የኑሮ ውድነት እያደር መጨመሩን ተከትሎ፣ የጓሮ አትክልት ትከሉ ከማለት እስከ “ሙዝ በዳቦ” የደረሰ የአመጋገብ ምክር በተለያየ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡ መልዕክቶችን ብዙዎች ሲጋሩት ተስተውሏል። ከሰሞኑ ደግሞ ነገሩ አለመረጋጋትና ሰላም ማጣት ባሳሰበው አድማጭና ተመልካች ዘንድ እንደቀልድ ይታይ እንጂ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ግን የኑሮ ውድነቱ በዚህ ከቀጠለ የአመጋገብና አኗኗር አኳኋንን መቀየር ግድ ሊል እንደሚችል ከወዲሁ እያሳሰቡ ነው። ይህም ከአገር ውስጥና ከውጪ ካሉ ጫናዎች ጋር ተዳምሮ፣ ለኢትዮጵያዊያን እያንዳንዱ ቀን በሩጫና በትግል የሚያልፍ ከባድ ቀን እንዲሆን እያደረገው ነው።
የኑሮ ውድነቱ ቢያንስ ባለበት እንዲረጋጋ ለማድረግ ሰላምን ከማስፈን ጀምሮ የመንግሥት ድግሶችን መቀነስን ጨምሮ ከሕዝብም ጭምር የሚጠበቁ ብዙ የቤት ሥራዎች እንዳሉ ነው ባለሞያዎች የሚመክሩት። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከሳምንት በፊት በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ “ሕብረተሰቡ የአኗኗር፣ የአበላል፣ የአመጋገብ ዘይቤውን መቀየር ዓለበት” ብሏል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን የኑሮ ውድነት ጉዳይ በማንሳት፣ የተለያዩ መረጃዎችን በማጣቀስና የምጣኔ ሀብት ባለሞያ በማናገር ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።
በኢትዮጵያ የኑሮ ወድነቱ ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት በየጊዜው ማሻቀቡና ተባብሶ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየጊዜው የሚያወጣቸው መረጃዎችና በማኅበረሰቡ ላይ የሚታየው የኑሮ ጫና ያመላክታል። በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ወድነት አሁን ላይ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ በእጅጉ እየፈተነ ይገኛል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የኑሮ ወድነት ተከሠተ የሚባለው የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም ወይም ገቢ ማነስ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተደምሮ የሚፈጥረው የመግዛት አቅም መዳከም ነው። በኢትዮጵያ ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ድረስ የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እያሻቀበ ቢሆንም፣ የአብዛኛው የማኅበረሰቡ ከፍል ገቢ ወይም የመግዛት አቅም ግን ከዋጋ ግሽበቱ እኩል ማደግ አለመቻሉን የዘርፉ ባለሙያዎቸ ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቶ አሁን ላይ ደግሞ ተጨማሪ አባባሽ ሁኔታዎች ገጥመውታል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያሳደረው ተጽእኖ እንዳለ ሆኖ፣ ከሰሜኑ ጦርነት መከሰት በኋላ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ በሳምንት ልዩነት እያሻቀበ ሄዶ የአብዛኛውን ማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ በብዙ ፈትኗል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዩክሬንና በሩሲያ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከውስጣዊ ችግሮች በተጨማሪ ለዋጋ ግሽበት ሌላ ምክንያት መሆኑን መንግሥት እየገለጸ ነው። የጦርነት መራዘምም የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ እንደሚያደርግ እና የማኅበረሰቡን ኑሮ እንደሚፈታተን የዘርፉ ባለሙያዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።
ቁጥሮች ምን ይላሉ?
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን ያመላክታል። ይህ በየዓመቱ እያደገ የመጣው የዋጋ ግሽበት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ማለትም 2005 ላይ ዓመታዊ አጠቀላይ የዋጋ ግሽበት 20 በመቶ ነበር።
ታዋቂው የመረጃ ቋት ስታቲስታ በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1986 እስከ 2021 ያሉትን ዓመታት ያካተተ የ35 ዓመት የኢትዮጵያ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ ያወጣው መረጃ ተከታዩን መረጃ አቀብሎናል። በኢትዮጵያ ከ35 ዓመታት በፊት የነበረው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት 5.55 በመቶ ነበር። እንደ ስታቲስታ መረጃ፣ ኢትዮጵያ በተጠቀሰው 35 ዓመት ውስጥ 2008 ላይ 44.37 በመቶ በማስመዝግብ ከፍተኛውን የዋጋ ግሽበት አሳልፋለች። በዓመቱ በ2009 ከ44.37 በመቶ በ8.48 በመቶ ዝቅ ካለ በኋላ፣ በ2011 ግሽበቱ 33.23 በመቶ ደርሶ እንደነበር መረጃው ያሳያል። ከዐስር ዓመት በፊት 33.23 በመቶ ደርሶ የነበረው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት በ2016 ማለትም ከአምስት ዓመት በኋላ ወደ 6.63 በመቶ ቢወርድም፣ ከዚያ ወዲህ በተከታታይ በየዓመቱ እያሻቀበ በ2021 የኢትዮጵያ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት 25.2 በመቶ ደርሷል።
ባለፉት አራት ዓመታት የነበረውን ዕድገት ደግሞ ስንመለከት፣ በ2010 የካቲት ወር ላይ የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 15.2 በመቶ ሲሆን፣ የምግብ ፍጆታዎች ግሽበት 19.9 በመቶ ነበር። ከአራት ዓመት በኋላ በተመሳሳይ ጊዜ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 33.6 በመቶ የደረሰ ደርሷል። በምግብ ፍጆታ ደግሞ ወደ 41 በመቶ አድጓል።
ባለፉት ሦስትና አራት ወራት ያለውን የዋጋ ግሽበት ስንመለከት ደግሞ፣ የ2014 የታኅሣሥ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 35.1 በመቶ ጭማሪ ዐሳይቷል። እንደዛው ሁሉ በምግብ ነክ ግብዓቶች ግሽበት ደግሞ 41.6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል። እንዲሁም፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት የታኅሣሥ ወር 2014 ካለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር 2013 ጋር ሲነጻጸርም የ26.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በኅዳር ወር 2014 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 33.0 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ወር ልዩነት ወደ 35.1 በመቶ ከፍ ብሏል። የምግብ ዋጋ ግሽበት የኅዳር ወር 2014 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 38.9 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ወር ውስጥ ወደ 41.6 በመቶ ከፍ ብሏል።
የ2014 የጥር ወር የዋጋ ግሽበት ዕድገትን ስንመለከት ከ2013 ተመሳሳይ ወቅታ ጋር ሲነጻጸር አጠቀላይ የዋጋ ግሽበት ዕድገቱ 34.5 በመቶ ሲሆን፣ የምግብ ፍጆታዎች ደግሞ የ39.9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ይህ ወቅት የምርት መሆኑን ተከትሎ እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ባቄላና ምሥር ላይ አንጻራዊ ቅናሽ ነበር።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየወሩ በሚያወጣው መረጃ መሠረት ያለፈው የካቲት 2014 አጠቀላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ33.6 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ የምግብ ዋጋ ግሽበት ደግሞ 41.9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ምንም እንኳን የተጠናቀቀው መጋቢት ወር ዋጋ ግሽበት መረጃ ባይወጣም፣ ባለፈው 2013 መጋቢት ወር ላይ የነበረው አጠቀላይ የዋጋ ግሽበት 20.6 በመቶ እንደነበር የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል።
የኑሮ ውድነት ለምን በረታ?
ለዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያቶች ከሚባሉት መካከል የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የገበያ ምኅዳር ብልሽት ወይም ሕገ ወጥ ደላሎች በገበያ ውስጥ የሚፈጥሩት ጣልቃ ገብነት እና የጥሬ ገንዘብ ሥርጭት መብዛት በቀዳሚነት የሚነሱ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ፣ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በኢትዮጵያ በየጊዜው እያደገ ለመጣው የዋጋ ግሽበት እንደመንስኤ እየተጠቀሱ የሚገኙት የውጭ ድጋፍ ማጠርና የውስጥ ፖለቲካ አለመረጋጋት መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር የኢትዮጵያን ዋጋ ግሽበት አስመልክቶ ያወጣው ጥናት ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር የቀረበና በአጥናፉ ተክለብርሃን (ዶ/ር) የተጠና፣ የኢትዮጵያ የዐሥር ዓመት የዋጋ ግሽበት ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ ከኹለት ዓመት በፊት የወጣው ጥናት እንደሚያሳየው፣ የፖለቲካ ችግሮች፣ የገንዘብ ሥርጭት መብዛት ወይም ያልተገባ የገንዘብ አቅርቦት፣ የመንግሥት ተቋማዊ አቅም ማነስ ወይም ተቋማዊ የአሠራር ችግሮች፣ ከምርት አቅርቦትና ከገበያ መዋቅር ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የኢንዱስትሪ ማምረቻ ወጪዎች መናር፣ የውጪና ገቢ ምርት አለመመጣጠን በጥናቱ ውስጥ የተነሱና ለአስርት ዓመታት የዋጋ ግሽበት መንስኤ መሆናቸውን ያሳያል።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት፣ በተንከባላይ የምርት አቅርቦት ዕጥረት፣ በመንግሥት በጀት አጠቃቀም ችግር፣ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች ዋጋ ጭማሪ፣ የገበያው በሥርዓትና በአግባቡ አለመመራት ብሎም የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት በመንግሥት በኩል በቂ ምላሽ እያገኘ ባለመሆኑ በየጊዜው እያደገና እየተባባሰ መምጣቱን ያብራራሉ።
በኢትዮጵያ የተከሠተው ጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች፣ ብሎም የፖለቲካ ምኅዳሩ በምርት አቅርቦትና ፍላጎት ላይ የፈጠረው አለመመጣጠን ለዋጋ ግሽበት ምክንያት እንደሆነ ባለሙያው አያይዘው አንስተዋል። እንዲሁም በጦርነትና በጸጥታ ችግር ውስጥ የሚገኘው የማኅበረሰብ ክፍል ምርት መስተጓጎሉ በምርት አቅርቦት ላይ ክፍተት እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።
የኑሮ ውድነቱ ምን ደረጀ ላይ ነው?
በኢትዮጵያ የተከሠተው የኑሮ ውድነት በየጊዜው እያሻቀበ ቢመጣም፣ አሁንም ኹነኛ መልስ እየተሠጠው አለመሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ። በየጊዜው እያሻቀበ የመጣው የኑሮ ውድነት ላለፉት ተከታታይ ዓመታት በፍጥነት እያደገ ቢመጣም፣ መንግሥት የኑሮ ወድነቱን ባለበት የሚገታ መፍትሔ አለመስጠቱም ይነሳል።
የኑሮ ወድነት ተከሠተ የሚባለው የዜጎች የመግዛት አቅም ከጊዜ ወጊዜ እየተዳከመ ሲመጣ ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን፣ አሁን በኢትዮጵያ እንደ አገር ከዋጋ ግሽበቱ ጋር አብሮ የሚያድግ እና ትልቅ ገቢ ባላቸው ሰዎች ላይ የኑሮ ውድነት ተከስቷል ማለት አይቻልም ይላሉ። ይሁን እንጂ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ጊዜያዊ ወይም የዕለት ሥራ ላይ ኑራቸውን መሠረት ያደረጉ ዜጎች ላይ የኑሮ ውድነት መከሠቱን ይገልጻሉ።
በጊዜያዊ ገቢ የሚተዳደሩና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ከፍሎች አሁን በተከሠተው የኑሮ ውድነት በጣም ተጎጂ መሆናቸውን የሚገልጹት ባለሙያው፣ በኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በኢ-መደበኛ ወይም “ቀን ሠርቶ ለማታ” የሚባሉ ዓይነት ሥራዎች ላይ የተሠማራ ነው ይላሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሴቶች አብዛኛውን ቁጥር እንደሚይዙና የኑሮ ውደነቱ በሴቶች ላይ ጫናው የበረታ እንደሚሆን ያብራራሉ።
የዋጋ ግሽበቱ የዕድገት መጠኑ ይለያይ እንጂ ከምግብ እስከ ቁሳቁስ፣ ከአልባሳት እስከ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ሆኖ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮው እየፈተነ ነው።
ዋሲሁን በመንግሥት በኩል በቂ የመፍትሔ ምላሽ አለመሰጠቱን ይገልጻሉ። ‹‹የዜጎች ኑሮ የተሻለ እንዲሆን መንግሥት ኃላፊነት አለበት›› የሚሉት ዋሲሁን፣ መንግሥት የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት የማሟላትና የተሻለ ገቢ እንዲኖራቸው የማድረግ ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ ለችግሩ በቂ ምላሽ እየሠጠ አይደለም ይላሉ።
‹‹መንግሥት ከማኅበረሰቡ እኩል ነው እየሠማ ያለው›› የሚሉት ባለሙያው፣ መንግሥት ችግሩን ልብ እንዲለውና አስቅድሞ መፍትሔ እንዲያስቀምጥ የዘርፉ ባለሙያዎች ብንወተውትም፣ ጠብ የሚሉ የመፍትሔ ሐሳቦች አላቀረበም ይላሉ። መንግሥት ከማኅበረሰቡ ቀድሞ ችግሩን መረዳትና መፍትሔ ማበጀት ካልቻለ፣ ዜጎች ምን ያድርጉ ወደሚለው መግባት አስፈላጊ ነውም ብለዋል። ማኅበረሰቡ መዘጋጀት አለበት የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን፣ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም እንዳልሆነ አሳስበዋል።
አሁን ባለው ወቅታዊ ኹኔታ የኑሮ ውድነቱ በውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የተወጠረ መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው የሚገልጹት ዋሲሁን፣ ማኅበረሰቡ ከወዲሁ ራሱን ማዘጋጀትና ወጪ ቆጣቢ አኗኗር ሥልት መከተልን መለማመድ እንዳለበት ጠቁመዋል።
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ከሠሞኑ በኑሮ ወድነት ዙሪያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ኹኔታ ‹ኅብረተሰቡ የአኗኗር፣ የአበላል፣ የአመጋገብ ዘይቤውን መቀየር አለበት።›› የሚል መልዕክት አስተላልፏል። መንግሥት በየጊዜው እያደገ ለመጣው የዋጋ ግሽበት በመግለጫው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ከገበያ ሥርዓት ቁጥጥር፣ ከውጭ የተገዙ ሸቀጦችን ማስገባትና አዲስ ፈጣን ግዢ ማካሔድ፣ የአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ብሎም ማኅበረሰቡን የመፍትሔ አካል ማድረግ ናቸው።
መንግሥት በሰጠው መግለጫ የኑሮ ውድነቱን በረዥምና በአጭር ጊዜ ለመፍታት ኅብረተሰቡን የመፍትሔ አካል ማድረግ አንዱ አማራጭ ነው ብሏል። ኅብረተሰቡ እንዴት የመፍትሔ አካል መሆን እንዳለበት ሲገልጽም ‹‹ኅብረተሰቡ ከወቅቱ ኹኔታ ጋር የመጀመሪያው ጉዳይ እራሱን ማስማማት አለበት። የአኗኗር፣ የአለባበስ፣ የአመጋገብ ዘይቤውን መቀየር አለበት። የገንዘብ አያያዝ ሥርዓቱንም መቀየር ይኖርበታል፤ ቁጠባን በስፋት መለማመድ ይጠበቅበታል። ከዓለም ዐቀፍ የዋጋ መጨመር ጋር የተያያዘውን ጉዳይ መንግሥት ምንም ማድረግ አይችልም›› ብሏል።
መንግሥት ለማኅበረሰቡ ባስተላለፈው መልዕክት ‹የአበላል ዘይቤ እስከ መቀየር› የደረሰው የችግሩን አሳሳቢነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው የሚሉት ዋሲሁን፣ እንደዚህ እውነቱን ተናግሮ ማኅበረሰቡን ማዘጋጀት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል። መንግሥት ያስተላለፈው መልዕክት ተገቢ መሆኑን የሚገልጹት ዋሲሁን፣ ማኅበረሰቡ ችግሩን ተገንዝቦ ከወዲሁ እራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት ጠቁመዋል።
እስከ መቼ?
በኢትዮጵያ የተከሠተውን የዋጋ ንረት ተከትሎ ዝቅተኛ ገቢ ባለው የማኅበረሰብ ከፍል ላይ የተከሠተው የኑሮ ውድነት እስካሁን ከመጣበት እና አሁን ካለው ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር ይገታል ወይስ በግስጋሴው ይቀጥላል የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ነው።
‹‹የዋጋ ንረት ሲወጣ ቀላል ነው፤ መቀነስ ግን ከባድ ነው›› የሚሉት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዋሲሁን፣ የዋጋ ንረት አሁን ካለው ውስጣዊና ውጫዊ ኹኔታ አንጻር በአጭር ጊዜ ለማስተካከል አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ እንደ አገር ሸማች መሆኗን ተከትሎ ከውጭ የምታስገባቸው ምርቶች በውጭ አገራት አቅርቦትና ዋጋ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው የየአገራቱ ችግሮች እስከቀጠሉ ድረስ ዋጋቸውም አብሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አገር የዋጋ ንረት አባባሽ ምክንያት የሆኑ የውስጥ ችግሮቿን ብትፈታ እንኳ፣ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ዋጋ ላይ የሚኖረው የወደፊት ዕጣ ፈንታ በምርት አቅራቢ ውጭ አገራት ኹኔታዎች ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን ባለሙያው ይናገራሉ። በቅርቡ የተቀሰቀሰው የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖው መታየቱን የሚያነሱት ባለሙያው፣ ችግሩን ለመግታት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያስፈለግ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል፣ የውስጥ ችግሮች ካልተፈቱ የዋጋ ንረቱን ማረጋጋት እንደማይቻል የሚገልጹት ባለሙያው፣ የፖለቲካ ኹኔታው በአጭር ጊዜ ካልተስተካከለ የዋጋ ንረቱና ኢኮኖሚው በአጭር ጊዜ እንደማይስተካከል አሳስበዋል። ከውስጥ ፖለቲካ ችግር ጋር በተገናኘ፣ የጸጥታ ችግር የተፈጠረባቸው አካባቢዎች ወደ ሠላማዊ ኹኔታ ተመልሰው ምርት ማምረት ካልቻሉ ችግሩ ወደፊትም እንደሚቀጥል አሳስበዋል። አሁን ካለው ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር የዋጋ ግሽበት የሚያስከትለው የኑሮ ውድነት ሊቀጥል ይችላል የሚሉት ዋሲሁን፣ መንግሥት ተዘጋጁ ያለው ችግሩ እንደሚቀጥል ሥጋት ስላለው ነው ይላሉ።
ማኅበረሰቡን ከከፋ ችግር ለመታደግ
የዋጋ ግሽበትና የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም ማነስ የፈጠረው የኑሮ ውድነት ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት የጀመረ ቢሆንም፣ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ዕድገቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሰ በመምጣቱ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ እየፈተነ፣ ግሽበቱም አሁንም እየገሰገሰ ነው። ታዲያ በዚህ ኹኔታ የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ ከመጣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ሸማች ከመሆኗና አሁን ካለው ዓለም ዐቀፍና አገራዊ ኹኔታ አንጻር ችግሩ የከፋ እንዳይሆን ከወዲሁ የዘርፉ ባለሙያዎች እያሳሰቡ ነው።
የዋጋ ንረቱ በያዘው ዕድገት የሚቀጥል ከሆነ የማኅበረሰቡን የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚገዳደርና ችግሩ የከፋ ስለሚሆን፣ ከወዲሁ ከማኅበረሰብ እስከ መንግሥት ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ዋሲሁን ይመክራሉ። ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ለረዥም ጊዜ መፍትሔ ሳያገኙ የሚቆዩ ከሆነ፣ የኑሮ ውድነቱ እስከ ምግብ ዕጥረት የሚደርስ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የሚገልጹት ዋሲሁን፣ መንግሥት በመጀመሪያ የዋጋ ንረቱን ባለበት ለማስቆም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።
የዋጋ ንረትን ባለበት ማስቆም በጣም ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን የሚገልፁት ዋሲሁን፣ ጎን ለጎን የፖለቲካ ኹኔታውን ማስተካከል አስፈላጊ ነው ብለዋል። በጸጥታ ችግር ምርት ያቆሙ አካባቢዎች ወደ ቀድመ ሠላማቸው በመመለስ ወደ ምርት ሥራ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባም ጠቆመዋል። በጸጥታ ችግሮች አምራች የሆኑ አካባቢዎች ምርት ማቆማቸው ገበያ ላይ ችግር ስለሚፈጥር ምርታማነትን ለማሳደግ የጸጥታ ችግሮችን አስተካክሎ ሠፊ መሬት ማልማት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የዋጋ ንረቱን ለማስቆም መንግሥት የጀመረውን የበጋ መስኖ ስንዴና የከተማ ግብርና ወይም የጓሮ አትክልት ልማት አጠናክሮ በመቀጠል፣ ማኅበረሰቡ ምርታማነቱን እንዲጨምር ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያው አመላክተዋል። አክለውም፣ የገበያ ሥርዓቱ ላይ የሚታየውን ችግር በተገቢው መንገድ ቁጥጥር በማድረግ ረገድ መንግሥት በየደረጃው ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።
አሁን ባለው ወቅታዊ ኹኔታ መንግሥት ወጪ መቀነስ እንዳለበት የሚገልጹት ባለሙያው፣ መንግሥት ድግስ መቀነስ፣ አዲስ ፕሮጀክት ከመጀመር መቆጠብ፣ ወጪ ቁጣቢ ሥራ መሥራት እንዳለበት አንስተዋል። መንግሥት ከሕዝብ ጋር በኹኔታዎች ላይ መናበብ እንዳለበት የሚጠቁሙት ባለሙያው፣ አሁን ላይ መንግሥት የሚለውና ሕዝብ የሚለው ‹ኹለት ስለተለያዩ አገራት የምናወራ ነው የሚመስለው› ብለዋል።
በዋጋ ንረት እና በገቢ ማነስ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም እንደ ማኅበረሰብ የሚደረጉ ዝግጅቶችና የሚሠሩ ሥራዎች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው፣ ከወዲሁ ማኅበረሰቡን በምርት፣ በአኗኗር፣ በቁጠባና በመሳሰሉት መዘጋጀት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014



