እና የሚናፍቁት ሕይወታቸውን አሳልፈው እየሰጡ በመኖራቸው ሊበረታቱ እንጂ ሊገለሉ አይገባም ሲሉም ያክላሉ።

‹‹ይህን ስንል ግን ተጠጋግተው እየተነካኩ ሰላም ይበሏቸው ማለት ሳይሆን፣ በርቀት ሆነው አይዟችሁ በማለት ከጎናቸው መሆናቸውን እንዲያሳዩ ይሁኑ ነው የምንለው።›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሰሚራ ለአዲስ ማለዳ አስተያየቷን በሰጠችበት ወቅት በጤና ተቋማት በቂ ያልሆነ የግብዓት አቅርቦት ባጋጠመበት ሁኔታ በርካታ ተግዳሮቶችን ተቋቁመው እንደሚሠሩ እና በዚህ ባልተመቻቸ ሁኔታ ላይ ጭራሽ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚደርሰው ጫና ደግሞ ተስፋ የሚያስቆርጥ እንደሆነ ትናገራለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com